እነሆ የ2022 የፊፋ የአለም ዋንጫ በ92 አመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሰኔ እና ሀምሌ ወደ ህዳር እና ታህሳስ ወራት የውድድር ጊዜውን ቀይሮ እና በአረቡ ክፍለ አለም: በሚጢጢየዋ ኳታር አስተናጋጅነት ሊከናወን እነሆ በትክክል አራት አመታት ቀርተውታል፡፡

ኳታር እንደ ጎርጎሮሳውያን የዘመን ቀመር በ2010 ይህንን ግዙፍ አለምአቀፋዊ የስፖርት ድግስ የማስተናገድ እድሉን ብታገኝም፡ ከዚህ እድል መገኘት በሗላ እስከአሁን ድረስ ያልበረዱ እንደ ሳኡዲ መራሹ የአካባቢው ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፊፋ የአባል ሀገራት ቀጣዩን የአለም ዋንጫ ኳታር ከፊፋ ውል በመፈረም ለማስተናገድ ከተስማማችው የ32 ሀገራት ውድድር ወደ 48 ተሳታፊዎች ይደግልን ጥያቄ አይነት ጫናዎች ቢበረታባትም አሁንም ውድድሩን ለማስተናገድ በትክክለኛው ፍጥነት እና መንገድ ጉዞዋን መቀጠሏ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ከዚህ በመቀጠልም ከአንድ አመት ከስድስት ወር በፊት በዶሀ፡ ኳታር በመገኘት ይህንን የአለም ዋንጫ ለማስተናገድ እያደረጉ የሚገኘውን ሽር-ጉድ እና ኳታር በአጠቃላይ እንደ ሀገር ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠችውን ትልቅ ትኩረት ከተመለከትኩ በሗላ፡ በወቅቱ ለሀትሪክ የስፖርት ጋዜጣ የከተብኳትን ጽሁፍ ታነቡልኝ ዘንድ በትህትና እጋብዛለሁ፡፡

By Haileegziabher Adhanom – @haileadhanom

ልዩ ጥንቅር “ለሀትሪክ ስፖርት”

አለም አቀፉ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር (AIPS)
ከኳታር ስፖርት ኮሚቴ ጋር በመተባበር ከአፍሪካ፣ አውሮፓ፣ ኤዥያ እና አሜሪካ አህጉራት፤ ከ11 ሀገራት ለተውጣጡ 12 ወጣት የስፖርት ጋዜጠኞች በኳታር ዶሀ በስፖርት ጋዜጠኝነት እና አለምአቀፋዊ አሰራሩ ዙሪያ ከሚያዚያ 20 – 29/2009 ዓ.ም ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በዚህ ስልጠና ላይ ተካፋይ ከነበሩት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ እንደ መሆኔና በቆይታዬ በተፈጠረልኝ ልዩ የጉብኝት አጋጣሚ፤ ኳታር ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠችውን ልዩ ትኩረት እና ካላት ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም በመነጨ ሀገሪቱ ውስጥ እየተከናወኑ ካሉ በርካታ ግዙፍ የስፖርት ልማት ስራዎች አንዱና ዋነኛ የሆነውን የኳታር 2022 የአለም ዋንጫ ዝግጅትን በተመለከተ በተከታዩ ጽሁፌ በመጠኑ ላስቃኛችሁ ወድጃለሁ፤ ከሁሉ አስቀድሜ ግን የኳታር ስፖርት ኮሚቴ (QSC) አባላት በቆይታችን ላሳዩን መልካምና ልባዊ መስተንግዶ በእናንተ በአንባቢዎቼ ስም ከፍ ያለ ምስጋናዬን እንዳደርስ ይፈቀድልኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ፤ መልካም የንባብ ቆይታ፡፡

ኳታር 2022 የአለም ዋንጫ ዝግጅት

ታላላቆቹ አሜሪካንና አውስትራሊያን በማሸነፍ የ2022ቱን የፊፋ የአለም ዋንጫ አስተናጋጅነት ክብርን ካገኘች በኋላ በተለይም በምእራባውያን ሚዲያዎች ዘንድ የማስተናገድ እድሉን ያገኘችበት መንገድ ፍትሀዊ አይደለም ከሚል ጀምሮ፣ በሀገሪቱ ያለው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ለተወዳዳሪዎች ጤና አመች አይደለም እንዲሁም ስታዲየሞቹን እየገነቡ ያሉ የሶስተኛው አለም ዜጎች አያያዝና እንክብካቤ መሰረታዊ የሰው ልጅ መብትን ያላከበረነው የሚሉ ያልተቋረጡ ትችቶችን እያስተናገደች የምትገኘው ኳታር 22ኛውን የአለም ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከለኛው ምስራቅ ክልል ለማስተናገድ ገና የአምስት አመት ተኩል እድሜ ቢቀራትም ስታዲየሞቹ መጠናቀቅ ካለባቸው 2020 ዓ.ም አስቀድማ ለማድረስ በትክክለኛው መንገድ እየተጓዘች እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልጸውልናል፡፡

በምእራባውያን ሚዲያዎች ዘንድ ደጋግመን የሰማነውን የስታዲየም ግንባታ ሰራተኞች ኢ ሰብአዊ አያያዝን በተመለከተ በዚህ ጽሁፍ እንዳላጋራችሁ በቆይታችን ከነዚህ ሰራተኞች ጋር የመገናኘት እድል ፈጽሞ አላገኘንም፡፡

ነገር ግን አዘጋጆቹ ከዚህ ቀደም የእግር ኳስ አፍቃሪው ህብረተሰብ አይቶት የማያውቀውን የአለም ዋንጫ እናስመለክታችኋላን ጠብቁን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

ለመሆኑ የኳታሩ የአለም ዋንጫን ከዚህ ቀደም ከነበሩ አለም ዋንጫዎች ለየት የሚያደርጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

እነሆ ምላሾቹን፡-

ውድድሩ የሚካሄድባቸው ቦታዎች በቅርብ ርቀት መገኘት፡-

የ2022 ዓ.ም የአለም ዋንጫን ለማስተናገድ ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት ከሚገነቡት ስምንት ዘመናዊ ስታዲየሞች እና የቡድኖቹ ማረፊያ ካምፖች እንዲሁም የደጋፊዎች መሳባሰቢያ ዞኖች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በቅርብ ርቀት ውስጥ መገንባታቸው፣ ተጫዋቾቹ ከልምምድ ወደ ሆቴላቸው እና ወደ ጨዋታ ስቴዲየሞች የሚያደርጉት ረዥም ጉዞን ማስቀረት በመቻሉ ለአላስፈላጊ ድካም እንዳይጋለጡ ከማድረጉ በተጨማሪ ደጋፊዎች ከአንዱ ስታዲየም ወደ ሌላኛው ስታዲየም ለመጓዝ የሚወስድባቸው ከፍተኛው የጊዜ ርቀት 1፡00 ሰአት ብቻ በመሆኑ በአንድ ቀን በስቴዲየም ተገኝቶ ሁለት እና ከዛ በላይ የአለም ዋንጫ ጨዋታዎችን የመከታተል እድል የሚፈጥር መሆኑ፡፡

በስታዲየሞቹ ግንባታ ወቅት ቴክኖሎጂ ያለው ትልቅ ቦታ:-

ውድድሩን ካታር እንድታዘጋጅ ከተመረጠች ጀምሮ ከሚነሱ ወቀሳዎች አንዱ የቦታው ሞቃታማነት ነው፤ ሀገሪቷም ለዚህ ቅሬታ ሁለት ምላሾችን አዘጋጅታለች እነሱም፣ የመጀመሪያው ውድድሩ በተለመዶ ከሚዘጋጅበት ሰኔ እና ሀምሌ ወሮች በአካባቢው በአመዛኙ ቀዝቃዛ ወቅቶች ወደሆኑት ህዳር እና ታህሳስ ማዛወር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለተመልካቾች በየወንበሮቻቸው ስር የአየር ማቀዝቀዣ በመግጠም ለተጫዋቾች ደግሞ በስታዲየሙ ጣራ በኩል ቀዝቃዛ አየር እንዲገባ በማድረግ ለተጫዋቾች እና ለተመልካቾች ምቹ የአየር ሁኔታን መፍጠር ናቸው፤ ይህንን እኔም በአንዱ የሀገሪቱ ጨዋታ ላይ በአካል በመገኘት ለማረጋገጥ ችያለሁ፣ የስታዲየሙ የውጭውና የውስጡ የሙቀት ሁኔታም ፈጽሞ የተለያየ ነው፡፡

ሀገሪቱ በመሰረተ ልማት ረገድ ያላት ዝግጁነት፡-

– እጅግ ዘመናዊ የአየር መንገድ፣ ሰፋፊ የየብስ መንገዶች፣ አለም ዋንጫውን ታሳቢ አድርጎ እየተገነባ ያለ የከተማ ውስጥ የባቡር መስመር፣ በርካታ ባለ ኮከብ ሆቴሎችና የእንግዳ ማረፊያዎች ከባህላዊ የበረሀ ላይ የድንኳን ማረፊያዎች ጋር ኳታር 2022 የአለም ዋንጫን ብለው ለሚመጡ እንግዶች ሁሉንም መሰረተ ልማቶች ከወዲሁ ያሟላች ሀገር በመሆኗ፡፡

ኳታር ከአለም ዋንጫው በኋላ ትታው ለማለፍ ያሰበቸው አሻራ፡-

ይህንን የአለም ዋንጫ ለየት ከሚያደርጉት በርካታ ነገሮች አንዱና የብዙዎችን ትኩረት የሳበው ይህ ሀገሪቱ ከውድደሩ በኋላ ትታው ማለፍ ስለምትፈልገው አሻራ እየሰራች ያለችው ስራ ነው፡፡ ይህም ማለት ኳታር ለውድድሩ ከሚገነቡ ስታዲሞች በአመዛኙ ስታዲየሙ በሚገነባበት አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ከውድድሩ በኋላ ከስፖርቱ እንዳይርቁና በመሰረተ ልማቶቹ በዘላቂነት እንዲጠቀሙባቸው ለማድረግ እየሰራች ያለችው ስራ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከስታዲየሞቹ የተወሰኑት ክፍሎች እየተገነቡ ያሉት በተገጣጣሚና ተነቃቃይ የስታዲየም ጣራዎች፣ የመቀመጫ ወንበሮችና ኮንክሪቶች ሲሆን ይህም ከውድድሩ መካሄድ በኋላ ለታዳጊ ሀገሮች እነዚህን የስታዲየም ክፍሎች በእርዳታ መልክ ለመስጠት ስላቀደች በመሆኑ ነው፡፡

የአለም ዋንጫን  ኳታር ማዘጋጀቷ ለኢትዮጵያውያን ምን ጥቅም ይኖረዋል ፡-

ሀገራችን በውድድሩየመሳተፍ እድልን ብታገኝም ባታገኝም የኳታር የአለም ዋንጫ ከመቸውም ጊዜ በላይ ከሀገራችን በቅርብ ርቀት የሚከናወን የአለም ዋንጫ ይሆናል፡፡ በ2400 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘውን ኳታር በ4፡30 የአየር በረራ ብቻ በቀጥታ የውድድሩ ታዳሚ መሆን የምንችል ከመሆኑም በላይ በተመሳሳይ የሰአት አቆጣጠር ላይ መገኘታችን ደግሞ ጨዋታወቹን በየቤታችን በምቾት ለመከታተል የሚጠቅመን ይሆናል፡፡

ከላይ በመጠኑ የጠቃቀስኳቸውንና ሌሎች በርካታ አስገራሚ ነገሮችን የያዘው የ2022 የኳታር የአለም ዋንጫ እስካሁን ካየናቸው የአለም ዋንጫዎች የተለየውን የአለም ዋንጫ ሊያስመለክተን የአምስት አመታት እድሜ ብቻ ይቀረዋል፤ አዘጋጆቹ የተለየውን የአለም ዋንጫ ጠብቁ ብለውናል፣ እውነት ይህ የአለም ዋንጫ የምንጊዜም ምርጡ የአለም ዋንጫ ይሆን? የዛ ሰው ይበለን፡፡

ኳታር እና አጠቃላይ የስፖርት ውድድሮች መስተንግዶዋ:-

በመካከለኛው ምስራቅ የአለማችን ክፍል የምትገኘው ኳታር በ11,000KM² የቆዳ ስፋት እና 2.5 ሚሊየን የህዝብ ብዛት(ከነዚህም መካከል 300,000 ብቻ ናቸው የኳታር ዜግነት ያላቸው የተቀሩት ደግሞ ስደተኞች ናቸው) ሚጢጢ የምትባል ነገር ግን ባላት የተፈጥሮ ነዳጅ ሀብት ምርት በመጠቀም በአለማችን ቀዳሚዋ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ባለቤት ዜጎች ሀገርም ነች፡፡

ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከባህላዊው የግመል ውድድር አንስቶ የፈረስ፣ ቼዝ፣የሜዳ ቴኒስ፣የጎልፍ፣ አትሌቲክስ፣ የመኪና አሽቅድምድም እና ሌሎች በርካታ የስፖርት አይነቶችን ሳትለይ በቋሚነት በየሳምንቱ ቢያንስ አንድ አለም አቀፋዊ የስፖርት ውድድርን እያስተናገደች ትገኛለች፣ የ2019 የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የኳታር 2022 የአለም ዋንጫ አስተናጋጅም እንደሆነች ልብ ይበሉ፣ በዚህም ቀስ በቀስ የስፖርት ቱሪዝም ገቢዋን እያሳደገች እና በአለም አቀፉ መድረክም ከዋነኞቹ የስፖርቱ አለም ተዋናዮች አንዷ እየሆነች መምጣቷን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ኳታር ለምን ስፖርቱ ላይ ይህን ያክል አተኮረች?

የባርሴሎና ክለብ የማልያ ላይ ስፖንሰር ፣ የፓሪስ ሴንት ዤርሜይን ክለብ ባለቤቶች፣ የግዙፉ አለም አቀፍ የስፖርት ኔትዎርክ ቢ ኢን ስፖርትስ መገኛ፣ ዲያጎ ማራዶና፣ ራውል ጎንዛሌዝ፣ ዣቪ ሄርናንዴዝ፣ ሰይዱ ኬታና ሌሎችም የእግር ኳስ ኮከቦች የእግር ኳስ ዘመናቸው ማብቂያ የማሰልጠኛና መጫዎቻ ክለቦች መገኛ፣ የግዙፎቹ አስፓየር የስፖርት አካዳሚ እና አፒ ስታር የስፖርት ህክምና ማእከል እንዲሁም ሌሎች በርካታ አስገራሚ የስፖርት መሰረተ ልማቶች መገኛም ነች፣ ጥያቄው ግን ኳታር ስፖርቱ ላይ ይሄ ሁሉ ኢንቨስትመንት ለምን አስፈለጋት? ነው::

ለዚህ ጥያቄ ከተለያዩ አስተያየት ሰጭዎች እነዚህ ሶስት ምላሾች ተደጋግመው ይደመጣሉ፡

የመጀመሪያው ዜጎቿን ጤናማና ንቁ ለማድረግ እንደሆነና ወደ ስፖርቱ እንዲሳቡ፣የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያዘወትሩ ለማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው አላማ ደግሞ ኳታርን ለመላው አለም ማስተዋወቅ ነው፣ በሁሉም አቅጣጫ ትኩረት በሚሰጠው የስፖርት ዘርፍ በመሳተፍ፣ በማዘጋጀትና ስፖንሰር በማድረግ የኳታርን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ እሴቶችን ማስተዋወቅ ነው : ሶስተኛውና ዋነኛው የኳታር የስፖርት ኢንቨስትመንት ትልቅ ግብ ግን ይሄኛው ነው፡ እሱም ሀገሪቱ “ራዕይ 2030” ብላ በሰየመችውና ከተፈጥሮ ሀብት ጥገኝነት የተላቀቀ ዘላቂ ኢኮኖሚን ለመገንባት በምታደርገው ርብርቦሽ ስፖርት አንዱ የዘላቂ ገቢ ምንጭ እንዲሆን ትኩረት ስለተሰጠው ነው፡፡

በዚህም መሰረት ኳታር በዘላቂነት የተለያዩ የስፖርት
ውድድሮችን በማስተናገድና በተለያየ መንገድ በመሳተፍ የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል በመሆን ከነዳጅ በኋላ ባሉት ዓመታት ኢኮኖሚዋን እንዲደግፍላት ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች መሆኑ ነው፡፡

               ————– አበቃሁ —————

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *