በፖላንድ ጊዲኒያ በተካሄደው 24ኛው የአለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በሴቶች የቡድን የወርቅ በወንዶች ደግሞ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች

ከውድድሩ አስቀድሞ ከፍተኛ የማሸነፍ ግምት የተሰጣቸው የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት አባብል የሻነህ እና የውድድሩ የቀድሞዋ አሸናፊ ነጻነት ጉደታ በውድድሩ 18ኛ እና 10ኛ ኪሜ ላይ በመውደቃቸው ምክንያት በግላቸው ከዚህ የተሻለ ደረጃ ይዘው ለማጠናቀቅ ቢቸገሩም በቡድን ቀዳሚ በመሆን ከሁለት አመት በፊት ያሳኩትን ድል ለመድገም ችለዋል።

ኢትዮጵያን ተከትለው ኬንያ እና ጀርመን በሴቶች የቡድን ውድድር የብር እና የነሀስ ሜዳሊያዎች ባለቤቶች ለመሆን በቅተዋል።

ኬንያዊቷ የሴቶች ብቻ የርቀቱ የክብረወሰን ባለቤት ፒርስ ጄፕቺርቺር ውድድሩን በ1:05:16 በቀዳሚነት ስታጠናቅቅ፡ በትውልድ ኢትዮጵያዊ እና በዜግነት ጀርመናዊቷ ሜላት ይሳቅ በ1:05:18 እና ያለምዘርፍ የኋላው በ1:05:19 ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

አትሌት ዘይነባ ይመር 4ኛ፣ አባብል የሻነህ 5ኛ፣ ነጻነት ጉደታ 8ኛ እና መሰረት ጎላ 15ኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በተመሳሳይ በወንዶች በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ ከኬንያ በመቀጠል በቡድን የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።

አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ ዩጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ እና ኬንያዊው ኪቢዎት ካንዴን ተከትሎ በመግባት የነሀስ ሜዳሊያ ሲያሸንፍ አንዱአምላክ በልሁ 5ኛ፣ ልዑል ገብረስላሴ 10ኛ፣ ሀይለማርያም ኪሮስ 11ኛ እና ጉዬ አዶላ 22ኛ በመግባት ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በአንድ ወርቅ፣ አንድ ብር እና ሁለት ነሀስ በድምሩ በአራት ሜዳሊያዎች ከኬንያ በመቀጠል በውድድሩ ከተሳታፋ 45 ሀገራት በሁለተኛነት ስታጠናቅቅ፤ ኬንያ ከኢትዮጵያ እኩል አራት ሜዳሊያዎችን ብታሸንፍም ሁለት ወርቅ እና ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን በመሰብሰቧ ምክንያት ቀዳሚ ለመሆን በቅታለች።

አንድ ወርቅ እና ነሀስ እንዲሁም አንድ ብር እና ነሀስ ያሸነፉት ዩጋንዳ እና ጀርመን ውድድሩን በቅደም ተከተል በሶስተኛ እና አራተኛነት ለማጠናቀቅ በቅተዋል።

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *