አዲስ አበባ – ሀምሌ 02/2014ዓ.ም የፊታችን አርብ በአሜሪካ ኦሪጎን በሚካሄደው የአለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና ተሳታፊ የሆነው የልዑካን ቡድን፡ ዛሬ ማምሻውን በስካይላይት ሆቴል በተከናወነ ስነስርዓት አሸኛኘት ተደርጎለታል።

በመርሃግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ የባህልና ስፖርት ሚንስትሩ ክቡር አቶ ቀጀላ መርዳሳ፡ ሚንስቴር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተው የማበረታቻ ንግግሮችን አድርገዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ አትሌቶችን ወክለው ንግግር ያደረጉት አትሌት ሰለሞን ባረጋ እና ወርቅውሃ ጌታቸው ስለዝግጅታቸው ሁኔታ ሀሳባቸውን ያካፈሉ ሲሆን፣ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ሰለሞን፡ ጥሩ የዝግጂት ጊዜ እንደነበራቸው ገልጾ “አሁን የሚቀረን አሜሪካን ሄዶ ጥሩ ውጤት ይዞ መመለስ ነው። እንደ ተማሪ ስናጠና ቆይተናል የቀረን ፈተናው ነው” ሲል፡ የ3000ሜ መሰናክል የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ወርቅውሃ ጌታቸው በበኩሏ “ክረምቱ አስቸጋሪ ቢሆንም ጥሩ ዝግጅት አድርገናል” ብላለች።

የብሔራዊ ቡድኑ የ5000ሜ እና 10,000ሜ ዋና አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሼቦ፡ አትሌቶቹ በጥሩ ሁኔታ ሲዘጋጁ መቆየታቸውን አስታውሰው፡ አሁን ላይ ካላቸው ወቅታዊ አቋም በመነሳትም በውድድሩ የተሻለ ነገር ይመዘገባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ጠቆም አድርገዋል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ኢትዮጵያ በውድድሩ የነበራትን ውጤታማነት በማስታወስ አትሌቶቹ ልክ እንደከዚህቀደሙ ሁሉ ህዝብን የሚያስደስት እና ሀገርን የሚያኮራ ውጤት ለማስመዝገብ እንዲተጉ አሳስበዋል።

በስፍራው የተገኙት የኢፌድሪ ባህል እና ስፖርት ሚንስቴር ክቡር አቶ ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው፡ ልዑካን ቡድኑ በጠንካራ የራስ መተማማን መንፈስ በመፎካከር በድል ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት ከሰኞ ጀምሮ በአምስት ዙሮች ውድድሩ ወደ ሚካሄድባት የፖርትላንዷ፡ ኦሪጎን ከተማ እንደሚያቀኑ ይጠበቃል።

18ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሐምሌ 8 እስከ 17/2014ዓ.ም ይከናወናል።

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *