መጋቢት 19/2013 ዓ.ም – የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ክብርት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፡ በአትሌቲክስ ስፖርት ላስመዘገበችው ስኬት እና ከዛም ለተሻገረው መልካም አበርክቶዋ ዕውቅና ለመስጠት የተዘጋጀው ሀገራዊ የምስጋና መድረክ በስካይላይት ሆቴል ተካሄደ።

እኤአ የ1992 ባርሴሎና እና 2000 ሲድኒ ኦሊምፒክ የ10,000ሜ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዋ እና የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በርካታ እንግዶች በተገኙበት ፕሮግራም ላይ ልዩልዩ ሽልማቶች ተበርክቶላታል።

ከአሳዳጊ ክለቧ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን አንደኛ ደረጃ ኒሻን የተሸለመች ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ አያት አካባቢ የሚገኘውን ትልቁን አደባባይ በስሟ ተሰይሞ ለማልማት ቃል የገባ ሲሆን፡ በተጨማሪም የሁለት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት አበርክቶላታል።

ከዚህ በተጨማሪም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአንድ ቢሊየን ብር ወጪ በሱሉልታ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘውን የስፖርት አካዳሚ በስሟ የሰየመ ሲሆን በተጨማሪ የአምስት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት አበርክቶላታል።

የእውቅናና ምስጋና መርሀ ግብሩ አዘጋጆች በበኩላቸው ከልዩልዩ አካላት ባሰባሰቡት ገንዘብ የ350 ግራም የወርቅ ኒሻን እንዲሁም 2020 ሞዴል ሌክሰስ መኪና ሸልማት በኢትዮጵያ ህዝብ ስም አበርክተውላታል።

ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ለተደረገላት እውቅና፣ ሽልማትና አክብሮት ምስጋናዋን ገልፃ ለሀገር በቅንነትና በትጋት ማገልገል ዋጋ እንዳለውና አገራችንን በትጋት ማገልገል እንደሚገባ አሳስባለች።

የእለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ደራርቱ የኢትዮጵያ ተምሳሌት ስትሆን የተደረገላት እውቅናና ምስጋና መርሀ ግብር መደረጉ ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል።

በመጨረሻም ከአቅም በላይ በሆነ በስራ ምክንያት በመርሀ ግብር ላይ በአካል መገኘት ያልቻሉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በቪዲዮ ባስተላለፋት መልዕክት ደራርቱ ለሀገር ማድረግ የሚገባትን ሁሉ ያደረገች ጠንካራና የዓላማ ፅናት ምሳሌ መሆኗን ገልፀዋል።

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *