የኢትዮጵያውያንን ስፖርት አፍቃሪያን ተደራሽ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የስፖርት ይዘቶች በሱፐርስፖርት/ዲኤስቲቪ የሚያቀርብ “ሱፐርስፖርት ልዩ” ቻነል ቁጥር 240ን፣ በትላንትናው ዕለት የተለያዩ የስፖርት፣ ባህል፣ ሚዲያና ኪነጥበብ የመንግስት ኃላፊዎችና ታላላቅ እንግዶች በተገኙበት በሀያት ሪጄንሲ ሆቴል ተመርቋል፡፡

የመልቲቾይስ ኢትዮጵያ የሬጉላቶሪና ኮርፖሬት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መታሰቢያ በላይነህ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፡ ለአቦል ቤተሰቦችና የፊልም ኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት እንኳን ለቻነሉ አንደኛ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን፡ ለስፖርቱ ባለድርሻዎችም አዲሱ የሱፐርስፖርት ልዩ ቻናል 240 ስራ በመጀመሩ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

አቶ መታሰቢያ የአፍሪካ ግዙፉ ስፖርትና መዝናኛ ይዘቶች አቅራቢው መልቲቾይስ አፍሪካ በሚሰራባቸው አገራት የህዝብና የሀገር ገፅታ ፣ ባህልና ታሪክ ለዓለም እንዲደርሱ እየሰራ ነው ያሉ ሲሆን በኢትዮጵያ ይህንኑ የሚያንፀባርቁ አቦልና ሱፐርስፖርት ልዩ ቻነሎች ተከፍተዋል ብለዋል።

ከአማርኛ በተጨማሪም ኦሮምኛን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን በስርጭት ጊዜ የመጠቀም ዕቅድ አለ ያሉ ሲሆን፡ መልቲቾይስ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በመመደብ ከአፍሪካ ሀገራት በላቀ መልኩ በኢትዮጵያ ለመስራት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በዕለቱ የተገኙት የክብር እንግዳ የኢትዮጵያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንደተናገሩት “ስፖርት መዝናኛ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የልማት አንዱ ምሶሶ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደ መንግስት የያዘችው ስትራቴጂ ስፖርት ለልማት የሚል ነው፡፡ በዚህ አግባብ ከመልቲቾይስ ጋር በትብብር እንሰራለን፡፡ በጀመርነው ልማትና አገራዊ የገፅታ ግንባታ ትክክለኛ ሚዲያ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በመሆኑም የድርሻችንን የምናግዝ ይሆናል፡፡ መልቲቾይስም ስፖርቱንና ባህሉን አስተሳስሮ የገፅታ ግንባታና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት እንዲሰራ አደራ እንላለን፡፡” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ ኢድሪስ በበኩላቸው “ዲኤስቲቪ ትናንት በአቦል የጀመረውን ዛሬ ደግሞ በሱፐርስፖርት ልዩ መምጣቱ አስዳሳች ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ዲኤስቲቪ ዓለምን ወደኛ ነበር የሚያመጣው አሁን ደግሞ እኛን ወደ ዓለም እየወሰደ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ለአፍሪካና ለዓለም ፤ ዓለምንና አፍሪካን ደግሞ ለእኛ በማስተዋወቅና በማስተሳሰር ትልቅ የገፅታ ግንባታ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ዲኤስቲቪ በዚህ ረገድ አይቻልም የተባለውን ችሎ ያሳየ ነው፡፡ በቀጣይም በሌሎች ተጨማሪ ቻናሎችና ቋንቋዎች እንደምናገኘው ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከመልቲቾይስ ጋር በትብብር ስምምነት የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ በሱፐርስፐርት/ዲኤስቲቪ አማካኝነት አህጉራዊ ስርጭት መሰጠቱ ያስገኘውን ጠቀሜታ በተመለከተ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ/ማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ሰይፈ “ ዲኤስቪ ፕሪሚየር ሊጋችንን በፋይናንስ ከመደገፍ ባለፈ በአቅም ግንባታ ረገድ ከፍተኛ እገዛ እያደረገልን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊዎች ሽልማት በመጠንና በዓይነት ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ዲኤስቲቪ የሊጋችንን የመታየት ዕድል በመፍጠሩ የነበረብንን ክፈተት እንድናውቅ ብቻም ሳይሆን ክፍተታችንን ለመሙላት ተግተን እንድንሰራ መነሳሳት ፈጥሮልናል፡፡” ብለዋል፡፡

የዓለም የምንጊዜም ምርጡ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴም ሱፐርስፖርት ለስፖርቱ ያደረገውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በመድረኩ ራሱን እንደምሳሌ በመጥቀስ መስክሯል፡፡ ኃይሌ “እኔን ያደመቀኝ ሱፐርስፖርት ነው፡፡ በተከታታይ ሶስት ዓመታት ማለት በ1995፣ 1996 እና 1997 እኤአ የሱፐርስፖርት ኮከብ ተሸላሚ አትሌት ነበርኩ፡፡ እኔን በዓለም ላይ እንዳደመቃችሁኝ ሁሉ የአሁኑን የአትሌቲክስ ትውልድ ለዓለም እንድታስተዋውቁ አደራ እላለሁ” ብሏል፡፡

ሰርቢያ ቤልግሬድ የ2022 የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶችን ከዓለም በአንደኝነት ማሸነፍ በአዲሱ ሱፐርስፖርት ልዩ በቀጥታ በአማርኛ መሰራጨቱን በተመለከተ በመድረኩ የተጠየቁት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሸቦ “ዲኤስቪ ዓይናፋርነታችንን የሚገፍ በዓለም መድረክ ላይ አትሌቶቻችን ራሳቸውን የሚገልፁበት፣ ስለሀገራቸውና ስለአትሌክሱ የሚናገሩበት የሚዲያ አማራጭ በመሆኑ ደስ ይለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ዲኤስቲቪ በኢትዮጵያ ለእግር ኳሱ የነበረውን ትኩረት በአትሌቲክሱ በመድገም የቤልግሬድ የቤት ውስጥ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የቀጥታ ዘገባ በማስተላለፉ የሚያስመሰግን ስራ ሰርቷል፡፡ እኛም በጣም ደስተኞች ነን፡፡ በተጨማሪም ለሌሎች ስፖርቶችም የመታያ ሜዳ ይሆናል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል፡፡

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *