በ ማርቆስ ኤልያስ (ጋዜጠኛ) – ለልዩ ስፖርት

በ1970ዎቹ፣ 80ዎቹ እና 90ዎቹ ጀርመን (ምዕራብ ጀርመን) በእነ ፍራንዝ ቤከንባዎር እየተመራች የዓለም እና አውሮፓ ዋንጫዎችን ደጋግማ ማሸነፍ ብትችልም፡ ሜዳ ላይ የሚታየው እግር ኳሷ ግን በበጎ የሚነሳ አልነበረም፡፡ ኧረ እንደውም እግር ኳሳዊ ስኬቷን “ከየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” በሚል ፍረጃ የተመደበ እና ለከፍተኛ ትችት የተዳረገ ነበር፡፡

ነገር ግን፡ የጊዜ መቁጠሪያችንን በፍጥነት ወደ አዲሱ የፈረንጆች ሚሌንየም እናምጣው እና ከዛን ወዲህ በጀርመን እግር ኳስ ምን እንደተፈጠረ እንመርምር እስኪ፡፡ ጀርመን በ2014 ብራዚል ላይ ያሸነፈችው የዓለም ዋንጫ ከዚህ ቀደም በ1954፣ በ1974 እና 1990 ካነሳቻቸው የአለም ዋንጫዎች ይበልጥ ትርጉም የነበረው፣ በብዙ ያነጋገረ እና በርካታ ትንታኔዎችም የተሰራበት ነበር፡፡

የጀርመን እግር ኳስ ለውጥ መነሻ ዩሮ 2000 ነው፡፡ ጀርመን ከእንግሊዝ፣ ፖርቹጋል እና ሮማንያ ጋር ተደልድላ በሁሉም ጨዋታዎች ማሸነፍ ካለመቻሏም ባሻገር በእንግሊዝ እና ፖርቹጋል ተሸንፋ ከሮማንያ ጋር አቻ ተለያይታ ባልተጠበቅ እና በሚያሳፍር ሁኔታ  ከምድብ ማጣርያው እንኳን ማለፍ ተሳናት፡፡

የተመዘገበው ውጤት ከአራት ዓመታት በፊት የአውሮፓ ዋንጫን ላነሳችው ሀገር “በእርግማን ውስጥ ያለ ምርቃት” ይመስል ነበር፡፡ ምክንያቱም የዩሮ 2000 አሳፋሪ አወዳደቅ ወደ ውስጧ እንድትመለከት እና በእግር ኳሷ ላይ የተለየ አካሄድ መከተል እንዳለባት ያመላከታት ነበርና፡፡

በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ ፍጥነት አልባ፣ አሰልቺ፣ በዕድሜ ጠገብ ተጨዋቾች የተሞላ እና መከላከል ላይ ያተኩር የነበረው የጀርመን እግር ኳስ ከዩሮ 2000 ውድቀት ማግስት በፍጥነት በአዲስ አካሄድ ለመጓዝ ጥርጊያ መንገዱን ጀመረ፡፡ በሒደትም ክህሎት ያለው፣ በወጣቶች የተገነባ እና የማጥቃት  አስተሳሰብ ያለው እግር ኳስ መታየት ጀመረ፡፡

የለውጡ ምልክት በትክክል ፍንጪ መስጠት እንደጀመረ የሚነገረው፡ በ2002 የዓለም ዋንጫ ጀርመን በብራዚል 2-0 ተሸንፋ ሻምፕዮን ሳትሆን በቀረችበት የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ነው፡፡ የያኔው የሩዲ ቮለር ቡድን ጎል ማስቆጠር ተሳነው እንጂ ከወትሮው በተለየ መልኩ ትኩረት የሚስብ እግር ኳስን ተጫውቶ በርካታ የጎል ማግባት ሙከራዎችን አድርጎ ነበር፡፡

በ2002 ፍፃሜ ደርሶ ዋንጫ ያጣው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን 12 ዓመታትን ጠብቆ ታላቁን ዋንጫ አነሳ፡፡ ከምንም በላይ በግማሽ ፍፃሜው አዘጋጇ ብራዚልን 7-1 በማሸነፍ ቡድኑ መነጋገርያ ሆነ፡፡

ይኽንን ድል ከዓመታት በኋላ ለማምጣት በትንሹ፣ 52 የልህቀት ማዕከላት (Center of Excellence) እና 366  የአሰልጣኞች ማሰልጠኛ ማዕከላት በመላው ጀርመን ገንብተዋል፡፡ በእነኚህ ማዕከላት ውስጥ ደግሞ 1300 ፕሮፌሽናል አሰልጣኞች ሙሉ ጊዜያቸውን በታዳጊዎች ላይ አተኩረው ሰርተዋል፡ እየሰሩም ይገኛሉ፡፡

በመጀመሪያ 2002 ላይ የጀርመን እግር ኳስ ማህበር እና የሀገሪቱ ፕሮፌሽናል ክለቦች በጋራ በመሆን 48 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ መጠነ ሰፊ የብቃት ማበልጸጊያ መርሀግብር (Extended Talent Promotion Programme) ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ፡፡ በእርግጥም የዚህ መርሀግብር ባጀት በአሁኑ ሰአት በእጥፍ ቢጨምርም አዋጪ በመሆኑ ምክንያት እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

የጀርመን እግር ኳስ በ1990ዎቹ ያጣው ይኽንን አስተሳሰብ ነበር፡፡ ጀርመንን ለዩሮ 96 ስኬት ያበቁት በርቲ ቮግትስ አዳዲስ ወጣት ተጨዋቾች አለመኖራቸውን ተከትሎ በቀጣይ ብሄራዊ ቡድኑ ችግር ውስጥ እንደሚወድቅ በጊዜው ተናግረው ነበር፡፡

ቮግትስ በ1998 የፈረንሳይ ዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ ከአራት ወራት በፊት ወጣቶችን ለማበልፀግ የሚያስችል አንድ አነስተኛ ማዕከል እንዲከፈት አድርገው የነበረ ቢሆንም በጀርመን የማስጠንቀቂያ ደውል  የተደወለው ግን ከላይ እንደገለጽኩት ከዩሮ 2000 ውድቀት መልስ ነበር፡፡

ከዚያ በፊት በጀርመን የወጣት ተጨዋቾችን ተሰጥኦ ለመለየት ይተገበር የነበረው አሰራር እንደ አሁኑ ዘመናዊነትን የተከተለ አልነበረም፡፡ የወቅቱ የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሚሮስላቭ ክሎዘ እንኳን በ21 ዓመቱ በአምስተኛ ዲቪዚዮን የሚጫወት አማተር ተጨዋች ነበር፡፡ ጥቂት መልማዮች ብቻ ወደ አገሪቱ ጠረፋማ ቦታዎች የሚያቀኑ መሆናቸውም እንዲህ ዓይነት ተሰጥኦን መመልከት አስቸጋሪ ነበር፡፡

በ2002 Extended Talent Promotion Programme በይፋ ሲመረቅ የቀድሞው የአገሪቱ ግብ ጠባቂ ጆርጅ ዳንኤል “ከዚህ በኋላ ወጣት ባለተሰጥኦ ተጨዋቾች ካሉ ከተራሮች ጀርባ ባሉ መንደሮች ውስጥ እንኳን ቢሆን ፈለገን እናገኛለን” በማለት ምልመላው ከቀደመው ጊዜ ይበልጥ ሰፊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ክለቦች እናገር

በጀርመን ይኽ የምልመላ እና ስልጠና ፕሮግራም ይፋ ከሆነ በሁዋላ ባለተሰጥኦ ተጨዋቾችን መመልመል ብቻውን ዋጋ እንደሌለው ባለሙያዎች ተገንዝበዋል፡፡ በጀርመን የተለመደው በስዊፐር (ጠራጊ) ተከላካይ እንዲሁም ሰው በሰው የመከላከል የጨዋታ መንገድ ጊዜው ያለፈበት እና ውጤታማ ለመሆን የሚያግዝ እንዳልሆነ ተረድተው የስልጠናውን መንገድ መቀየር እንዳለባቸው ተረድተው ውሳኔ ላይ መድረስ ነበረባቸው፡፡ ይኽንንም በተግባር ፈፅመዋል፡፡

ጀርመን ትኩረት ያደረገችው በየክልሉ በሚገኙ ባለተሰጥኦ ተጨዋቾች ላይ ብቻ አልነበረም፡፡ ለዚህ ተብሎ የተመደበውን ባጀት በትምህርት ቤት ተሰጥኦ ላይ አውለዋል፡፡ በት/ቤት ታዳጊ ተማሪዎች እና ተሰጥኦ ያላቸው ሌሎች ተጨማሪ በትልቅ ደረጃ መጫወት የሚችሉ ተጨዋቾችን የሚመለምሉ አሰልጣኞች ማፍራት ግድ ብሎዋቸዋል፡፡

ክለቦች በቀደመው ጊዜ በውጭ ተጨዋች ላይ ያተኩሩ ነበር፡፡ ውጤት ላይ ማተኮራቸው እንዲሁም ስለዛሬ ብቻ ማሰባቸው 11 ተጨዋቾችን ገዝተው የቡንደስሊጋውን ዋንጫ ቢያነሱ ደስተኞች ነበሩ፡፡ በአዲሱ ፕሮግራም ግን የእግርኳስ ማህበሩን አካሄድ ተቀብለው ከት/ቤቶች ጋር ለመስራት መተባበር ነበረባቸው፡፡

እርግጥ ነው ሁሉም የቡንደስሊጋ ክለቦች የሚኮሩበት የራሳቸው አካዳሚ ነበራቸው፡፡ በቅርብ ርቀት ላይ የነበሩ ባለተሰጥኦ ተጨዋቾችን መልምለው ለትልቅ ደረጃ የማብቃት ባህል እንደነበራቸውም የተደበቀ ምስጢር አይደለም፡፡ ይኽ ፕሮግራም በስራ ላይ ሲውል ግን ይበልጥ ት/ቤቶች ላይ ማተኮር ጀመሩ፡፡ ይኽ አካሄድ ከፍ ባለ ክፍያ ሌሎች ተጨዋቾችን ከማስፈረም እና ውጤታማ ከመሆን ይልቅ ይበልጥ ትዕግስተኛ መሆንን ግድ ይል ነበር፡፡

ጀርመን ከግዢ ወጥታ ድንገት በወጣቶች ላይ መስራት የመረጠችበት ምክንያት ምንድነው?

ታሪክ

በአሁኑ ሰዓት የጀርመን እግርኳስ አካሄድ የእንግሊዝን ሞዴል የሚከተል ነው፡፡ የእግር ኳስ ማህበሩ ብሄራዊ ቡድኖችን፣ የተወሰኑ የውስጥ ውድድሮችን እና አርቢትሮችን በበላይነት ይመራል፡፡ ፕሮፌሽናል ክለቦች ግን የራሳቸው ማህበር አላቸው፡፡ ይኽ ማህበር German Football League ይሰኛል፡፡ ቡንደስሊጋውን እና ሁለተኛውን ቡንደስሊጋ በበላይነት ይመራል፡፡ እስከ ፈረንጆች ሚሊኒየም ድረስ ግን ሊጉን የሚመራው የእግርኳስ ማህበሩ ነበር፡፡ ያም ቢሆን የሚና ለውጥ ከተደረገ በሁዋላ የእግርኳስ ማህበሩም ሆነ ሊጉ ስራቸውን በተቀናጀ መልኩ ያከናውናሉ፡፡

መርሃቸውም ለእግርኳስ ማህበሩ ጥሩ የሆኑ ነገሮች በሙሉ ለሊጉም ጥሩ ናቸው የሚል ነው፡፡ ይኽ የብሄራዊ ቡድኑን ጉዳይም ይጨምራል፡፡

ጀርመን በዩሮ 2000 ከምድብ ማጣርያ ውጭ ከሆነች ከሁለት ወር በሁዋላ ነሐሴ ወር ላይ የእግርኳስ ማህበሩ ብሄራዊ ቡድኑን ለማሻሻል በማሰብ አንድ ግብረሃይል አቋቋመ፡፡ ከሰባት የጀርመን ቡንደስሊጋ ክለቦች የተወጣጡ ተወካዮች የዚህ ኮሚቴ አካል ናቸው፡፡ በበላይነት የሚመራው ደግሞ በዩሮ 2000 የተመዘገበውን ውጤት “እጅግ በጣም አስደንጋጭ ውድቀት” ሲል በገለፀው የባየርን ሙኒኩ ሊቀመንበር ካርል ሄይንዘ ሩሚኒገ ነበር፡፡

ሌላኛው የኮሚቴው አባል የባየር ሌቨርኩሰኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ቮልቭጋንግ ሆልዝሃውሰር ደግሞ በወቅቱ “ይህንን ብሄራዊ ቡድኑን መመልከት ያለብን በቡንደስሊጋው 19ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ምርጥ ቡድን ነው” የሚል አስተያየትን ሰጥተው ነበር፡፡

ይኽ ሐሳብ ሁሉንም ባያስማማም የእግርኳስ ማህበሩ እና ሊጉ ስራ ተከፋፍለው እና ራሳቸውን ችለው መጓዝ እንዲጀምሩ ቀላል የማይባል ሚና ነበረው፡፡ ይኽ የተፈጠረው አብዮትም ክለቦችን የበለጠ በወጣት ተጨዋቾች ላይ እንዲያተኩሩ አደረጋቸው፡፡

ገንዘብ

ሌላው ምክንያት በወረቀት ላይ ከሚታሰበው በተቃራኒ በወቅቱ ክለቦች ከብሄራዊ ቡድኑ ያነሰ የፋይናንስ አቅም ላይ መገኘታቸው ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በ2001 መጨረሻ ቡንደስሊጋውን ለማስተላለፍ መብት የተሰጠው የቴሌቪዥን ጣብያ የገንዘብ አቅሙ ሲዳከም ክለቦች የባሰውኑ ችግር ውስጥ ገቡ፡፡

ከባየርን ሙኒክ በስተቀር ሌሎቹ በተጨዋቾች ዝውውር ገበያው ላይ ከእንግሊዝ፣ ስፔን እና ጣልያን ክለቦች ጋር መፎካከር የማይችሉ በመሆናቸው የግድ በወጣት ተጨዋቾች ላይ ከማተኮር ውጪ አማራጪ አልነበራቸውም፡፡

ለዚህ ትክክለኛ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ነው፡፡  ክለቡ በቀደሙት ዓመታት በወጣቶች ላይ ስኬታማ ቢሆንም ግዢ ላይ ማተኮርን ይመርጥ ነበር፡፡ ከ1994 – 1998 ድረስ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ከ19 ዓመት በታች ሻምፕዮን ሆኗል፡፡

ነገር ግን አንድም ተጨዋች ዋናውን ቡድን ሰብሮ መግባት አለመቻሉ ክለቡ ምን ያክል የግዢ ፖሊሲ ላይ ጥገኛ እንደነበር ማሳያ ነው፡፡

አስገዳጅነት

ቦሩሲያ ዶርትሙንድ የፋይናንስ አቅሙ ተዳክሞ ሊፈርስ ከጫፍ ሲደርስ የታደገው ባየርን ሙኒክ ነበር፡፡ ይኽ ደግሞ ዶርትሙንድን ጨምሮ ሌሎች ክለቦችን ፊታቸውን ወደ ወጣት ተጨዋቾች እንዲመለሱ አደረጋቸው፡፡

በጀርመን ሊግ ህግ መሰረት አንድ ክለብ የፕሮፌሽናል ላይሰንስ ሊያገኝ የሚችለው ሊጉ ያወጣውን ህግ ሲያከብር ነው፡፡ ዋንኛው ደግሞ የፋይናንስ አቅም ነው፡፡ የጀርመን ክለቦች በተረጋጋ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ እንዲገኙ ያደረጋቸው ዋናው ምክንያት ይኽ ነው፡፡

በ2001 እና 2002 Extended Talent Promotion Programme ተጠንቶ በይፋ ስራውን ሲጀምር የእግርኳስ ማህበሩ እና የሊጉ ክለቦች ‹‹የትኛውም የአገሪቱ ፕሮፌሽናል ክለብ የልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) ገንብቶ ብቁ የሆኑ ወጣቶችን እንዲያፈራ›› የሚል አስገዳጅ ህግ አወጡ፡፡

ህጉ ምን ያህል ታዳጊ ተጨዋቾች ለጀርመን ታዳጊ/ወጣት ቡድን ማጫወት እንዳለባቸው እንዲሁም የአሰልጣኞች እና ፊዚዮቴራፒ ቁጥር መካተት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ህጉን ተላልልፎ የተገኘ ቡድን ደግሞ ፍቃዱን ይነጠቃል፡፡

በሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጭ ያሉ አካሄዶች መቀየር

የጀርመን እግር ኳስ በእንግሊዝ ካለው አካሄድ ይለያል፡፡ እንደ ሮማን አብራሞቪች ወይም አቡ ዳቢ አንድን ክለብ ጠቅልሎ በባለቤትነት የሚመሩበትን አካሄድ በጀርመን ፈልጋችሁ አታገኙም፡፡ የአገሪቱ ክለቦች ለረጅም ዓመታት ባህል የሆነውን ማህበረሰብ አቀፍ የሆነ እና ለአንድ የጋራ በጎ ነገር የሚመራ በመሆኑ ከእንግሊዝ የተለየ ነው፡፡

ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ይኽንን አካሄድ ለመቀበል ፍላጎት አላሳየም፡፡ ነገር ግን የክለብ ላይሰንሱን ሊነጠቅ ከጫፍ  ሲደርስ ውሳኔውን ለመቀበል ተገድዷል፡፡ በዚህ ውሳኔ ተገዶ የገነባው የልህቀት ማዕከል ያፈራው ማርዮ ጎትዘ በ2014 የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ የማሸነፍያ ጎል አግብቶ አገሪቱ 24 ዓመታትን ጠብቃ የዓለም ዋንጫ እንድታነሳ አድርጓል፡፡

የጀርመን እግርኳስ አብዮትን በተመለከተ ሁለት ግብዓቶችን መኮረጅ አይቻልም፡፡ የማህበረሰብ እና ባህል ለውጡ በጀርመን ብቻ ያለ ይመስላል፡፡ የማህበረሰብ ለውጡ በግልፅ በ2009 ተስተውሏል፡፡ የጀርመን ከ21 ዓመት በታች በአውሮፓ ወጣቶች ዋንጫ የእንግሊዝ አቻውን 4-0 ያሸነፈበት ጨዋታ ለዚህ ትክክለኛ ማሳያ ነው፡፡ በወቅቱ አብዛኞቹ የቡድኑ ተጨዋቾች የዘር ግንዳቸው ከሌሎች አገራት የሚመዘዝ ነበር፡፡ አንድሬስ ቤክ (ራሺያ)፣ ሰባስትያን ቦኒሽ (ፖላንድ)፣ ዤሮም ቦአቴንግ (ጋና)፣ ዴኒስ አጎ እና ቼኔዱ ኤዲ (ናይጄርያ)፣ ፋብያን ጆንሰን (አሜሪካ)፣ ጎንዛሎ ካስትሮ (ስፔን)፣ ሳሚ ኬዲራ እና አኒስ ቤን-ሃቲራ (ቱንዚያ)፣ አሽካን ዴጃጋህ (ኢራን) እና መሱት ኦዚል (ቱርክ) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ይኽ ከ11 ዓመት በፊት የተከሰተው አጋጣሚ ጀርመን በመጨረሻም እንደ ሌሎች ዘመናዊ የሚባሉ ምዕራብዓውያን አገራት የስደተኞች መዳረሻ እንደሆነች ማረጋገጫ ነበር፡፡ ይኽ የሆነው ዘግይቶ ግን ደግሞ ግልፅ በሆነ ምክንያት ነው፡፡ ጀርመን አብዛኛዎቹን ቅኝ የገዛቻቸው አገራትን ለቃ የወጣችው ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ነበር፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተከሰቱት ነገሮች አገሪቱን ለስደተኞች ተመራጭ ቦታ አላደረጋትም፡፡

ከመጀመርያው የቱርክ ስደተኞች የተገኙ ልጆች ማንም ለጀርመን ብሄራዊ ቡድን ይጫወታሉ ብሎ አልጠበቃቸውም ነበር፡ ነገር ግን ሳይጠበቅ ነገሩ እውን ሆነ፡፡

አሁን ወደ ጀርመን የተሰደዱ ቱርካውያን ልጆች ከቤተሰቦቻቸው አገር ይልቅ ለተወለዱባት ጀርመንመጫወትን ይመርጣሉ፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ይኽ አጋጣሚ የተከሰተው የአገሪቱ እግርኳስ እንደ አዲስ እየተዋቀረ በነበረበት ሰዓት መሆኑ የአገሪቱ እግርኳስ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡

የጀርመን እግርኳስ እንዲሻሻል ብሎም የዘመናዊ እግርኳስ ሞዴል እንዲሆን ያገዘው ሌላው ምክንያት ወጣት እና ከፍ ባለ የእግርኳስ ደረጃ ያልተጫወቱ እንዲሁም አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር አቅማቸው ከፍ ያሉ አሰልጣኞች ብቅ ማለታቸው ነበር፡፡

ለብዙዎች በዚህ ረገድ ቀድመው ወደ አዕምሮዋቸው የሚመጡት የርገን ክሎፕ ቢሆኑም ራልፍ ራኚክ፣ ቶማስ ቱኸል እና ዮዓኪም ላቭ ሌሎች ማሳያ ናቸው፡፡

የጀርመን እግርኳስ ማህበር ከዩሮ 2004 ውድቀት መልስ (ጀርመን በፖርቹጋል አዘጋጅነት በተዘጋጀው የአውሮፓ ዋንጫ ሆላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ላትቪያ በሚገኙበት ምድብ ብትደለደልም ልክ እንደ ዩሮ 2000 ሁሉ ከምድቧ ማለፍ አልቻለችም ነበር) ሩዲ ቮለር ተሰናብቶ የጀርመን እግር ኳስ የለውጥ ሂደት ላይ መሆኑን ለዓለም እግር ኳስ እንደሚያሳዩ ተስፋ የተጣለባቸውን የርገን ክሊንስማንን በመሾም ብሄራዊ ቡድኑ አሁን ለደረሰበት የስኬት ደረጃ እንዲበቃ ምክንያት ሆኗል፡፡

ክሊንስማን በ2006 ጀርመን ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ማራኪ እግርኳስን የሚጫወት ቡድን አቅርቦ የሻምፒዮንነት ህልሙ ባይሳካም ምክትሉ ላቭ ሙሉ ሃላፊነቱን ተረክበው ላለፉት 14 ዓመታት እያሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡ በ2014 የዓለም ዋንጫ ላይ የተመዘገበው ጣፋጭ ስኬት ደግሞ የእግርኳስ ማህበሩ ትዕግስት ውጤት ነው፡፡


ስለ ጸሀፊው


ማርቆስ ኤልያስ 

የስፖርት ጋዜጠኛ እና የቀጥታ ጨዋታ አስተላላፊ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *