ጋዜጠኛ ታዘብ አራጋው – ለአማራ ብዙሀን መገናኛ ድርጀት እንደዘገበው

ባሕር ዳር- መስከረም 15/2013 ዓ.ም – 1977 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ምንጊዜም የማይረሳ አስከፊ ዘመን እንደነበር ይነገራል፡፡ ያሳለፉት በትውስታ ቅርብ ጊዜ ላይ የተከወነ ያክል ምስል ከሳች አድርገው ድርቅ እና ርኃቡን ይተርኩታል፤ ሰሚዎቹ ደግሞ ቀልባቸው ተንጠልጥሎ ሕመማቸውን እየታመሙ፣ ጠኔያቸውን ተጣነው ያዳምጧቸዋል፡፡ ያኔ ነበር ሕጻኑ ከወላጅ እናቱ ጋር የትውልድ ቀየውን ለቆ ወደ ሰፈራ ጣቢያ ያመራው፡፡

የያኔው ስደተኛ ሕጻን የአሁኑ ታዋቂ የስፖርት ጋዜጠኛ ፍስሐ ተገኝ ከወላጅ እናቱ ጋር ከያኔዋ ወሎ ጠቅላይ ግዛት ላስታ አውራጃ ከአሁኗ የሰሜን ወሎዋ ግዳን ወረዳ ሙጃ አካባቢ ተነስተው ወደ ወለጋ አቀኑ፡፡ ከእናቱ ጋር በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የደረሰው ሕጻን ዳግም ሕይወት ፊቷን አዞረችበትና ወላጅ እናቱን በሞት ተነጠቀ፡፡ ምንም እንኳን ሐዘኑ ከባድ ቢሆንም ሕይወት ትቀጥላለች እና ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናት ወደሚገኙበት በአካባቢው ካለ ሦስተኛ የሰፈራ ጣቢያ ተቀላቀለ፡፡

በሦስተኛ የሰፈራ ጣቢያ እያለ ነበር የኤስ ኦ ኤስ ዓለም አቀፍ የሕጻናት መርጃ ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ተቀብሎ ወደ ጥንታዊቷ የሐረር ከተማ የወሰደው፡፡ ወሎ ተወልዶ፣ በወለጋ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የአጭር ጊዜ ቆይታ የነበረው ጋዜጠኛ ፍስሐ ሐረር የዕድገቱ ከተማ ሆነች፡፡ ሐረር ውስጥ ተምሮ፣ ተላምዶ እና ባህሉን ኑሮ ያደገው ፍስሐ ራሱን የሐረር ልጅ አድርጎ ያያል፤ የልጅነት ትውስታው ሁሉ ከሐረር ነበረና።

ጋዜጠኛ ፍስሐ በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ዘርፍ አንቱታን ካተረፉት ውስን ጋዜጠኞች መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከ13 ዓመታት በፊት ወደ እንግሊዝ ሀገር አምርቶ ነዋሪነቱን በዚያው አድርጓል፡፡ ነገር ግን ከትውልድ ሀገሩም ወጥቶ ሁሌም አንድ ጥያቄ ነበረው “የማንነት” በስደት ከወሎ መውጣቱን ያውቃል፤ እናቱን በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ አጥቷል፤ አባቱ በሕይወት አለመኖራቸው ተነግሮታል፤ የተረፈው ነገር እናቱ በሕጻንነቱ የነገሩት ቁርጥራጭ የማንነት ተረኮች ብቻ ነበሩ፡፡ የተረፈ ወዳጅ ዘመድ ይኖረው ይሆን? እትብቱ የተቀበረው ቦታስ የት ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሊያፈላልግ ከ13 ዓመታት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት ተመለሰ፡፡

ወደ ሐረር ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ሲገባ የተሞላው መረጃ ወሎ ጠቅላይ ግዛት ላስታ አውራጃ ሙጃ በሚባል አካባቢ ቀበሌ 15 እንደተወለደ ያሳያል፡፡ የእናት እና የአባቱን ስም እስከ አያት ከትውልድ ቀየው ጋር ይዞ ማፈላለግ ጀመረ፡፡ ግን ብዙም አልደከመም ላልይበላ በሚገኝ አንድ ጓደኛው ቤተሰብ አማካኝነት በተባለው ቦታ ሲፈለግ በሕይወት የሉም የተባሉትን አባቱን ጨምሮ ወንድሙን፣ የእናቱን ወንድም አቶ ፈንታው ታገልን እና ሌሎች ቤተሰቦቹን ተቀላቀለ፡፡ የዚያን አስከፊ ዘመን ትውስታ ባያጠፋውም ፍስሐ ከየት እና የማን እንደሆነ አውቋል፡፡

የተወለደበትን ቦታ ረግጦ ሲያይ ያኔ በድርቁ ምክንያት ከተፈጠረው አስከፊ ክስተት ይልቅ ዛሬም ከቀሪው ዓለም እጅግ ወደኋላ የቀረው የትምህርት፣ የጤና እና የመሠረተ ልማት ግንባታ ያሳዝነዋል፡፡ የተረሳ አካባቢ እንደሆነም ይሰማዋል፡፡ ስሜት ብቻ ግን አይደለም ለአካባቢው የእትብት ዋጋ ከፋይም ሆኗል፤ ፍስሐ፡፡

ቤተሰቦቹን እና የትውልድ ቀየውን ፈልጎ ያገኘው ጋዜጠኛ ፍስሐ በቀጣይ አቅሙ የፈቀደውን እና ለአካባቢው ያስፈልጋል ያለውን አደረገ፡፡ 417 ሺህ ብር በላይ ወጪ አድርጎ “የብርግነት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን” ሠርቷል፡፡ ትምህርት ቤቱ ሁለት ብሎኮች እና ስምንት የመማሪያ ክፍሎች ተግንብተውለታል፡፡ የግዳን ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም አያሌው 45 የተማሪ ወንበሮችን ለማሠራት በወረዳው ከተደራጁ ወጣቶች ጋር ውል መውሰዱንም ነግረውናል፡፡

ጋዜጠኛ ፍስሐ ለተማሪዎቹ የጽሕፈት መሣሪያ ድጋፍ እያቀረበ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን የምታስተናግደው የብርግነት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መለስተኛ ሙሉ ሳይክል (1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል) የማደግ እድል እንዳላት ነው አቶ አብርሃም የነገሩን፡፡ ባለፈው ዓመት 173 ተማሪዎችን ተቀብላ የምታስተናግደው ትምህርት ቤቷ በቀጣይ እስከ 350 ተማሪዎችን የማስተናገድ አቅም ማግኘቷንም ገልጸዋል፡፡

“ትምህርት ላይ መሥራት ትውልድ ላይ መሥራት ነው” ያሉት የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፤ ጋዜጠኛ ፍስሐ ለሌሎች የአካባቢው እና የክልሉ ተወላጆችም በየአካባቢው መሰል የዳስ እና የድንጋይ መቀመጫ ትምህርት ቤቶችን በመተጋገዝ መቀየር እንደሚቻል ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *