በ ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል – ለልዩ ስፖርት

እግር ኳስ በሚሊዮኞች ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ያለ የሀገራችን ተወዳጅ ስፖርት ነው፡፡ የቅርብ ጊዜያት አጋጣሚዎችን ትተን በጊዜያት መለዋወጥ፣ በተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች መገንባት እና መፍረስ፣ በደካማ ውጤቶች መካከል ሳይቀየር የተጓዘ ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች ጽናትና ታማኝነት ብቻ ይመስለኛል፡፡ ይሄንን ሚሊዮኖች በገንዘብና በጊዜ ዋጋ የሚከፍሉለትን፣ መንግስት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይን የሚያፈስለትን ስፖርት በየጊዜው የሚመራው የእግር ኳስ አካል በተቀያየረበት አጋጣሚ ሁሉ የተሻለ ሥህተት መስራቱን፣ የበለጠ ከፍ ብሎ የመውድቅ ውድድሩን አጠናክሮታል፡፡ ኢትዮጵያ ስህተት የሚሰራ የእግር ኳስ አመራር ብቻ አይደለም ችግሯ፡፡ በሁሉ ነገሮቹ ከስህተቶች የተሰራ ለመታረም፣ ለመስማት፣ ካለፈው ውድቀት ለማገገም ያልተዘጋጀን የእግር ኳስ አመራር ምን ማድረግ ይቻላል?

በቅርቡ በኮቪድ ምክንያት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ስራ አስፈጻሚ የሁሉንም ብሔራዊ ቡድኖች የአሰልጣኞች ቅጥር ውል እንደሚያቋርጥ ይፋ አደረገ፡፡ በወቅቱ የቀረቡ ምክንያቶች እግር ኳስ በአህጉር ደረጃ እና በኢትዮጵያ መቼ እንደሚጀምር ስለማይታወቅ ነው የሚል ምላሽ ሰጠ፡፡ በጊዜው ባለሙያዎች ይሄ ነገር ስህተት ነው ብለው ተቃውሞ አሰሙ፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች እግር ኳስ ኮቪድን ተቋቁሞ እየተጀመረ ነበርና በሀገራችንም፣ በአፍሪካም ውድድር መጀመሩ አይቀርም፡፡ እንደገና ብሔራዊ ቡድን ከመመስረት ኮንትራቱን ማደስ ይሻላል በሚል ብዙዎች ምክር ሰጡ፡፡ “ማንም እጄን ጠምዝዞ ኮንትራት አያስፈርመኝም” ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በውሳኔው ጸና፡፡ ይሄ ውሳኔ ተወስኖ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዘ ዉስጥ በአፍሪካ ፤ በኢትዮጵያ እግር ኩዋስ የሚጀምርበት እድል ተፈጠረ፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እንደውም ማጣሪዎች የሚካሄዱባቸውን መርሃ ግብሮች የፌዴሬሽኑ ግብታዊ ውሳኔ ተላልፎ ሳይረሳ ወዲያውኑ ይፋ አደረገ፡፡ የብዙ ባለሙያዎች ምክር ሳይሆን ስህተት ብርቁ ያልሆነው ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ ተግባራዊ ሆኖ የቡድኖቹ ዝግጅት በአሰልጣኘ አለመኖር ምክንያት ከነበረባት ሳይቀጥል ቀረ፡፡

የውድድሮቹ ጊዜ በፍጥነት መድረሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ የማይቀረውን የአሰልጣኞች ምደባ የሚያደርግበት ጊዜ ደረሰ፡፡ እዚህ ላይ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ብዙ ነገሮችን ከግምት በማስገባት የፌዴሬሽኑ አመራር የሰራውን ስህተት በሌላ ስህተት አያርምም ከመጀመሪያው ስህተትም የተሻለ ስህተት በመፍጠር በስፖርት ቤተሰቡ ላይ ሌላ ችግር አይፈጥርም ብለው ግምታቸውን አስቀመጡ፡፡

ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው – የብሄራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ

ሙያውን ከሙያተኞች በላይ አውቀዋለሁ ያለው ውሳኔ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባህር ዳር ላይ የኮትዲቫርን ብሔራዊ ቡድን በጨዋታ ብልጫ ጭምር አሸንፎ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያን የማለፍ ተስፋውን አለምልሟል፡፡ ጠፍቶ የነበረው የእግር ኳስ ተመልካች በደስታ የብሔራዊ ቡድኑን ጨዋታ መከታተል ጀምሯል፡፡ በአንድ ወቅት ወደብሔራዊ ቡድን አትጥሩን እስከማለት የደረሱ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ወደ ቡድኑ የመግባት ፍላጎታቸው ጨምሯል፡፡ አሰልጣኙ እና ተጨዋቾቹ በኮቪድ ወቅት ሳይቀር በቴክኖሎጂ የታገዘ ዝግጅት እና መግባባት ፈጥረዋል፡፡ በአንጻሩ ኮትዲቫር በኢትዮጵያ ቡድን በደረሰባት ሽንፈት የተነሳ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኟን እስከማሰናበት ደርሳለች፡፡

በአሳማኝ መመዘኛ ሳይሆን መወሰን ስለሚችል ብቻ የአሰልጣኝ አብርሃም መብርሃቱን ኮንትራት ያቋረጠው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ስህተቱን የሚያርምበት እድል እንደገና አገኘ፡፡ የአሰልጣኝ ቅጥር እንደገና የሚያስፈልግበት ጊዜ መጣ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ የአሰልጣኝ ቅጥር ምክረ ሃሳብ የማገኘው ከቴክኒክ ክፍሉ ነው በሚል ጉዳዩን ወደ ቴክኒክ ክፍሉ መራው፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ከ30 ዓመት በላይ ከአፍሪካ ዋንጫ የመራቁን ሂደት የደመደሙት ጉምቱው ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እና ሌሎች አምስት በእግር ኳስ የተፈተኑ ባለሙያዎች ያሉበት ኮሚቴ ስለሆነ ብዙዎች ትክክለኛ ውሳኔ ያሳልፋል ብለው ተስፋ አደረጉ፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴው ቀደሞ በስፖርት ጋዜጠኞች፣ በስፖርት ባለሙያዎች፤ በብዙ ተመልካቾች ስለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች፤በተለይም ስለ ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ የተሰጠውን በቡድኑ ውስጥ መቀጠል አለበት የሚል ሃሳብ የሚደግፍ ውሳኔ ለፌዴሬሽኑ አቀረበ፡፡

ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኒጀር ጋር ላለው የደርሶ መልስ ፍልሚያ ያለው ጊዜ በጣም አጭር መሆኑ አዲስ አሰልጣኝ ማምጣት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ሁለተኛ አሰልጣኝ አብርሃም መብርሃቱ መጀመሪያ የተረከበውን እና ብዙ ድክመት የነበረበትን ብሔራዊ ቡድን ወደ አሸናፊነት ቀይሮታል፡፡ የአፍሪካ ሃያል ቡድን ከሚባሉት አንዱን የኮትዲቫርን ብሔራዊ ቡድን ብዙዎችን ባስገረመ ብልጫ ረትቷል፡፡ ከተጨዋቾች ጋር ከፍተኛ መግባባትን በመፍጠር ለብሔራዊ ቡናቸው የሚዋደቁ ተጨዋቾችን ማሳየት ችሏል፡፡ ዘጠኝ ምክንያቶችን የዘረዘረው የቴክኒክ ኮሚቴ ኢንስትራክተር አብርሃም በቡድኑ እንዲቀጥል በሙሉ ድምጽ የውሳኔ ሃሳብ አቀረበ፡፡ በብዙዎች የተጠበቀ ውሳኔ ነበር፡፡ ያልተጠበቀው የባለሙያዎችን ምክር ጥሎ ያለሙያው እና ከስፖርቱ ቤተሰብ ተቃራኒ የተወሰነው የስራ አስፈጻሚው ውሳኔ ነው፤፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ በየምርጫ ዘመኑ ብዙ ቃል የሚገቡ፣ ስፖርቱን በአንድ ጀምበር የሚቀይሩ ይመስል እስኪመረጡ የተስፋ ስትራቴጂ የሚቀይሱ፣ በብሔርም በቲፎዞም፣ በገንዘብም ሰው አደራጅተው መንበሩን ለመቆጣጠር የሚተጉ መሪ ተብየዎችን ደጋግሞ የሚያስተናግድ መስክ ነው፤፡

የቀደሟቸውን ስራ አስፈጻሚዎች የሚያስንቁ ተከታታይ የስህተት ድራማዎችን እሚተውኑ፤ እሚከውኑ አስተዳዳሪዎችን እያቀፈ የሚሄድ የስህተት ቤት ሆኖ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ቀጥሏል፡፡

ዉበቱ አባተ – የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ

በአሁኑ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ የሚመራው ስራ አስፈጻሚ ከባለሙያዎች ተቃራኒ፣ ከብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ተቃርኖ፤ ምክረ ሃሳብንም ጥሎ ማን አለብኝነት ባለው ሁኔታ ኢንስትራክተር አብርሃም አይቀጥልም ሲል ወሰነ፡፡ ኮትዲቫርን ያሸነፈው ቡድን ያሸነፈበትን ሃሳብ የመራው ሰው እንዳይቀጥል ወሰነ፡፡ በቡድኑ ተስፋ በመቁረጥ የተበተነውን የእግር ኳስ ቤተሰብ የመለሰው አሰልጣኝ እንዳይቀጥል ወሰነ፡፡ በዚህ መንገድ ከተጫወትን ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንመልሳታለን ብለው ተጫዋቾች ራሳቸው የመሰከሩለትን ሰው እንዳይቀጥል ወሰነ፡፡ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ በመጀመሪያ የስራውን ስህተት ማረም ላይ ወደቀ፡፡ በመቀጠል ተመሳሳይ እንደውም የተሻለ ስህተት በመስራት ሪከርዱን አሻሻለ፡፡ በመጨረሻም ከስህተቶች የማይማር መሆኑን አሳየ፡፡

ተመሳሳይ እጥፋቶች ላይ እየደጋገሙ መውደቅ

በየትኛውም መስክ በየትኛውም የህይወት ጉዞ ትወድቃለህ፡፡ ትነሳለህ፡፡ ስህተትም ትሰራለህ እንደገና ትኖራለህ፡፡ ከስህተቶችህም ከስኬቶችህም ተምረህ የተሸልክ ሆነህ ትቀጥላለህ፡፡ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ከስህተት መማር ተመሳሳይ ውድቀትን አለመድገም የተሰጠ ፀጋ አይመስልም፡፡ በየስራ አስፈጻሚ መለዋወጥ እግር ኳስ እና የዚህ ተወዳጅ ስፖርት ቤተሰብ ማዘን እና መቃጠሉን ቀጥሏል፡፡ ራሳቸውን ከባለሙያዎች በላይ የሚያደርጉ ብሔዊ ቡድኑን ዋጋ የሚያስከፍሉ ስህተቶችን የሚወስኑ፣ ውስብስብ በሆነው የስፖርት እውቀት ልክ የማይገኙ ከእነሱ ውጭ ሰው የሌለ ይመስል ስፖርቱ ላይ ደግመው ደጋግመው እየተመላለሱ ፌዴሬሽኑን ኋላ ቀር ያደረጉ የእግር ኳስ ስፖርት ስራ አስፈጻሚ አባላት እግር ኳሱን ማሳዘናቸውን ቀጥለዋል፡፡

በግሌ የኢንስትራክተር አብርሃም የመሰናበትን ውሳኔ እንደብዙ ባለሙያዎች የመቃወሜ ምክንያት አዲስ የተሾሙትን አሰልጣኝ በመቃወም አይደለም፡፡ እግር ኳስ ላይ ከስሜታዊነት የፀዱ፤ ሀገርን ያስቀደሙ፤ የግል ፍላጎትና መተዋወቅ ሳይሆን ሀገራዊ መለኪያዎች ላይ የሚያተኩሩ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ ከመፈለግ ነው፡፡ የዛሬ ያልተጠኑና ግብታዊ ውሳኔዎች ነገ ደግመው ሌሎች አሰልጣኞችንም እንዳይጎዱ ከመፈለግ የሚሰነዘር ሀሳብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እጅግ የሚደነቅ ጉዞ ከአደረገባቸው ሶስት አመታት በኋላ አሰልጣኙ የተሰናበቱበት መንገድ ዛሬም ድረስ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ ያኔም በድንገተኝነት ፤ እግር ኳሳዊ ባልሆነ ስሜት እና ቅናት አሰልጣኙን ከሰሩት ስራ በታች አድርጎ ለማሰናበት የተሄደበት መንገድ አስካሁን እግር ኳሱን ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ እግር ኳስ ተመልክተው የማያውቁ ሰዎች ስለ እግር ኳስ የወሰኑበት ጥቁር ውሳኔ ነበር፡፡ ምስጋና ለሰሩት ህያው ስራ ይሁንና  ሰውነት ቢሻው በስፖርቱ ቤተሰብ ልብ ውስጥ ህያው ሆነው ቀጠሉ፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ እሳቸው ላይ የተሰራው ስህተት እንዳይደገም ያቀረቡት ሃሳብ በሌላ አጋጣሚ በተመሳሳይ የስራ አስፈጻሚ ውሳኔ ውድቅ ሆኖ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዋጋ ሊከፍል የቀረበ ይመስላል፡፡

 

ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ – የብ/ቡድኑ የቀድሞ አሰልጣኝ

አሰልጣኝ አብርሃም መብርሃቱ የኢትዮጵያ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ቢያልፍ የእሱ ስራ ውጤት እንደሆነ፤ ቡድኑ ማለፍ አቅቶት ቢሸነፍ አጫዋወቱ ቢበላሽ ደግሞ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ የስራው ስህተት ውጤት አድርጎ የስፖርት ቤተሰብ እንዲያስብለት የተደረገ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ድጋሚ ከራቀ ስምንት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ቡድኑ በተደጋጋሚ ከአፍሪካ ዋንጫ ለመራቁ ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ባምንም በአመራር ስህተቶች ብዙ ነገሮችን በየጊዜው የሚደበላለቀው የስራ አስፈጻሚ ግን ተወዳዳሪ አልባ ይመስለኛል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የፉትቦል ፌዴሬሽን

እንዳሁኑ ውሉ የጠፋበት የስህተት ቋት፣ ጆሮ አልባ እና ከዘመናዊው እግር ኳስ ጋር የማይሄድ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ይዘን ከመቀመጣችን በፊት የአፍሪካ ቀዳሚ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለቤት ነበርን፡፡ ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች የእግር ኳስ ፌዴሬሽንና ብሔራዊ ቡድን ማቋቋም ፍጹም በማያስቡበት ጊዜ ኢትዮጵያ በሺ ዘጠኝ መቶ አርባ አንድ (1941) የፉትቦል ፌዴሬሽን ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ መስርታለች፡፡ ሌተናል ኮሎኔል ከበደ ገብሬን በፕሬዝዳንትነት፣ ሌተናን ኮሎኔል አበበ ደገፉን በምክትል ፕሬዝዳንትነት፣ ይድነቃቸው ተሰማን በዋና ጸሃፊነት እና ሌሎች በርካታ አባላትን ይዞ ተመሰረተ፡፡ ይሄ ስራ አስፈጻሚ የመጀመሪያውን የፌዴሬሽኑን መተዳደሪያ ደንብ ያፀደቀ ነው፡፡ የስፖርትን በሀይማኖት እና ፖለቲካዊ ጉዳይ ያለመግባት፣ የሕዝባዊ ክለቦች ማቋቋም ፤የክለቦች የብሔራዊ ቡድን አመራር እና ሌሎች ጉዳዮችን በደንብ አጥንቶ የጀመረ ፌዴሬሽን ነው፡፡ ከዚህ ስራ አስፈጻሚ የተነሱት ይድነቃቸው ተሰማ የአፍሪካ እግር ኳስ አባት እስከመባል ያበቃ አመራር አሳይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በትንሹ የሰማንያ (80) አመት ልምድ ባለቤት ነው፡፡ ዛሬ ትናንት የተፈጠሩ ሀገራት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች በሁለንተናቸው ከእኛ የተሻሉ ሆነው ብሔራዊ ቡድናቸውን፤ እግር ኳሳቸውን በተረጋጋ መንገድ እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በአንጻሩ ከምርጫው እስከ እለት ስራው የግለሰብ ፍላጎት፣ ፖለቲካዊ ሽኩቻ፣ የራስ ጥቅም፣ የክህሎት ክፍተት፣ ውዝግብ የሚያጅቡት እንደ እድሜው እንደልምዱ ያልዘለቀ የእግር ኳስ አመራር ይዘን ቀጥለናል፡፡

አቶ ኢሳያስ ጂራ – የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት

እግር ኳስ አሁንም በተወዳጅነት ቀዳሚ ስፖርት ነው፡፡ በየክልል ከተሞች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎ ያሏቸው ክለቦች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ የሚያስተዳድረውን ሊግ የሚከታተለው ታዳሚ ከብዙ ሃገሮች ጋር ሲነጻጸር ቀዳሚ ነው ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ በዚህ ውስጥ ውጤታማ ብሔራዊ ቡድን ቢፈጠር የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆነው ራሱ ስራ አስፈጻሚው ነው፡፡ እግር ኳሱ በሀገራችን የተደራጁና ዘመናዊ ማዘውተሪያዎች ያጥሩታል፡፡ ስፖንሰርሺፕ የእግር ኳሱ ችግር ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ በዚህ አቅጣጫ የሰራው ስራ አመርቂ የሚባል አይደለም፡፡ የሚከበሩ አሰልጣኞች፣ የገነኑ ኮከቦች፣ የተረጋጉ የእግር ኳስ ክለቦች በመፍጠር ረገድ ገና ምንም ያልሰራ የእግር ኳስ ስራ አስፈጻሚ ነው፤፡ የሊጉን ውድድር እንዲያስተዳድሩ ለክለቦቹ የሰጠበት፤ ብዙ አይነት የብሔራዊ ቡድኖችን ማቋቋም ፤የራስ ህንፃ መገንባት እንደመልካም ነገሮች ቢቆጠሩለትም በተቃራኒ ስህተቶቹ በብዙ ደረጃ የሚጠቀስ የእግር ኳስ አስተዳደርም ነው፡፡ በዚህ መሀል ነው እንግዲህ በብሔራዊ ቡድኑ የአሰልጣኝነት ቅጥር ላይ ትልቅ ስህተት በመስራት የስራ አስፈጻሚው የስፖርት ቤተሰቡን ወደ ሌላ ተስፋ መቁረጥ የመራው፤፡

እግር ኳስ የተለያዩ ባለቤቶች አሉት፡፡ የእነዚህ የተለያዩ ባለድርሻዎች ፍላጎት ጥቅም እና ሚና በማስተሳሰር እግር ኳሱን ወደፊት የሚያራምዱ ውሳኔዎችን መወሰን የሚችል አመራር ወሳኝ ነው፡፡ እግር ኳስ በዘፈቀደ የሚመራበት ጊዜ አልፏል፡፡ ሀሳብ አፍልቆ ስትራቴጂ ቀርጾ የእግር ኳሳችንን ጥያቄዎች በትልልቅ እሳቤዎች መምራት በሚገባን ሰዓትና ጊዜ እንደዚህ ተመልካች በኳሱ ላይ ፊቱን እንዲያዞር የሚያደርግ ግብታዊ ውሳኔ የሚፈጽም ስራ አስፈጻሚ ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ የተሻለ አስተሳሰብ እና እግር ኳሳዊ አረዳድ ባላቸው አገልጋይ ባለሙያዎች መተካትም ይኖርበታል፡፡

የእግር ኳስ አመራሮቻችን በቆሙበት ልክ ስፖርቱ አልቆመም፡፡ ቴክኖሎጂ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እና ሌሎች ሁነቶች ስፖርቱን በፍጥነት እየቀየሩት ነው፡፡ ለመማር ያልተዘጋጀ የራሱን ድምጽ ብቻ እየሰማ በሚሊዮኖች ስሜት ላይ ውሃ የሚቸልስ  የእግር ኳስ አመራር ፍጹም ለስፖርቱ እንቅፋት ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ሳይኖረው ይቀጥላል፡፡ በኮቪድ ምክንያት ችግር ውስጥ የገባውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጉዳይ የመራበት መንገድ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ሃሳብ አልባ፣ ሌሎችን ያላዳመጠ፣ ማን አለብኝነት የተንጸባረቀበት፣ የግል ፍላጎት የቀደመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሁሌም ከፍታና ዝቅታ ይኖራሉ፡፡ የእርካታ እና የተስፋ መቁረጥ ጊዜያትም አይጠፉም፡፡ ማሸነፍ እና መሸነፍም የጉዞ አካል ናቸው፡፡ ግን ተለዋዋጭነትን በትእግስት በብስለት በማስተዋል መምራት ወሳኝ ነው፡፡ እግር ኳሳችን በዚህ አልታደለም፡፡ ስህተት በሚሰራ ሳይሆን ከስህተት የተዋቀረ በሚመስል የእግር ኳስ አስተዳደር ዋጋ መክፈሉን ቀጥሏል፡፡


ስለ ጸሀፊው


ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለበርካታ አመታት በስፖርት ጋዜጠኛነት እና ልዩ ልዩ ሀላፊነቶች፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በፋና ቴሊቪዥን በአቅራቢነት እንዲሁም በብስራት ኤፍኤም 101.1 በሳምንት ለሶስት ቀናት የሚተላለፈው “ትሪቡን ስፖርት” ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

 

 

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *