ምስጋና እና መልካም ምኞት

ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኜ ከተቀጠርኩ በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታችንን በሃዋሳ አለም አቀፍ ስታድየም ሴራሊዮንን በማሸነፍ ስራችንን በድል መጀመራችን ይታወሳል።

ከዚያም በሌሎች የአህጉሪቱ እና የአለም ዋንጫ ማጣሪያ መርሃ ግብሮች ላይ በመሳተፍ ካለፉት ስህተቶቻችን በመማር በሂደት የቡድኑን መሻሻል እየጎለበተ መጥቶ ኮትዲቯርን በአፍሪካ ማጣሪያ ጨዋታ በማሸነፍ እና ጠንካራ ቡድን በመገንባት የማለፍ ተስፋ ማሳየት ችለናል።

ምንም እንኳ የያዝነውን የማለፍ ተስፋ ዕውን ለማድረግና የተጣለብንን ሃገራዊ ሃላፊነት ከዳር ለማድረስ እና ህልማችንን ለማሳካት የነበረንን ፅኑ ፍላጎት በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተቀባይነት ባያገኝም እና ቢያሳዝነኝም ስኬቱን በማስቀጠል ረገድ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቻቸው እንዲሁም ተጨዋቾቹ ጠንክረው ሰርተው ብሔራዊ ቡድናችንን ለአፍሪካ ዋንጫ እንደሚያበቁት ሙሉ እምነት አለኝ።

ምስጋና

ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር በነበረኝ የሁለት ዓመት ቆይታ ካጣሁት ነገር ይልቅ ያገኘሁት ይበልጣልና ለዚህም ብዙዎችን ማመስገን እወዳለሁ። ከሁሉ አስቀድሜ ፈጣሪዬን እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!

በመቀጠል ቡድኑ እዚህ እንዲደርስ በመከባበር፣ በመደጋገፍ እና በመተሳሰብ ብሄራዊ ቡድኑን ለዚህ ያበቃችሁትን ተጨዋቾቼን እና ረዳት አሰልጣኞቼን ፋሲል ተካልኝ (ረዳት አሰልጣኝ)፣ ሙሉጌታ ምህረት (ረዳት አሰልጣኝ)፣ እንዲሁም ውብሸት ደሳለኝ (የበረኞች አሰልጣኝ) እና ይስሀቅ ሽፈራው (physiotherapist)፣ በታማኝነት በጥሩም በአስቸጋሪም ጊዜያት ከጎኔ በመሆን ስላገዙኝ እያመሰገንኩ፤

በተጨማሪም ምንም ገንዘብ ሳይከፈላቸው ደግሞ ብሄራዊ ቡድኑ የሀገር እንደሆነ በመገንዘብ እርዳታቸውን ባስፈለገኝ ጊዜ ሁሉ ከቡድኑ ጎን በመሆን ያገዙኝ ዶክተር ተስፋዬ ብርሀኔ Nutritionist (ከአዳማ University)፣ ዶክተር ዘሩ በቀለ የ catapult ባለሙያ (ከአዲስ አበባ University)፣ ሳሙኤል ስለሺ የሳይኮሎጂ ባለሙያ (አዲስ አበባ University) በሄዳቹበት መልካም እድል እየተመኘሁ ባላቹበት ምስጋናዬ ከልብ ይድረሳቹ!

ከዚህ በተጨማሪ ጨዋታዎችን በምናደርግበት ግዜ ሁሉ በስታዲየም በመገኘት ጊዜያችሁን፣ ገንዘባችሁንና ጉልበታችሁን መስዋት ላደረጋችሁ….

  • የባህር ዳር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች!
  • የሃዋሳ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች!
  • የመቀሌ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች!
  • የድሬደዋ ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዋች!
  • የአዲስ አበባ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች!

– የፕሪምየር ሊግ እና የሱፐር ሊግ ጨዋታ ለማየት በሄድኩባቸው ክልሎች ሁሉ የስፓርት ቤተሰቡ ላደረገልኝ አቀባበል እና ለሰጠኝ ፍቅር ከልብ አመሰግናለሁ!

– በፍፁም ሀገራዊ ስሜት ድጋፋቹን ከዳር እስከዳር ለሰጣቹን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ለምትገኙ መላው ኢትዮጵያውያን የሀገሬ ልጆች ምስጋናዬ ከልብ ነው!

– አስፈላጊውን ድጋፍ ለሰጣቹን የሁሉም ከተማ አስተዳደሮች፣ የፌደራልና የክልል ስፖርት ኮሚሽኖች እና የክልል ፌደሬሽኖች ምስጋናዬ ይድረሳቹ!

– ለሁሉም የስፖርት የሚድያ አካላት ቡድኑ ሲደክም በመተቸት ቡድኑ ጥሩ መሻሻል ሲታሳይ በማበረታታት ከጎናችን ስለሆናቹ ምስጋናዬ ይድረሳቹ!

– ለተሰጠኝ የስራ ነፃነት እና ትብብር ማመስገን የግድ ነውና ለስራ አስፈፃሚው ምስጋናዬ ይድረሳችሁ እላለሁ!

– የብሄራዊ ቴክኒክ ኮሚቴውና አጠቃላይ የተቋሙ ሰራተኞች ልፋታችን ግቡን እንዲመታ ሞያዊና የሞራል ድጋፍ ሰጥታችኋልና የታላቁ ምስጋናዬ አካል መሆናችሁን እንዳትዘነጉ እፈልጋለሁ!

– እንዲሁም ድጋፍ ያደረጋችሁልኝን የሙያ አጋሮቼን (አሰልጣኞች) ከልብ አመሰግናለሁ!

እንደሚታወቀው ብሔራዊ ቡድናችን ለኒጀር የደርሶ መልስ ጨዋታ ዝግጅት ለመጀመር 1 ቀን ሲቀረው የኮሮና ቫይረስ ወደ ሃገራችን መግባቱ ያቀድነው ዝግጅት እና ፕሮግራም እንዲቋረጥ ሆኗል።

በዚህም ይህንን አስከፊ በሽታን ለመዋጋት ህይወታቸውን መስዕዋት አድርገው ከፊት ለፊት ለተጋፈጡ የህክምና እና የጤና ባለሙያዎች ያለንን ታላቅ አክብሮት እየገለፅን፣ የኮትዲቫሩ ድል ለነሱና በኮቪድ 19 ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ይሁንልን እላለሁ!

በመጨረሻም ለአሰልጣኝ ውበቱ እና ለመላው የቡድኑ አባላት መልካም እድል እና ጥሩ የስራ ጊዜን እመኛለሁ!

ድል ለዋልያዎቹ! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ

አብርሃም መብራቱ
የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር እና የፊፋ ሃይ ፕርፎርማንስ ኤክስፐርት

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *