ኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም

ኢዩጂን ሀምሌ 08/2014 ዓ.ም – የአትሌቲክሱ ዓለም፡ የዓለም ዋንጫ፡ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለ18ኛ ጊዜ፡ በአስተናጋጇ ሀገረ አሜሪካ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ መካሄድ ይጀምራል።

ለቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት የስፖርቱን አለም ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ ይዞ እንደሚቆይ የሚገመተው ሻምፒዮናው፡ 192 ሀገራትን የሚወከሉ እና ወደ 2000 የሚጠጉ አትሌቶች፡ በ49 የውድድር አይነቶች የአለም ኮከብ ለመሆን ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያደርጉበት ይጠበቃል።

በስፖርት መሰረተ ልማቷ እና የአትሌቲክስ ውጤታማነቷ ይህ ቀረሽ የማትባለው አስተናጋጇ አሜሪካም፡ በየአመቱ የዳይመንድ ሊግ ውድድር በሚካሄድበት የኦሬገን ዩኒቨርሲቲው ሄይዋርድ ፊልድ ስቴዲየም፡ የምርጦቹን ፉክክር ለማከናወን ዝግጅቷን አጠናቃለች።

ነገር ግን ወደ ስፍራው የሚያመሩ አትሌቶች፣ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች እና ደጋፊዎች ላይ ከመግቢያ ቪዛ ጋር ተያይዘው በተፈጠሩ መጉላላቶች እና ክልከላወች ምክንያት ውድድሩ ላይ አሉታዊ ስሜት እንዳይፈጠር የሚል ስጋት ብዙዎች ላይ ይታያል።

የውድድሩ የምንጊዜም ምርጥ ሰባተኛዋ ውጤታማ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያም፡ እንደወትሮው ሁሉ ለከፍተኛ ውጤት የምትጠበቅበትን እና ለ18ኛ ጊዜ የምትሳተፍበትን ውድድር፡ በወንዶች 3000ሜ መሰናክል እና በሴቶች የ1500ሜ ማጠሪያወች ውድድሯን ዛሬ ትጀምራለች።


በውድድሩ ላይ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች የየሀገራቸውን ስም ከፍ አድርጎ ከማስጠራት ባለፈ ጠቀም ያለ የገንዘብ ሽልማትም ተዘጋጅቶላቸዋል። በዚህም መሰረት በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ የሚጨርሱ አትሌቶች ከ80,000 እስከ 5000ሺህ ዶላር የተዘጋጀላቸው ሲሆን የዓለም ክብረወሰን ለሚሰብሩ ደግሞ የተጨማሪ 100,000 ሺህ ዶላር ጉርሻ በጃፓኑ ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ቲዲኬ አማካኝነት ቀርቦላቸዋል።

የአለም አትሌቲክስ ጉባኤ ስፖርቱ ልክ እንደ እግር ኳሱ ሁሉ ከኦሊምፒክ በተጨማሪ የራሱ የሆነ አለም አቀፍ ውድድር ማከናወን እንዳለበት በወሰነው መሰረት፡ ሻምፒዮናውን እኤአ ከ1983 ጀምሮ ያለመቆራረጥ እየተዘጋጀ ይገኛል።

ይሄኛው ውድድር ከአንድ አመት በፊት መካሄድ የነበረበት ቢሆንም፡ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የጊዜ ሽግሽግ ካደረገው የ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ጋር በመደራረቡ ምክንያት ወደ ዘንድሮ መተላለፉ ይታወሳል።

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *