አበበ ዲንቂሳ፣ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ገዛኸኝ አበራ

ውድድሩ ለኮቪድ 19 ቅድመ ጥንቃቄ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተዘጋጅቷል

ታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም፡ የ20ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጥር 2 ቀን ይካሄዳል፡፡ የውድድሩ ምዝገባ ከታህሳስ 2 ቀን ጀምሮ ተሳታፊዎች በያሉበት አሞሌን በመጠቀም እንዲያካሂዱ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ 200 ተሳታፊ ተመዝጋቢዎች ለውድድሩ መዘጋጃ የሚሆን የመለማመጃ ቲ-ሸርት በነጻ እንደሚሰጣቸውም ታውቋል፡፡

20ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በዘንድሮ ውድድሩ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ 12500 ተሳታፊዎች ብቻ ይኖሩታል፡፡ በተጨማሪም የአለም አቀፍ ተሳታፊዎችን ለማካተት ውድድሩ በሚካሄድበት ተመሳሳይ ቀን በቨርቹዋል ውድድር በያሉበት ተሳታፊ እንዲሆኑና የ20ኛውን አመት ክብረ በዓል አብረው እንዲያከብሩ ቅድመ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ መሰረት ከቀድሞ ተሳታፊ 25 በመቶ ብቻ አሳታፊ የሚደርገው ታላቁ ሩጫ የሚከተሉትን የሚከተሉትን የኮቪድ-19 ቅድመ ጥንቃቄዎች ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

ውድድሩ የሚጀመረው በሶስት የተለያዩ ማዕበሎች(አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ) ይሆናል፡፡ ሶስቱ ማዕበሎች ወደ መስቀል አደባባይ የሚመጡበት አቅጣጫ በየተ–ሸርት ቀለሙ ተለያይቶ የተሰየመ ነው፡፡ እያንዳንዱ ማዕበልም ማህበራዊ ርቀትን ለማስጠበቅ ሲባል በ 3 እና በ4 ቡድን ይከፈላል፡፡ ሩጫው በሶስት የተለያዩ መነሻ ሰዓታ የሚደረግ ሲሆን ተሳታፊዎች የሚጀምሩበትን ሰዓት እና አብረው የሚሮጡትን ቡድን ለመለየት ከሩጫ ቲ-ሸርታቸው ጋር አብረው የሚወስዱት የደረት የመሮጫ ፊደል ጠቋሚ ይሆናል፡፡

እያንዳንዱ ተሳታፊ ከሚመርጠው የቲ-ሸርት ቀለም ባሻገር የመወዳደሪያ የደረት ቁጥር በፊደል የሚወስዱ ይሆናል፡፡ ተሳታፊዎች የመሮጫ ቲ-ሸርታቸውን ሲወስዱ አብሮ የሚሰጣቸውን የአፍና አፍንጫ ጭንብል የውድድሩ መነሻ፤ የመሰበሰቢያ ቦታና ውድድሩን ከጨረሱ በኋላ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ተሳታፊዎች መወዳደሪያ ቦታው ላይ እንደደረሱ እያንዳንዱ ተሳታፊ የሰውነት ሙቀት ልኬት ይደረግለታል፡፡እንዲሁም በውድድ መነሻና መድረሻ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር ይቀርባል፡፡

ወፎችን ታሳቢ ያደረገ የሀይል መሰረተ ልማት የ2013 የሩጫ መልዕክት ሲሆን በርድ ላይፍ አፍሪካ- የነጩ ጆፌ አሞራ ፕሮጀክት የዚህ መልዕክት አስተላላፊና አጋር ድርጅት ነው፡፡

የዚህን አመት ታላቁ ሩጫ ለየት የሚያደርገው የውድድሩ መነሻ መስቀል አደባባይ ሆኖ መድረሻው አትላስ አከባቢ መሆኑ ነው፡፡ ተሳታፊዎች ውድድሩ ሊካሄድ 10ቀናት ሲቀሩት የመወዳደሪያ ቲ-ሸርት ፤ የመሮጫ የደረት ቁጥር ፊደል እና ጭምብል ምዝገባ ሲያደርጉ በመረጡዋቸው የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች በመሄድ መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡

የዘንድሮ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አጋር ድርጅቶች ቶታል እንደወትሮ የስያሜ ስፖንሰር ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ማልታ-የብርታት መጠጥ፤ አሞሌ- የዚህ ዘመት የመመዝገቢያ መንገድ፤ በርድ ላይፍ አፍሪካ-የነጩ ጆፌ አሞራ ፕሮጀክት- የሩጫው የመልዕክት ስፖንሰር፤ ቱሪዝም ኢትዮጵያ፤ ኢንዶሚ፤ ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል፤ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት- የሚዲያ አጋር፤ አርኪ ውሃ እና ሳስ ፋርማሲስ ናቸው፡፡

የ2013 ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመመዝገቢያ ዋጋ 450ብር ሲሆን ለመመዝገብ በቴሌግራም @greatethrun መጠቀም የሚቻል መሆኑ ተገልጧል፡፡

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *