የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር “የስፖርት ጨዋነት ምንጮች” በሚል ርዕስ በሸራተን አዲስ ሆቴል ያዘጋጀውን የባለድርሻ አካላት የሁለት ቀናት የውይይት መድረክ: ባለ 12  ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቀቀ፡፡

በውይይቱ ላይ በስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት መንስኤዎች እና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት ሀሳባቸውን ያካፈሉ ሲሆን ይህንኑ ተከትሎ የተዘጋጀው የጉባኤው ሙሉ የአቋም መግለጫ ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

የአቋም መግለጫ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ ‹‹በኢትዮጵያዊያኖች መካከል ውይይት መባዛት አለበት›› ባሉት መሠረት፤ በሚያዚያ 14 እና 15 2011 ዓ.ም በሼራተን አዲስ ሆቴል ለሁለት ቀን የተካሄደው “የስፖርት ጨዋነት ምንጮች” የውይይት መድረክ፤ የሚቀጥለውን የአቋም መግለጫ ለኢትዮጵያ መንግሥት እንዲቀርብ በጋራ ተስማምቷል፡፡

በቅድሚያም ጉባዔው፡-

1) የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ሚኒስቴር እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በውይይቱ ላይ በመካፈላቸው፣እንዲሁም

2) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በመተባበሩና ለውጥ ፈላጊ መሆኑን በመግለጹ የተሰማውን ደስታ እየገለጸ፤

3) የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር በራስ ተነሳሽነትና የጠቅላይ ሚኒስትሩን መመሪያ በመከተል የውይይቱን መድረክ ስላዘጋጀ ምስጋናውን እያቀረበ፤

4) በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጨዋታ አካባቢ የሚፈጠረው ረብሻ በጎሣ፣ በብሔር ወይም በቋንቋ ልዩነት ላይ የተመሠረተ እየሆነ መምጣቱንበመረዳት፣

5) ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች መካከል የፖለቲካ አመለካከቶቻቸውን የሚያንጸባርቁ ስሞች፣አርማዎችና ልዩ ልዩ ምልክቶች ያሏቸው መኖራቸውን በመገንዘብ፣

6) ክልሎችም ሆኑ ከተሞች እግር ኳስንየፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ማድረጋቸውን በማስተዋል፣

7) በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳም፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ጨዋታ አስጊና አሳዛኝ ሁኔታ ላይ በመገኘቱ፣

8) ዘርን የተመለከቱ የኦሊምፒክ ቻርተርና የኢንተርናሽናል ፌዴሬሽኖች ደንቦች እየተጣሱ በመሆኑ፣

9) የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ አስተዳዳሪዎች በሙያና በችሎታ ሳይሆን በብሔር ተዋፅዖ የሚመረጡበት አሠራር በመኖሩ፣

10) የትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች ስፖርት እንቅስቃሴ መዳከም በመጉላቱ፣

11) ያም ሆኖ፣ የእግር ኳስ ክለቦችን አቅም በመመዘንና ያገሪቱን ኢኮኖሚ በማገናዘብ፣

12) የኢትዮጵያ አንድነት የሚጠነክርበትና ሕዝቡም የሚዋሐድበት የስፖርት እንቅስቃሴው መሆኑን በማመን፣

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ  ሪፐብሊክ መንግሥት የስፖርት እንቅስቃሴውን ችግሮች በመረዳትና ዓለማቀፍ የስፖርቶቹን ሕጎች እና ደንቦች ለማክበር ይቻል ዘንድ ተገቢውን እርምጃዎች ለመውሰድ እንዲረዳ የውይይቱ መድረክ በሚከተሉት አቋሞች ላይ በጋራ ተስማምቷል፡-

1) የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ የዘር ልዩነት እንዲጠፋና የኦሊምፒክ ቻርተርና የኢንተርናሽናል ስፖርት ፌዴሬሽኖች ደንቦች እንዲከበሩ እንዲደረግ፤

2) ዘራቸውን ወይም ብሔራቸውን መሠረት አድርገው የተቋቋሙት የእግር ኳስ ክለቦች ስማቸውን እንዲቀይሩ፤

3) የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የልዩ ልዩ ስፖርት ፌዴሬሽኖች መሪዎችና አባሎች በዘራቸው ሳይሆን በሞያቸውና በችሎታቸው ብቻ እንዲመረጡ፤

4) የትምህርት ሚኒስቴር ስፖርት በትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች እንዲስፋፋ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ፤

5) የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ አገልጋዮች በጎ ፈቃደኞች መሆናቸውን በመገንዘብ የወጣቱ ትውልድ በበጎ ፈቃደኝነት እንዲሰለፍ እንዲበረታታ፤

6) የኢትዮጵያን ስፖርት ድርጅቶች ለማገልገል የሚመኙ ሁሉ በስነ-ምግባር ኮሚቴዎችና በመንግሥት ፀጥታና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም በፖሊስና በፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲመረመሩ፤

7) ኢትዮጵያን በዓለም ስፖርት ጉባኤዎች የሚወክሉት መልዕክተኞች ቢያንስ አንድ የውጭ አገር ቋንቋ አጣርተው የሚያውቁና ውይይቱን መከታተል የሚችሉ መሆናቸውእንዲረጋገጥ፤

8) የፖሊስና የደህንነት ድርጅቶች የስፖርት ውድድሮችን በተለይ እግር ኳስ ጨዋታን በፀጥታና በጥበቃ መስክ ከፌዴሬሽኖቹ ጋር በመተባበር የሚሠሩ ቋሚ ኃላፊዎች በየከተሞቹ እንዲመደቡ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ፤

9) በኢትዮጵያ ያሉት የስፖርት ስታዲዮሞችና መጫወቻ ስፍራዎች ተገቢ የእሳት አደጋ መከላከያ እንዲሁም የሕክምናና የአምቡላንስ አገልግሎትና በቂ የመፀዳጃ ስፍራዎች እንዲኖራቸው፤

10) የአልኮል መጠጥ ከስታዲዮሞች ውስጥ እንዳይሸጥና ሲጃራ ማጨስ ክልክል መሆኑን እንዲታወጅ፤

11) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚዘጋጁት ውድድሮች ፎርማት ለክለቦች ተስማሚና ለስፖርት ዕድገት የሚጠቅም እንዲሆን እንዲደረግ፤

12) ይህን የአቋም መግለጫ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያቀርቡልንና መንግሥትም ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የኢትዮጵያ ስፖርት እንቅስቃሴ የኦሊምፒክ ቻርተር አክባሪ እንዲሆን ተገቢውን ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ክብርት የሰላም ሚኒስትርንና ክብርት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትርን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

አዲስ አበባ
ሚያዚያ 15 ቀን 2011 ዓ.ም
የስፖርት ጨዋነት ምንጮች የውይይት መድረክ

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *