ስዩም ከበደ ከባለቤቱ ወ/ሮ አስቴር ተስፋዬ እና ልጁ ናትናኤል ጋር

በ መንሱር አብዱልቀኒ – ለልዩ ስፖርት

‹‹’ጌታዬ ሆይ! እዚህ መድረክ ላይ እንዳታዋርደኝ’ እያልኩ ደጋግሜ ፀሎት አደረስኩ፡፡ መድረኩንና አጋጣሚውን አልቅሼ እንዳላበላሸው ሰጋሁ፡፡ ምራቄን ዋጥ ማድረግ እንዳለብኝ ለራሴ ነገርኩት፡፡ ወሬ ባበዛ ኖሮ እንባዬ ታምቆ ባልቀረ ነበር፡፡››

በሼራተን አዲስ የከዋክብቱ ምሽት ስዩም ከበደ የ2013 የኢትዮጵያ ኮከብ አሰልጣኝ ሆኖ ከተመረጠ በኋላ ሽልማቱን ለእናቱ ማስታወሻነት እንዲውልለት ሲናገር ከራሱ ጋር የገባበት የስሜት ግብግብ ነበር፡፡ እንባ የተናነቀው በአሰርት ዓመታት ሙያዊ ህይወቱ ባገኘው ክብር የደስታ ሲቃ ተሰምቶት አልነበረም፡፡ ከልጅነት እስከ ጉልምስና አብረውት ወጥተውና ወርደው በመጨረሻ ያቺን የሽልማት ምሽት ሳያዩ የተለዩት የእናቱ ጥልቅ ሃዘን ረብሾት እንጂ፡፡ ይህ ታሪክ ከዚያ ንግግር በስተጀርባ ያለው የአሰልጣኙ የህይወት ምሥጢር ነው፡፡

አላማጣ፣ ወሎ – 1962

‹‹ልጆች፡- ኑ አባታችሁን ታያላችሁ›› ተብለው ከትምህርት ቤት ተጠሩ፡፡ የ10 ዓመቱ ስዩም ከበደና ታናሽ እህቱ ሰሞኑን በቤት ያልነበሩትን አባት የሚያገኙ መስሏቸው ነበር፡፡

ስዩም በአላማጣ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገና የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ አባቱ አቶ ከበደ እሸቱ የከተማው አስተዳዳሪ የነበሩ ሹመኛ ጸሐፊ ናቸው፡፡ ከትምህርት ቤት መልስ ስዩም ወደ ቤቱ ሳይሆን ወደ አባቱ መሥሪያ ቤት ሄዶ ከእርሳቸው ጋር ይውልና አብሮ ወደ ቤት ይመለሳል፡፡ ይህ የቤቱ ትልቁ ወንድ ልጅ ልማድ ነው፡፡ ሌላኛው ወንድሙ መላኩ ገና ይድሃል፡፡ ክፉ ደጉን እንኳን አያውቅም ነበር፡፡

የልጅ ነገር…

መጫወቻ ኳስ የሚገዛለት፣ ከእኩዮቹ ጋር ሲጫወት በአድናቆት የሚመለከተው አባቱ በድንገት መታመሙን እንኳን አልሰማም፡፡ የሄዱት ለሽርሽር መስሎት ይሆናል፡፡ አቶ ከበደ ግን ህመም ጠንቶባቸው ወደ ደሴ ሆስፒታል ተወስደው በህይወት አልተመለሱም፡፡

አስከሬናቸው ወደ አላማጣ መጥቶ፣ ከዚያም ዳገቱን ተከትሎ ወዳለችው የትውልድ ቀዬአቸው ዞብል ተወስዶ ሲቀበር፣ ልጅ ስዩም ምን እየተከናወነ እንደሆነ እንኳን በቅጡ አልተረዳም፡፡

ሞት እስከ ወዲያኛው መለየት መሆኑን ያወቀው እያደር የቤቱ አባወራ እንዳልተመለሱ ካረጋገጠ በኋላ ነበር፡፡

ሰልስት ሰባትን፣ ሰባት ደግሞ የ40 ቀን መታሰቢያን አስከትሎ ከቤተ-ዘመዱ ዓይን ላይ እምባው ከደረቀ በኋላ እመት አበቡ ዘለቀ ትልቁን ወንድ ልጃቸውን ጠርተው ይዘውት ወደ ጓዳ ገቡ፡፡

ምስጢራቸውን የሚቆልፉበትን ብረት ሳጥን ከፍተው ስዩም ያልገመተውን ዕቃ አወጡ፡፡ ሮመር ሰዓትና አብሮትም መልዕክት የተጻፈበት ብጣሽ ወረቀት ነበር፡፡

‹‹ልጄ ሆይ፡- ምን እንደሁ አላውቅም፡፡ ግን አባትህ ይህን ማስታወሻ ጥሎልህ ነው ያለፈው፡፡ እስቲ ጽህፈቱን አንብበው›› ብለው ሰጡት፡፡

በወቅቱ ሽቅርቅሮች የሚያስሩት ሮመር ሰዓቱን ከተቀበለ በኋላ የተጠቀለለውን ወረቀት ከፈተው፡፡

እንዲህ ይላል፡፡

‹‹ችግር ቢያጋጥምህ ትካዜን አታብዛ፣

ቀንና መከራ ያልፋል እንደዋዛ››

ደሃ አባት ለልጁ የሚያወርሰው የዘልዓለም ምክር ነበር፡፡

ስዩም ከአባቱ አቶ ከበደ እሸቱ ጋር በ1960ዎቹ – አላማጣ

አዲስ አበባ – 2013

ሼራተን አዲስ

‹‹የ2013 ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምርጥ አሰልጣኝ…››

ሰውነት ቢሻው ከኤንቬሎፕ ውስጥ የተጻፈውን አወጡ፡፡

‹‹…ስዩም ከበደ!››

የአዳራሹ ጭብጨባ ተከለተ፡፡ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ልብም በኩራትና በትዝታ ሊቀልጥ ምንም አልቀረውም፡፡ አጼዎቹ በነገሡበት ዘመን የስዩም ኮከብነት ያልተጠበቀ ባይሆንም በሼራተን ላሊበላ አዳራሽ የታደሙ እንግዶች ምርጫውን በጭብጨባ አሞገሱት፡፡

ስዩም ስጋ ይዞታል፡፡ ከ18 ዓመታት በፊት እስከ መጨረሻው ጨዋታ ድረስ የዘለቀውን ፉክክር አሸንፎ ፈረሰኞቹን ለክብር ሲያበቃ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች በትከሻቸው ላይ ተሸክመውት ጨፍረዋል፡፡ አሁን ያን ማድረግ አይቻልም፡፡ በልጅነቱ በደቃቃነቱ የሚታወቀው ሰው ክብደትም ሆነ የስራ ልምድ ጨምሯል፡፡ በሙያውም ምራቁን ውጧል፡፡

ሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2013 ደግሞ በሼራተን ምሽት እንባውን ዋጥ አድርጎ ንግግሩን አሰማ፡፡

‹‹ይህ ዋንጫ መታሰቢያነቱ ከሁለት ዓመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየችኝ እናቴ ወይዘሮ አበቡ ዘለቀ ይሁንልኝ›› አለ፡፡ እናቱን የሚወድ ሁሉ ሲሰማው ስሜቱ መነካቱ አይቀርም፡፡ ስዩም ንግግሩን የጨረሰው፣ ሳግ መጣሁ መጣሁ እያለው፣ ከራሱ ጋር እየታገለ ነበር፡፡

‹‹ስለእናቴ መናገሬን ብቀጥል ኖሮ በእንባ መሸነፌ አይቀርም ነበር፡፡ ስለዚህ ማርዘም አልፈለግኩም›› ይላል አሰልጣኙ፡፡

እመት አበቡ በወጣትነታቸው ልቅም ያሉ ቆንጆ ወሎዬ ነበሩ፡፡ ባለቤታቸው ከሞት ተለይተው በዞብል ግብዓተ መሬታቸው ከተፈጸመ አንስቶ ‹‹ልጆቼ በእንጀራ አባት ስር አይኖሩም›› ብለው ለራሳቸው የገቡትን ቃል አላፈረሱም፡፡ የእናትነት ፍቅርን ሳያጎድሉባቸው ስድስቱን ልጆቻቸውን እናትም አባትም ሆነው፣ መቀነታቸውን አጥብቀው ለማዕረግ አብቅተዋቸዋል፡፡

የእመቲቱ የዚህ ዓለም ሩጫ ልጆቻቸውን ለወግ በማብቃት የሚጠናቀቅ ነበር፡፡ የመጨረሻዋ ልጃቸው ስራ እስክትይዝ ድረስ ጠብቀው በቃላቸው መሠረት የምንኩስና ቆብ ደፉ፡፡

የስዩምና የእናቱ ቅርበት ይለያል፡፡ የልጅነት የእግር ኳስ ህይወቱ ያለ እመት አበቡ ባልሰመረ፣ ኋላም የሙሉ ሰዓት የእግር ኳስ ባለሙያ ባልሆነ ነበር፡፡

‹‹ከአካባቢያችን ልጆች ጋር ማለዳ እየተነሳን ኳስ እንጫወት ነበር፡፡ አሰልጣኝም ነበረን፡፡ በዘመኑ አላርም ሰዓቶች ስላልነበሩ እናቴን ማልደሽ ቀስቅሺኝ ብዬ እተኛለሁ፡፡ ቀድሞ የተነሳ ተጫዋች በየደጃፋችን ማልዶ እየመጣ ያፏጭ ነበር፡፡ እማማ ‘ሰዓቱ ይረፍድበት ይሆን?’ ብላ በመጨነቅ በቅጡ የማትተኛባቸው ሌሊቶች ነበሩ፡፡

‹‹እንቅልፍ አድክሞኝ ከአልጋ ለመነሳት ሲከብደኝ እንኳን እናቴ ‹ልጄ፡- ተነስ ተጫወት፡፡ ስትመለስ በቅቤ የተለወሰ ቂጣ አዘጋጅቼ እጠብቅሃለሁ› እያለች ለእግር ኳስ እንድነሳሳ ታደርገኝ ነበር›› ይላል በትዝታ፡፡

ለልጅዋ ስኬት የምትመኝ የዋህ እናት የሞቲቬሽን ስልት መሆኑ ነው፡፡

ታዳጊው ስዩም በአካልና በአእምሮ ጎልብቶ በክለቦች የመጫወት አቅም ላይ ሲደርስም እመት አበቡ ከልጃቸው አልተለዩም፡፡ በ1975 ለመጀመሪያ ጊዜ ደሴን ተሰናብቶ ለመንግሥት ስራ ወደ መቱ ሲሄድ እናቱ ሰማይ የተደፋባቸው ያህል ያዘኑት ለዚህ ነው፡፡

‹‹ተሰናብቼ ስወጣ የሞትኩ ያህል ነው የተለቀሰው፡፡››

የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ከ39 ዓመት በፊት የሆነውን ያስታውሳል፡፡

‹‹አንዱ ልጄ፣ ሁሉ ነገሬ ተለየኝ›› እያሉ እናቱ ተንሰቀሰቁ፡፡

በሁኔታው የደነገጠው ጎረቤት ተሰብስቦ እማማ አበቡን አጽናናቸው፡፡፡

‹‹በዚህ ዓይነት ልጅዎ ራሱን ችሎ የሚጦረዎ መቼ ነው? አይዘኑ እንጂ…›› እያለ አግባባቸው፡፡

‹‹እንዲህ ስሜቷ መረበሹን ሳይ እኔም ስራውን ትቼ እዚያው ደሴ ልቀር ምንም አልቀረኝም ነበር፡፡ መቱ፣ ኢሉባቦር ከደረስኩ በኋላም በምናቤ የሚታየኝ የእናቴ ለቅሶ ብቻ ሆነ፡፡››

ስዩም በመቱ ስፖርት ኮሚሽን መስሪያ ቤት በብር 350 ተቀጠረ፡፡

‹‹በየወሩ የምግብ ወጪዬን የሚሸፍንልኝን 120 ብር አስቀርቼ የተቀረውን ለእናቴ እልክ ነበር›› ይላል፡፡

ጊዜ ጊዜን ተክቶ፣ ስዩም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ሆኖ ኑሮውን በአዲስ አበባ ካደረገ ጀምሮም ለእናቱ ስልክ ሳይደውል የሚውልበትን ቀን አያስታውስም፡፡

በ1994 በቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝነት በተሾመበት ወቅት እመት አበቡ ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ሊያደርጉ ጠቅልለው ሸገር ገቡ፡፡ በአካል ይበልጥ ቀርበውትም ቢሆን ስራው የተቃና እንዲሆን ጸሎታቸውን አጥብቀው ያዙ፡፡

‹‹ለስኬቴ ሁሉ የእናቴ ጸሎት እንደረዳኝ አምናለሁ፡፡ በጸሎት ታስበኛለች፡፡ በሚድያ በኩል የቡድኖቼን ውጤትም በቅርበት ትከታተላለች፡፡ አይዞህ ትለኛለች፡፡

‹‹ክትትሏ ሲበዛም ‹እንቺ መነኩሴ ነሽ፡፡ ቤተክርስቲያን መሳም እንጂ ስለእግር ኳስ ምን አገባሽ?› ይሏት ነበር›› የሚለው ስዩም የእናቱን ውለታ ዕድሜ ልኩን አይዘነጋም፡፡

እማሆይ አበቡ የምንኩስና ቆባቸውን ከደፉ በኋላ

አዲስ አበባ – ግንቦት 2011 

ቀፋፊው እሁድ

እሁድ ግንቦት 4 ቀን 2011 ስዩም ከአልጋው የተነሳው የቅዳሜ ምሽቱን የቤተሰብ ቀልድና ጨዋታ እንዲሁም በሰንበት ዕለት ስለሚታደምበት ሠርግ እያሰበ ነበር፡፡

የስጋ ዘመድ ሠርግ ስላለ ከቤቱ ሽክ ብሎ ወጣ፡፡ ባለቤቱም ከጎኑ አለች፡፡

የሚዜው ፈዛዛ… አስረሽ ምቺው በጦፈበት ሰዓት የእጅ ስልኩ ጠራ፡፡ ደዋዩ ወደ ቤት እንዲመጣ አጥብቆ ጠየቀው፡፡ እማሆይ አበቡ ትንፋሻቸው ያለወትሮ ቁርጥ ቁርጥ እያለ መሆኑ ተነገረው፡፡ ሰርጉን ትቶ ተቻኩሎ ወደ ሆስፒታል አመራ፡፡

በመንገዱ መኪናውን በትኩረት ማሽከርከር አልቻለም፡፡ ጅብ ጥላውን እንደጣለበት የዱር ተጓዥ አንዳች መጥፎ ስሜት ሰውነቱን ወሮታል፡፡ ነገሩ አላማረውም፡፡ ባለቤቱን አስከትሎ ሆስፒታል ሲደርስ ያልተለመደ የቤተዘመድ ግርግር ተመለከተ፡፡ የሰላም እንዳልሆነ ግልጽ ነበር፡፡

የዘመድ አዝማድ መኪኖች ተራ በተራ ወደ ሆስፒታሉ መድረሳቸው ጥሩ ነገር ጠቋሚ አልነበረም፡፡ ስዩም የህይወቱን ከባዱን እውነት የሚጋትባት አፍታ መድረሷን አወቀ፡፡

እማሆይ አርፈዋል፡፡

ዕድሜው በ50ዎቹ ግዛት የገባው አሰልጣኝ መርዶውን ሲሰማ ሱፍ ከረባቱን ትቶ፣ ሰዎች ምን ይሉኛልን ረስቶ በከባድ ሃዘን ጨርቁን ጣለ፡፡

‹‹ተንከባለልኩ፡፡ የምይዝ የምጨብጠውን አጣሁ፡፡ ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ ጣልኩት፡፡ ጮህኩኝ፡፡ ሰውነቴን ጎሰምኩ፡፡ ፈጽሞ የማልቋቋመው ጥልቅ ሃዘን ወቀደብኝ፡፡ ለራሴ ጥያቄ መልስ አጣሁለት፡፡ እንደ እብድ ተወራጨሁ፡፡ ትናንት ምሽት ስንጨዋወት አምሽተን አልነበር እንዴ? ጤናማዋን እናቴን ምን አገኘብኝ? አልኩ፡፡ የሚመልስልኝ አልነበረም፡፡››

ድሬዳዋ

ሚያዝያ 2013

ከቤተሰቡ ስድስት ልጆች አንዷ ደስታ ከበደ ‹‹መሬት ጠብ አይልም›› በሚባለው ህልሟ ትለያለች፡፡ የእማሆይ አበቡ የሙት ዓመት ወጥቶ፣ ሁለተኛ ሙት ዓመታቸው በተቃረበበት ጊዜ የስዩም ፋሲል ከነማ በፕሪምየር ሊጉ መሪነት ጸንቶ የክብሩን ዘመን እየናፈቀ ነበር፡፡

የሊጉ ውድድር በጦዘባት ድሬዳዋ ሳለ አሰልጣኙ ‹‹ህልሟ ቅዠት ሆኖ አያውቅም›› ከምትባለዋ ታናሽ እህቱ ዘንድ፣ ከወደ ደሴ ስልክ ተደወለለት፡፡

‹‹ወንድሜ አድምጠኝ፡፡ ዛሬ በጠለቀ የእንቅልፍ ዓለም ሳልሆን ህልም አልሜያለሁ፡፡ አብራርተሽ ንገሪኝ ካልከኝ ምላሽ ልሰጥህ አልችልም፡፡ አልተኛሁም፡፡ በቁሜ፣ አቅሌን ሳልስት ያየሁትን ልነግርህ ነው፡፡

‹‹እማዬ ላንተ መልዕክት አላት፡፡ እንደ ባዘቶ በነጣ ልብስ ከፊት ለፊቴ ተደቅና ነግራኛለች፡፡

‹…ለስዩም ንገሪልኝ፡፡ ኳሱ ዘንድሮ ተሳክቶልሃል፡፡ እንኳን ደስ ያለህ› በይው ብላኛለች፡፡››

አለችው፡፡

ነገሩ ለስዩም እንቆቅልሽ ነበር፡፡ ግን ከዚህ በላይ እንዳይጠይቅ ተነግሮታል፡፡ ነገሩ ለራሷ ለደስታ ግራ አጋቢ ነበር፡፡

‹‹መልዕክቱን ነግራኝ ስልኩ ከተዘጋ በኋላ በሐሳብ ጭልጥ ብዬ ወትሮም ከህሊናዬ በማትጠፋው እናቴ ትዝታ ተወሰድኩ›› ይላል፡፡

በአዲስ አበባ ሳለ በሳህሊተ ማሪያም ቤተክርቲያን በሳምንት አንድ ጊዜም ቢሆን መቃብራቸውን ይጎበኛል፡፡ ለሁለት ዓመት ገደማ ይህን ከማድረግ አልጎደለም ነበር፡፡

እመት አበቡ ከሁለቱ ልጆቻቸው ስዩም እና መላኩ ጋር

አዲስ አበባ ስታዲየም

2005

ድንገት ማጅራቱን አንዳች ነገር አጥብቆ ሲጨምቀው ስዩም ከበደ ተቻኩሎ ወደ ኋላው ዞረ፡፡ ለ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ዋልያዎቹ ከቤኒን ጋር ከመጫወታቸው አስቀድሞ ከአንድ የሃገር ውስጥ ቡድን ጋር አቋማቸውን ሊፈትሹ ተጫዋቾች በማሟሟቅ ላይ ነበሩ፡፡

‹‹ማነው የሚቀልድብኝ? ብዬ በቁጣ ጀርባዬን ተመለከትኩ፡፡ በሰው የተነካሁ ያህል፣ ማጅራቴ በእጅ እንደተያዘ ነበር የተሰማኝ፡፡››

ስዩም በግርምት ያስታውሳል፡፡

‹‹ነገር ግን ኋላዬን ብገላምጥ ማንም አልነበረም፡፡››

ገጠመኙ ከዚህ በፊት የማያውቀው እንግዳ ነበር፡፡ ከዚያች አፍታ ጀምሮ ማጅራቱን የጨመደደው ነገር ቀስፎ ይዞ አልለቅ አለው፡፡ ዕይታው ብዥታ አመጣ፡፡ በአንቴና ምክንያት እንደተንሸዋረረ ቴሌቪዥን በሜዳ ላይ የሚያሟሙቁት ተጫዋቾች ጥንድ ጥንድ ሆነው ታዩት፡፡ ያልተለመደ ስሜት በመከተሉ ጨዋታውን ትቶ ከቡድኑ ወጌሻ ጋር በስታዲየሙ አቅራቢያ ወደሚገኘው ሆስፒታል አመራ፡፡ ሲሄድ ስዩም አይታወቀው እንጂ ሚዛኑን መጠበቅ አቅቶት በአረማመዱ ይንገዳገድ ነበር፡፡

የሞት ሞቱን ቤተዛታ ሆስፒታል ደረሰ፡፡

ጠንከር ያለ ምርመራም ተደረገለት፡፡ ከህክምና መሳሪያ ኮምፒዩተሮች ጋር የተያያዙ በርካታ ገመዶች በተገለጠው ደረቱ ላይ ለጥፈውበት የህመሙን መንስኤ ለማወቅ ታተሩ፡፡

በስታዲየሙ ጨዋታው እየተካሄደ ነው፡፡ ረዳት አሰልጣኙ ግን ከስታዲየሙ ደጃፍ በአንድ አስፋልት ብቻ በሚለየው ሆስፒታል አልጋ ላይ ተዘርግቷል፡፡

ምርመራው አብቅቶ፣ ገመዱ ሁሉ ከተነቃቀለ በኋላ ከተኛበት ተነስቶ እንዲቀመጥ ታዘዘ፡፡ የዶክተሮቹን ምክር እንደሰማ ግን ሆዱ ይላወስ ጀመር፡፡

አጥወለወለው፡፡

‹‹በውስጤ ያለው ሁሉ ሲወጣ ጤንነት ተሰማኝ›› ይላል ስዩም – በተቀመጠበት ካስመለሰው በኋላ የሆነውን ሲያስታውስ፡፡

‹‹ተነስቼ ወደ ስታዲየሙ ያመራሁት ከዚህ በኋላ ነው፡፡ የድንገተኛው ጤናዬ ነገር ስላሳሰበኝ ወንድሜ መላኩ ከበደን ወደ ስታዲየም እንዲመጣ ስልክ ደውዬ ጠራሁት፡፡››

ጨዋታው ቀጥሏል፡፡

ዋናው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በትሪቡን ተቀምጠው ከፍ ባለ ዕይታ ቡድኑን ይገመግማሉ፡፡ ረዳታቸው ስዩም ወደ ተጠባባቂዎቹ መቀመጫ አምርቶ ከሜዳው ዳር ቆመ፡፡

ጨዋታው ሲጠናቀቅ የተጠራው መላኩ ከባለቤቱ ጋር ስታዲየም ደርሷል፡፡ ስዩም ያለ ድጋፍ ወደ ትሪቡኑ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ሲሄድ ደረጃውን የሚወጣበትና ችሎ የሚራመድበት ጉልበት አላጣም፡፡

መላኩና ባለቤቱ በመኪናቸው ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ አሰልጣኙም ከአሽከርካሪው ወንድሙ ጎን ተቀምጦ፣  የወንድሙ ባለቤትም ከበስተጀርባው ትከሻውን እየነካካችው፣ እየተጨዋወቱ ከስታዲየሙ ወጡ፡፡

‹‹ሰላማዊው ጉዟችን ግን ከጊቢው በር ብዙም አልራቀም›› ይላል ስዩም፡፡

‹‹መኪናው የውጭውን ደጃፍ እንዳለፈ ህመሜ ተመልሶ መጣ፡፡ አቅሌን ሳትኩ፡፡ ወንድሜና ባለቤቱ ተጣድፈው ያልሞተ በድኔን ይዘው ወደ ሆስፒታል ወሰዱኝ፡፡ በአዲስ ህይወት ሆስፒታል ከተኛሁ በኋላ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሳህሉ ገብረወልድ፣ ሰውነት ቢሻውና ሌሎችም ተመላልሰው ጠይቀውኛል፡፡ ግን አንዱም ስለመምጣቱ አላወቅኩት፡፡ ለድፍን ሰባት ቀናት ራሴን ስቼ ቆየሁ፡፡››

ሳይታወቅ ከባድ የደም ግፊት ጎልማሳውን አሰልጣኝ ከሞት አፋፍ ላይ አደረሰው፡፡ በአንጎሉ ላይ አነስተኛ የደም መርጋት ተገኘ፡፡ ደሙ በቶሎ ካልተጠረገ መላ ሰውነቱ የማይታዘዝበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል የሚል ከዶክተሮቹ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ስለተሰጠ የህብረት ባንክ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ፕሬዚዳንት የሆነው ወንድሙ መላኩ የውጭ ሃገር የህክምና ዕድል ለማግኘት አማራጮችን መፈለግ ጀመረ፡፡ ሆኖም በሆስፒታሉ ሌላ ስፔሻሊስት የተገመገመው የአሰልጣኙ ያለፈ የጤና ታሪክ፣ የረጋው ደም በሁለት ፍሬ ኪኒን ብቻ ሊድን እንደሚችል በመረጋገጡ የባህር ማዶው ህክምና አማራጭ ተረስቶ አንዷ ፍሬ በብር 2ሺህ የምትሸጠውን ኪኒን ለማግኘት ከተማው ታሰሰ፡፡

የስዩም ቤተሰብ መድኃኒቱን በሃገር ውስጥ ፋርማሲዎች ማግኘት ከባድ እንደሆነ ከዶክተሮቹ ተረድቷል፡፡ መላኩ ለንግድ ስራ ከዱባይ አዲስ አበባ ለሚመላለሰው ጓደኛው ችግራቸውን አማክሮ ኪኒኑን ማስመጣት እንዳለበት በመረዳቱ ወደ ጓደኛው ስልክ ደወለ፡፡

‹‹እባክህ፣ ወንድሜ በጠና ታሟል፡፡ ይህ ኪኒን እጅግ ያስፈልገናል፡፡ ሁለት ፍሬ ብቻ…›› የመላኩ ተማጽኖ ነበር፡፡

ስዩም ዕድለኛ ሆነ፡፡

ከመላኩ ጓደኛ የተገኘው ምላሽ ለማመን የሚቸግር ነበር።

‹‹እንዳጋጣሚ… ኪኒኑን ይዤ መጥቻለሁ፡፡ ሁለት ፍሬ እሰጥሃለሁ፡፡››

ከሚሊዮኖች አንድ ጊዜ ብቻ ሊሆን የሚችል ዕድለኝነት፡፡

ስዩም በሁለት ቀን ልዩነት ኪኒኖቹን ወስዶ ስጋቱ ተወገደለት፣ ጤናውም ቀስ በቀስ ተመለሰ፡፡

ከዚያ ጊዜ ወዲህ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ በሚያስጨንቀው ሙያ ሲቀጥል የደም ግፊት መቆጣጠሪያ መድኃኒቱን ዘንግቶ አያውቅም፡፡

ከዋንጫው ክብር አንድ ዓመት በፊት፣ የስዩም የጤና ፈተና – ኮቪድ

ሐምሌ 2012

አዲስ አበባ

ክረምቱ አስገምግሟል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ጥላ በሸገር ላይ ዱካኩን ጥሏል፡፡ ቡድኖች ለ2013 ውድድር የሚዘጋጁበት ወቅት ሲቃረብ ስዩም ጤንነት አልሰማህ አለው፡፡

‹‹የምግብ ሽታ አስጠላኝ፣ መገጣጠሚያዬ ይቆረጣጥመኛል፡፡ ሰውነቴ ምቾት አልሰጥህ ሲለኝ ለምርመራ ወደ ብሩክ ክሊኒክ አመራሁ›› ይላል አሰልጣኙ፡፡

የክሊኒኩ ባለሙያዎች ራጂ እንዲነሳ አዘዙ፡፡ የምርመራው ውጤት ሳምባው ውሃ መቋጠሩን አረጋገጠ፡፡ በኋላም በኮሮና ቫይረስ መያዙን አረዱት፡፡

የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ዋንጫ ይፈልጋሉ፡፡ የከተማው አስተዳደርም ቁርጠኛ ነው፡፡ ቡድኑ ጥሩ ስብስብ ቢኖረውም ስዩም ለአዲሱ የውድድር ዘመን የሚፈልጋቸውን ሌሎች ተጫዋቾች ለማስፈረም ወዲያ ወዲህ ማለት ነበረበት፡፡ ህመሙ ግን የሚያላውስ አልሆነም፡፡ ራሱን ለይቶ በሆስፒታል ለኮቪድ ህሙማን የሚደረገው ክትትል ተጀመረለት፡፡

ሌሎች ህመሞች ባሉባቸው ሰዎች ላይ ኮቪድ ሊጠና እንደሚችል ይታወቃል፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየም በጨዋታ ላይ ሳለ ማጅራቱን ጨምድዶ ሆስፒታል ያቆየው የደም ግፊት በዚህ ጊዜ ለክፉ እንዳይዳርገው ሰግቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ተከፍቷል፡፡ ፋሲል ግን ንቁ አልነበረም፡፡ አይደክሜው ሺመክት ጉግሳ ለወላይታ ድቻ ፈርሟል፡፡ ጎል አነፍናፊው ሙጂብ ቃሲም ሄዷል፡፡ የቡድኑ አንዳንድ ቋሚ ተሰላፊዎችም ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡ በቃል ተስማምተው ለፋሲል ያልፈረሙ ሌሎች ተጫዋቾችም ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከል የኢትዮጵያ ቡናው አማኑኤል እያሱ አንዱ ነው፡፡ የኋላው ማገር ያሬድ ባየን ቅዱስ ጊዮርጊሶች አነጋግረውታል የሚል ወሬም አለ፡፡

እስኪያገግሙ ድረስ ኮቪድ አግላይ በሽታ ነው፡፡ አሰልጣኙም ከአለቆቹ ጋር ተገናኝቶ ቡድኑን የሚያጠናክሩ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ስለማይችል ከጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ማስተዋል ስዩም ጋር በስልክ ብቻ ግንኙነቱን አጠናከረ፡፡ ሌሎቹ የቡድኑ ኃላፊዎችም በ2013 ዐፄዎቹ ብርቱ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ኃላፊነታቸውን በሚገባ ተወጡ፡፡

አምበል ያሬድ ባየ ከባለቤቱ ጋር እንዲሁም ስዩም፣ ባለቤቱ እና ልጁ

ግንቦት 2013

ሃዋሳ

ዋና አሰልጣኝ ስዩም ከበደ እና የቡድን መሪው ሃብታሙ ዘዋለ ፋሲል ሳይጫወት ሻምፒዮን መሆኑን የሚያረጋግጥበት ጨዋታ ላይ አፍጥጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሚከተለው ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ጣለ፡፡ ፋሲል ከነማ ቀሪ ጨዋታዎቹን ቢሸነፍ እንኳን ዐፄዎቹ የፕሪምየር ሊጉን ዘውድ ከመድፋት አያግዳቸውም፡፡ በወበቃማው የሃዋሳ ከሰዓት በኋላ የጨዋታው ማብቃት ፊሽካ ሲነፋ የስዩም ስሜት በደስታና ሃዘን ተሞላ፡፡

የስሜት መደበላለቁ በሃዋሳ አልተጀመረም፡፡ ፋሲል ከነማ ወደ ዋንጫው ግስጋሴውን ባጠናከረ ጊዜ ሁሉ ስዩም ሃሳቡ አንድ ነበር፡፡

‹‹ጅማ ላይ አራቱን ጨዋታዎች ሳንሸነፍ ስናጠናቅቅ፣ ባህር ዳር ላይ ከአምስቱ ጨዋታዎች አራቱን ስናሸንፍ፣ ወደ ሻምፒዮንነቱ ስንንደረደር፣ ሁሉም የድል ዋዜማ ዝማሬ እያሰማ ሲጨፍር እኔ ግን….››

ስዩም ይቀጥላል፡፡

‹‹እኔ ግን ወደ ሆቴል ክፍሌ ገብቼ አለቅሳለሁ፡፡ ሆድ ይብሰኛል፡፡ ‹ምነው እናቴ ይህችን ቀን አይታ በሞተች› የሚል ቁጭት ይረብሸኛል፡፡››

2013 ለፋሲል የድል ዘመን ሆነ፡፡ ውድድሩ ግን ቀላል አልነበረም፡፡ ስዩም ኃላፊነቱን ለመልቀቅ እስኪያስብ ድረስ የደጋፊዎች ተቃውሞ የበረታበት ፈታኝ ጊዜንም አሳልፏል፡፡ ተቃሙሞው አስተክዞታል፡፡ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊትም፣ በዝግጅት መጀመሪያ ወቅት በጤናውም ተፈትኗል፡፡ በታሪካዊቷ የነገሥታቱ መዲና ጎንደር ብቻ ሳይሆን በእግር ኳስ አሰልጣኝነቱ ባሳለፈባቸው የውጭና የሃገር ውስጥ ክለቦችና ብሔራዊ ቡድኖች ሁሉ የሚገጥመው ፈተና ጊዜያዊ እና አላፊ እንደሆኑ የተማረው ጎልምሶ የልጅ አባት ከሆነ በኋላ አይደለም፡፡ ነፍስ ሳያውቅ በድንገት በሞት የተለዩት አባቱ የተውለትን የውርስ ምክር እመት አበቡ ከሰጡት በኋላ እንጂ፡፡

‹‹ችግር ቢያጋጥምህ ትካዜን አታብዛ፣

ቀንና መከራ ያልፋል እንደዋዛ!››

አዎ! ያ ቀን አልፏል፡፡


ስለ ጸሀፊው


መንሱር አብዱልቀኒ (የእግር ኳስ ጋዜጠኛ)

በብስራት ኤፍኤም 101.1 የሚተላለፈው ዕለታዊዉ የብስራት ስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *