በ ብሩክ አብሪና – ለልዩ ስፖርት

የ2013ዓ.ም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የፊታችን ቅዳሜ ሲጀምር፡ ከበርካታ አዳዲስ ነገሮች ጋር መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ ጨዋታዎች በሱፐር ስፖርት በቀጥታ የሚሰራጩ ሲሆን አለማችንን ያስጨነቀው የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ሊጋችንን ለመጀመሪያ ጊዜ የምንመለከትበትም ሆናል፡፡

ከዚህ ቀጥሎ በማስነብባችሁ ጽሁፍ በእኔ እምነት በአዲሱ የውድድር ዘመን ከእነማን፣ ምን ልንመለከት እንደምንችል የዳሰስኩበትን የቅድመ ውድድር ምልከታዬን አካፍላችኋለሁ፡ መልካም ንባብ፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ የሶስት አመታት ዋንጫ አልባ ጉዞ…

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በተደጋጋሚ ሻምፒዮን በመሆን የሚሰተካከለው የለም፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብን፡፡  ነገር ግን ከ2009 ዓ.ም በኃላ የሊጉን ዋንጫ ማሳካት አልቻለም፡፡ የሊጉ የዋንጫ  ተፎካካሪ ክለቦች መብዛት አንዱ ምክንያት ቢሆንም ክለቡም በ3አመታት ውስጥ ያሳየው ወጥነት የጎደለው  የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የመጀመሪያውን ደረጃ ይወስዳል ቢባል ብዙም አይጎረብጥም።

ፈረሰኞቹ በቫስ ፒንቶ፣ በስቱሀርት ሀል እና በሰርጂዮ በተመሩበት ወቅት በጣም የተለያየ አጨዋወትን ያስመለከቱን ሲሆን፡ ያስመዘገቡት ውጤትም የተለያየ ነበር፡፡ ቡድኑ በ2009ዓ.ም አራት ጨዋታዎችን ብቻ ሲሸነፍ፡ በተከታዩ አመትም  በፒንቶ እየተመራ ሶስት ጨዋታ ብቻ ቢሸነፍም በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ነጥብ ተጋርቶ በመውጣቱ ምክንያትም የሊጉን ዋንጫ አጥቷል፡፡  በ2011ዓ.ም ደግሞ ሰባት ጨዋታዎችን የተሸነፈ ሲሆን በውድድር አመቱ  ከሊጉ ከወረዱት መከላከያ እና ደቡብ ፖሊስ እንኳን ያነሰ ግብ ብቻ ነው ያስቆጠረው። ይህም የስቱዋርት ሀልን መጨረሻ አፋጥኖታል፡፡

ፈረሰኞቹ ባለፉት አመታት ወደ ለመዱት የአሸናፊነት መንገድ ለመመለስ፡ የተለያዩ አሰልጣኞችን ከመሞከር በተጨማሪ በየአመቱ ጥሩ የሚባሉ ተጫዋቾችንም ጭምር ማሰፈርም ቢችሉም፡ የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርገው ለመሳም ግን አልበቁም። ሁኔታው ደጋፊውንም ሆነ አመራሩን ያስደሰተ ካለመሆኑ በተጨማሪም ተጫዋቾቹንም በከፍተኛ ጫና ውስጥ የከተተ ነበር።

ፈረሰኞቹ  ዘንድሮስ ወደ ዋንጫ?

ክለቡ በያዝነው የክረምት የዝውውር መስኮት ጥቂት ተጫዋቾችን ማለትም አዲሰ ግደይን እና ከነአን ማርከነህን ቀደም ብሎ በቅርቡ ደግሞ የመቀሌውን አማኑኤል ገብረሚካኤልን ብቻ በማስፈርም ይልቁንም የነባር ተጫዋቾቹን ውል በማራዘም ቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረ ሲሆን፡ በአፍሪካ  ልምድ አላቸው ብሎም ክለቡንም ከሀገር ውስጥ ባለፈ በአፍሪካ መድረክ ተፎካካሪ ያደርጉልኛል ብሎ ከአስመጣቸው ከጀርመናዊው አርነስት ሚዴንዶርፕ ጋር በግዜ መለያየቱም ከወዲው የፈረሰኞቹን የአመቱ ጅማሬ በጥያቄ እና በጥርጣሬ እንዲታይ አድርጎታል።

ሊጉ የሚጀመርበት ቀን ከመቃረቡ ጋር ተያይዞ፡ ቡድኑ ያለ ቋሚ ዋና አሰልጣኝ የውድድር አመቱን ይጀምራል ወይ የሚለውም ትኩረትን ስቧል።

የቡድኑ የአምና ጥንካሬ

ፈረሰኞቹ በተሰረዘው የአምናው የሊግ ውድድር ላይ ትልቁ ጥንካሬአቸው በርካታ ተዳክመው የነበሩ  እና ወደ መረሳት ደረጃ ደርሰው የነበሩ ተጫዋቾች ወደ ጥሩ አቋማቸው የተመለሱበት አመት ነበር፡፡ ለምሳሌ፡ ከጉዳት ጋር ሲታገሉ የነበሩት ሳላዲን ሰይድ፣ ጌታነህ ከበደ እንዲሁም ወደ ክለቡ ከመጡ ጀምሮ የተጠበቀውን ያህል መሆን ያልቻሉት አብዱልከሪም መሀመድ፣ ሄኖክ አዱኛ እና በተለይም ጋዲሳ መብራቴ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች  መሆን የቻሉበት ነበር፡፡

ሌላው በአስቻለው እና በፍሪምፖንግ የሚመራው የተከላካይ ክፍል ዋናው የቡድኑ የጥንካሬ ምንጭ ነበር። ቡድኑ ሊጉ አስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በ17 ጨዋታዎች ያስተናገደው 13 ግቦች ብቻ ነበር። በዚህ ረገድ የሚስተካከለው የሊጉ መሪ የነበረው ፋሲል ከነማ ብቻ ነው።

የቡድኑ ደካማ ጎን

ፈረሰኞቹ በውድድር አመቱ ትንሽ ግብ ያሰተናግዱ  እንጂ በ17 ጨዋታዎች ያስቆጠሩት 22  ግብ ብቻ ነው፡ ይህም በአማካይ በጨዋታ 1.2 ጎል ማለት ነው፡፡ አንድ ማሳያ ለመጨመር ካስፈለገ፡ ቡድኑ በአንድ ጨዋታ ከሶስት ግቦች በላይ ማስቆጠር የቻለው በሶስት ጨዋታዎች ብቻ  መሆኑን መጥቀስ በቂ ነው።

ከዚህም ባለፈ ቡድኑ የወጥነት ችግርም የሚታይበት የነበረ ሲሆን፡ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው ሁለት ነጥብ ብቻ ሲሆን፡ በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጭ ተደጋጋሚ ነጥቦችን መጣልም ታይቶበታል።  ከዚህ በተጨማሪም ተደራራቢ የተጫዋቾች ጉዳት፣  ለምሰሌ፡  የአቤል ያለው፣ አቤል እንዳለ፣ ሳላዲን ሰይድ  እና ናትናኤል ዘለቀ ጉዳቶች፣ እንዲሁም ቡድኑ በውድድር አመቱ ይህ ነው የሚባል የተረጋጋ የጨዋታ አቀራርብም ሆነ የአጨዋዎት ዘይቤን አለመከተሉ በቡድኑ ውጤታማነት ላይ፣ በተጫዋቾቹ መግባባት ላይ  የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ መገመት ይቻላል፡፡

አማኑኤል ገብረሚካኤል

አዳዲስ ፈራሚዎቹ ምን ይጨምሩለታል?

ፈረሰኞቹ በክረምቱ  አዲስ ግደይን፣ ከነአን ማርክነህን እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን ያስፈረሙ ሲሆን አዲስ ግደይ በሊጉ ለተከታታይ አመታት በወጥነት በግብ አስቆጣሪነቱ የቀጠለ እና በሲዳማ የዋንጫ ተፎካካሪነት ጉዞ ትልቅ ድርሻ የሚወስድ ተጫዋች ነበር። ይህም የማይነጥፍ ወጥነት ያለው ብቃቱን በፈረሰኞቹ ቤት መድገም ከቻለ ከጌታነህ ሳላዲን እና አቤል ጋር ከሚኖረው ጥምረት ባለፈ በክለቡ ውስጥ እራሱ የሚኖረውን የመሰለፍ ፉክክርም ከፍ ያደርገዋል። ነገር ግን አዲስ ቡድኑ ውስጥ በሚኖረው ጠባብ የመሰለፍ ዕድል ላይ ተመራጭ ለመሆን የሁለገብነትን ባህሪ ማከል ይጠበቅበታል።

ይህም አዲስ በሲዳማም ሆነ በብሄራዊ ቡድንም ሲያስወቅሰው ከነበሩ ነገሮች አንዱ ቡድኑን በመከላከል ወቅት ማገዝ ላይ ደካማ መሆኑ ሲሆን ይህን ማስተካከል ከቻለ በፈረሰኞቹ ቤት ደምቆ ለመውጣት ላይቸገር ይችላል።

ሌላኛው ፈራሚ ከነአን ደግሞ የቡድኑን የአማካይ ክፍል የፈጠራ አቅም ከፍ ከማድረጉ ባለፈ፡ በተለያዩ ቦታዎች መጫወት መቻሉ ሌላው ጠንካራ ጎኑ ሲሆን ያብስራ ተስፋዬ ጉዳት ላይ ከመሆኑ የተነሳ አምና በእርሱ  ሲሸፈን የነበረውን ነፃ ወይም የፈጠራ ቦታን ሊሸፍን እንደሚችል ይታመናል። ከነአን ሌላው ጥንካሬው ግብ አስቆጣሪነቱ ሲሆን ያለቀላቸው ለግብ የሚሆኑ ኳሶችንሞ አመቻችቶ በማቀበል የሚታማ አለመሆኑ የፈረሰኞቹ ጉዞ ላይ የራሱን አስተዋፅኦ ማከል የሚችልበት አቅም አለው።

አማኑኤል ገብረሚካኤል በቀድሞ ክለቡ መቀሌ ሰባ እንደርታም ሆነ በብሄራዊ ቡድኑ ላይ የነበረው ያለፉት አመታት ወጥ አቋሙ የክለቡን የጎል ምንጭ አማራጮች በማስፋት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል፡፡

ማን ይደምቅ  ይሆን?

ከኮቪድ መከሰት በኋላ የተጫዋቾች አካላዊ አቅም እና የወጥ አቋም ችግር ሊስተዋል እንደሚችል ቢጠበቅም፡ ነገር ግን ባለፉት አመታት ካሳዩት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በመነሳት ዕድገታቸውን ሊያስቀጥሉ  ይችላሉ ብዬ የምጠብቃቸው ተጫዋቾችም አሉ፡፡

ከቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም ባለፉት ሁለት አመታት ባዳረጋቸው  የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ፡ በአሰልጣኞቹም የመጀመሪያ ተመራጭ ከመሆኑ ባለፈ እና በተሰለፈባቸው ጨዋታዎቹ  ያለውን ሳይሰስት በመስጠት የቡድኑ ወሳኝ ግብ አስቆጣሪ እንደዚሁም የግብ ዕድሎችን ለቡድን አጋሮቹ በመፍጠር ጭምር  በአጭር ግዜ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች እና ደጋፊውም በስሙ መዘመር የቻሉለት የመስመር አጥቂው አቤል ያለው ዘንድሮ በሊጉ ሊያንፀባርቁ ከሚችሉ ተጫዋች መሀል ዋነኛው ተጠቃሽ ነው።

በመጨረሻም ፈረሰኞቹ ያላቻው የቡድን ስብስ፡ ዘንድሮም ለሊጉ ዋንጫ በተፎካካሪነት ከሚጠበቁ ቡድኖች ቀዳሚዎቹ የሚያደርጋቸው ሲሆን፡ ቡድኑን በሀላፊነት የሚረከበው ባለሞያም ከክለቡ የሚሰጠው የመጀመሪያ ግዴታ  የሊጉን ዋንጫ ማሳካት እንደሚሆን ይጠበቃል።

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *