በ ብሩክ አብሪና – ለልዩ ስፖርት

በሀገራችን እግር ኳስ እንዳለው ደጋፊ ብዛትና ዝና እንደዚሁም ታላቅነት በሊጉ ያለው ውጤታማነት እጅግ ከታሪኩ ጋር የተራራቀ ነው፤ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ። በክለቡ ታሪክ በሊጉ ወርቃማ ታሪክ ከፃፈው ከ2003 ስብስብ በኋላ ዳግም በሊጉ ማማ ላይ ለመቀመጥ ተቸግሯል። ክለቡ ወደ ሊጉ የበላይነት ለመመለስ መፍትሄ ብሎ ያመነባቸውን በርካታ ለውጦች ማድረግ ቢችልም 12 ቁጥር ለባሹ ደጋፊ የተራበውን የሊግ ዋንጫ ግን ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በመጡት አሰልጣኞች ማሳካት አልቻሉም። ይህም በየአመቱ በክለቡ እና በደጋፊዎች መሀል ሰፊ ክፍተቶችን ከመፍጠሩ ባለፈም ደጋፊዎች ግልፅ ተቃውሞ እስከማሰማት ደርሰዋል::

ከ2009 እስከ 2011 ያለውን ብቻ እንኳን ብንመለከት በ2010 በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ እየተመራ 3ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀበት ውጤት ከቅርብ ዓመታት ውጤቶቹ በትልቅ ደረጃ የሚነሳለት ነው:: በቀጣዩ ዓመት ካቆመበት ይቀጥላል ብለው ደጋፊዎች ቢጠብቁም 9ኛ በመሆን ጨርሷል:: የውጤት ማሽቆልቆሉ በፈጠረው ጫና በደጋፊዎቹ ይፈለግ የነበረው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋችና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከአሜሪካ ጥሪ ተደርጎለት የአሰልጣኝነት መንበሩን መረከቡ የሚታወስ ነው።

በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ሳይጠናቀቅ በተሰረዘው ባለፈው የውድድር ዓመት አሰልጣኝ ካሳዬ በ1990ዎቹ ቡድኑን በሰራበት የጂኬ ፍልስፍና እየተመራ ሊጉ ሲቋረጥ ከ17 ጨዋታዎች 22 ነጥብ ሰብስቦ 8ኛ ደረጃ ላይ ነበር። የቡድኑ ጥንካሬ ቡናማዎቹ በተሰረዘው የውድድር አመት ትልቁ ጥንካሬያቸው ያመኑበትን የጨዋታ መንገድ በከባድ ጫና ውስጥም ሆነው ለመተግበር ወደ ሗላ አለማለታቸው ነው::

በእርግጥ በአንዳንድ አጋጣሚዎች እንደ አስፈላጊነቱ የሚቀያየር የአጨዋወት መንገድ ሲከተል ቢታይም በአብዛኛው ግን ቡድኑ የሁሉንም ሜዳ ላይ ያሉ ተጫዋቾቹን የኳስ ንክኪ በሚፈልግ መልኩ ለመጫወት ሲሞክር ታይቷል:: ይህም በሊጉ በተለየ የሚታይ እና አላማው ግልፅ የሆነ የጨዋታ ሀሳብን ለመተግበር ጥረት ላይ እንዳለ ያመላከተ ነበር::

ሌላው ክለቡ ሙሉ ትኩረቱን በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ላይ ብቻ በማድረግ ከዚህ ቀደም በብዙ ወጪ አውጥቶባቸው ነገር ግን በተፈለገው ደረጃ ያልተጠቀመባቸውን የውጭ ሀገር ተጫዋቾች በማሰናበት የነሱን ቦታ በታዳጊዎች ለመሸፈን መሞከሩና ከከፍተኛ ሊግ ሳይቀር ተጫዋቾችን በቡድኑ ውስጥ ማካተቱ በቀጣይም በወጣቶች ላይ ተስፉ ሰጪ ሀሳቦችን ይዞ የመጣ እንደሆነ ያሳያል።

በተጨማሪም የወጣት ተጫዋቾቹ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ዕድገት አንዱ ጥንካሬው የነበረ ሲሆን በተለይም ወደ ቡድኑ ከመጡ ጀምሮ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው የአጥቂው አቡበከር ናስሩ እየበሰለ መምጣት እና የመስመር አጥቂው ሚኪያስ መኮንን ከጉዳት በኋላ ዳግም ወደ ምርጥ ብቃቱ መመለሱ የሚነሳ ሲሆን ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ የሀብታሙ ታደሰ ጎልቶ ቢነሳም በአሰልጣኙ የጨዋታ ምርጫ ተቀዳሚ የሆኑት ታፈሰ ሰለሞን እና ፍቅረየሱስም ቶሎ ከቡድኑ ጋር መግባባታቸው እንደዚሁም የአቤል ከበደ የተረጋጋ አጨዋወት በቡናማው ቤት የተመለከትነው መልካም ጎን ነበር።

በዚህ መንገድ ለግብ ጠባቂዎችም ቡድኑ የሰጠው ነፃነት እና ብዙም በሊጋችን ባልተለመደ መልኩ እያፈራረቀ መጠቀም ከዚህ ቀደም የሚነሳውን የጨዋታ ዕድሎችን የማግኘት ጥያቄን በተወሰነ መልኩ ለመቅረፍም በር የከፈተ ነው።

ደካማ ጎን

በቡናማዎቹ ቤት በትልቅ ደረጃ የሚነሳው ችግር ጫናን የመቋቋም ሲሆን ይህም ተጫዋቾቹ ቡድኑ እየሞከረ ያለውን የጨዋታ መንገድ ቶሎ ለመላመድ ሲቸገሩ እና በሚሰሯቸው ስህተቶች ላይ የመቆዘም ወይም ቶሎ ከስህተት ለመውጣት መቸገር ነው:: በተጨማሪም የሚገኙ አጋጣሚዎችንም ወደ ጎልነት ለመቀየር ሲቸገር ተስተውሏል።

ለምሳሌ እንኳ በሸገር ደርቢ ካደረጋቸው ከ5 ያላነሱ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ምንም ግብ ሳያስቆጥር ወጥቷል። ቡድኑ ምንም እንኳ በሽግግር ላይ ቢሆንም በሊጉ ተፎካካሪነቱን አስጠብቆ ለመቀጠል እና የደጋፊውን የአሸናፊነት ጥያቄን ለመመለስ አላማ ባለው መንገድ የሚገኙትን ዕድሎች መጠቀም ይኖርበታል።

Abubeker Nasir

 

ቡናማዎቹ ከዚህም ባለፈ በወጥነት የቋሚ ተሰላፊዎች አለመለየት በየጨዋታው የሚታዩ የውህደት ችግሮችም ይነሱበታል።

ለአንድ ቡድን ሁሉም እኩል ድርሻ ቢኖራቸውም ወጥነት ያለው እና ውጤታማነትን ይዘው መጓዝ የሚችሉ ቋሚ ተሰላፊዎች ደግሞ ሊለዩ እንደሚገባ ይታመናል::

ማን ይደምቅ ይሆን?

ከኮቪድ መከሰት በሗላ የተጫዋቾች አቅምና የወጥነት ችግር ሊስተዋል እንደሚችል ቢጠበቅም ነገር ግን ባለፉት አመታት ካሳዩት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና ዕድገታቸውን ሊያስቀጥሉ ይችላሉ ብዬ የምጠብቃቸው ተጫዋቾች ያሉ ሲሆን ከቡናማዎቹ በኩል በዚህ ረገድ ስሙ ቀድሞ የሚጠቀሰው ሙሉ ለሙሉ ከጉዳት ነፃ ሆኖ ከተጫወተ በሜዳላይ ያለውን ለመስጠት የማይሰስተው ተጫዋች አቡበከር ናስር ነው::

ተጫዋቹ ከአመት አመት ዕድገት እና ብስለቱ እየዳበረ ከመምጣቱም ባለፈ ሀላፊነቶችን በመቀበል እና በመውሰድም ጭምር እራሱን በወጣትነቱ ለትልቅ ሀላፊነቶች እያበቃ መሆኑን በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታቸው ከወልቂጤ ከተማ ጋር ሁለት ለ ሁለት ሲለያዩ ሁለቱንም ጎሎች በማስቆጠር አስመስክሯል::በብሄራዊ ቡድኑም ያሳየው እንቅስቃሴ በሊጉ ላይ ቡናማዎቹን በሚገባ ለማገልገል የሚያስቸለው እንደሚሆን መገመት አያዳግትም።

በመጨረሻም ቡናማዎቹ ለአሰልጣኙ የሰጡት ግዜ እና ነፃነት ረዥም ግዜን ታሳቢ ያደረገ ውጤታማነትን ለማምጣት ክለቡ እንደተዘጋጀ የሚያሳይ ሲሆን ትልቁ ጥያቄ ግን ደጋፊዎች ሽግግር ላይ ያለውን ቡድናቸውን ምን ያህል ይታገሳሉ የሚለው ነው::

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *