ጋዜጠኛ ታምሩ አለሙ

ኑሮውን በአሜሪካን ሀገር ያደረገው ጋዜጠኛ ታምሩ አለሙ የምስጋና እና የእውቅና ሽልማት ሊበረከትለት ነው።

ጋዜጠኛው ከሚኖርበት ዋሽንግተን ዲሲ በመሆን፡ የቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክን፣ የእግርኳስ ብሔራዊ ቡድናችንን የ2021 ካሜሮን አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እና ከሰሞኑ የተጠናቀቀውን የኦሬገኑን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ባመረ መልኩ ሲዘግብ እንደነበር ይታወሳል።

ሽልማቱን፡ ጋዜጠኛው በተጣበበ ጊዜው እና አመች ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በሰራው አስደናቂ ስራ የተደሰቱት፡ የግራንድ ቴክኖሎጂና የጆሳምቢን ትሬዲንግ ባለቤት የሆኑት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ እንዳዘጋጁለትም ለማወቅ ችለናል።

ለጋዜጠኛ ታምሩ የሚሰጠው የምስክር ወረቀት እና ልዩ አዋርድ፡ አቶ ዮሴፍ ለዕረፍት በሚገኙበት ጀርመን ሀገር በልዩ ዲዛይን የተሰራ እንደሆነና በቅርቡ ወደ አሜሪካ ሲሄዱ እንደሚያበረክቱለትም ተናግረዋል።

አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ

ሽልማቱ ስለፈጠረበት ስሜት አስተያዬቱን ለልዩ ስፖርት የሰጠው ጋዜጠኛው፡ “ዕውቅናው ፈጽሞ ያልጠበቅኩት እና ደስ የሚል ስሜት የፈጠረብኝ ነው። የምውደውን ሙያዬን አሁን ካለሁበት የስራ እና የትምህርት ሁኔታ እያጣጣምኩ ለመከወን የማደርገውን ጥረት ተረድተው፡ የእውቅና እና የምስጋና ሽልማቱን ያዘጋጁልኝ አቶ ዮሴፍንም አመሰግናለሁ።” ብሏል።

በተጨማሪም፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ከአለም ሻምፒዮናው መጠናቀቅ በኋላ፡ በቀጥታ በመደወል ስለሚሰራው ስራ ላቀረበችለት ምስጋና እና ማበረታቻም አክብሮቱን ገልጿል።

ጋዜጠኛ ታምሩ አለሙ ከዚህ ቀደም በሬዲዮ ፋና፣ በኢቲቪ፣ በብስራት ሬዲዮና በሌሎች ተቋማት መስራቱ የሚታወስ ሲሆን፡ በአሁኑ ሰዓት፡ በዋናነት በማህበራዊ ሚዲያው፡ በተጨማሪነት ደግሞ በተለያዩ የብሮድካስት ሚዲያዎች በፍሪላንሰርነት በሙያው እያገለገለ ይገኛል።

ጋዜጠኛው ከኮ/ር ደራርቱ ጋር
author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *