አዲስ አበባ – መስከረም 18/2013 ዓ.ም – የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በጉዳት ምክንያት ከእግር ኳስ ተጫዋችነታቸው እስኪለዩ ድረስ፡ በተለይም በ1980ኛዎቹ መጨረሻ ላይ አሁን ከፈረሰው ፐልፕ እና ወረቀት እግር ኳስ ቡድን ጋር ጥሩ የሚባል ቆይታ እንደነበራቸው ይታወሳል፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወደ ስልጠናው አለም ከተቀላቀሉ ጀምሮ ታላላቅ የሚባሉ የሀገራችንን ክለቦችን ያሰለጠኑ ሲሆን፡ በተለይም በ2003ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡናን የሊጉ ሻምፒየን ያደረጉበት ውጤታቸው በትልቁ ይነሳል፡፡

አሰልጣኙ በሀገር ውስጥ ካሰለጠኗቸው አዳማ ከነማ፣ ፋሲል ከነማ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ሀዋሳ ከነማ፣ ደደቢት እና ሰበታ ከነማ ክለቦች በተጨማሪ፣ ወደ ጎረቤት ሀገር ሱዳን በማቅናት አልአህሊ ሸንዲን ያሰለጠኑ ሲሆን፤ በሱዳን ቆይታቸው ክለቡን በሊጉ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ እንዲጨርስ በማድረግ ለአፍሪካ ኮንፌደሬሽንስ ዋንጫ ተሳታፊነት አብቅተውታል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፉት ሁለት አመታት ብሄራዊ ቡድኑን የመሩትን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱን ኮንትራት የማደስ እድሉ ሰፊ እንደነበር ሲገለጽ ቢቆይም በመጨረሻው ሰዓት የሃሳብ ለውጥ በማድረግ አሰልጣኝ ዉበቱን መሾሙ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡

አሰልጣኝ ዉበቱ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ላለፉት አስር ወራት ያክል ተበትኖ የቆየውን ብሄራዊ ቡድን በማሳባሰብ በቀጣዮቹ ወራት ውስጥ ከኒጀር ጋር ላለበትን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ተፎካካሪ ቡድን ማቅረብ የመጀመሪያ ስራቸው እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ለአሰልጣኝ ዉበቱ አባተ፡ በብሄራዊ ቡድኑ የሀላፊነት ቆይታቸው ወቅት፡ ቡድኑን ለካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ እና ለኳታሩ የአለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን የመጨረሻ ዙር የጥሎ ማለፍ ደረጃ ማድረስ ዋናዋናዎቹ ግቦች ሆነው በፌዴሬሽኑ እንደተቀመጡላቸው ተገልጿል።

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *