በ ሳሙኤል ስለሺ – የስፖርት ባለሞያ – ለልዩ ስፖርት

አቡበከር እና ሚኪያስ ከክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ እና ዋና አሰልጣኙ ካሳዬ ጋር

ሰሞኑን ኢትዮጵያ ቡና ለክለቡ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ጭምር ብሩህ ተስፋ ያላቸውን አቡበከር ናስር እና ሚኪያስ መኮንን የተባሉ ሁለት ወጣት ተጨዋቾችን ባልተለመደ ሁኔታ ለአምስት አመታት ማስፈረሙን ተከትሎ በሐገራችን አዲስ የተጨዋቾች ዝውውር ባህል ሊያቆጠቁጥ የሚችልበትን ተስፋ አሳይቷል፡፡ የተጨዋቾቹን ሙሉ ጥቅም በማክበር፣ የኢኮኖሚ ጥያቄ በአግባቡ በመመለስ፣ የሚገባቸውን ክፍያ በመፈፀም ረዘም ላሉ ጊዜያት ወጥነት ያላቸውን ተጨዋቾች መጠቀም ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ በአሁን ጊዜ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ተጨዋቾችን ለአጭር ጊዜ ብቻ ማስፈረም፣ ተጫዋቾችን ከማቆየት እና ክፍተቶቻቸው ላይ ከመስራት ይልቅ ሁሌ በግዢ ላይ መንጠልጠል፣ በአንድ የዝውውር መስኮት በርካታ ተጨዋቾችን መልቀቅ፣ ብዛት ያላቸው ተጨዋቾችን በአንድ ጊዜ ማስፈረም እና መሰል አሰራሮች በስፋት ይታያሉ፡፡

ይህ የተጨዋቾች ዝውውር ዘዬ ምንም አለም አቀፍ ተሞክሮ የሌለው፣ በጥናትም ሆነ በፅሁፍ ያልተደገፈ፣ የተጨዋቾችን እድገት የሚገታ፣ የቡድኖችን ጥንካሬ የሚጎዳ፣ የሐገርን እግር ኳስ የሚያቀጭጭ፣ ለሐብት ብክነት፣ ለሙስና/ሌብነት/ስርቆት የሚዳርግ በአጠቃላይ እግር ኳሳዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሌለው በተቃራኒው ስፖርቱንም ሆነ ስፖርተኛውን የሚደፍቅ አካሄድ ነው፡፡ ይህንን ባህል ማን ጀመረው፣ ማን አሳደገው፣ ለምን ተጀመረ፣ ለምን መግታት አልተቻለም የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎችን ለዛሬው የክፍል አንድ ጥንቅር ጋብ አድርጌ የእግር ኳስ ስፖርት መደብን አና የቡድን ግንባታ ሳይንሳዊ ሒደት ትንታኔዎች ላይ ብቻ ላተኩር፡፡ ቀሪዎቹን በክፍል 2 እና 3 ጥንቅሮች እመለስበታለሁ፡፡

የእግር ኳስ ስፖርት መደብ

በብዙዎቻችን ዘንድ ስፖርትን “የግል” እና “የቡድን” በማለት የመክፈል ዝንባሌዎች ይታያሉ፡፡ ሆኖም ግን የስፖርት ስነልቦና “የግል” የሚባል ስፖርት አይነት እንደሌለ እና ሁሉም ስፖርቶች የቡድን ስፖርቶች (Team Sport) እንደሆኑ እና ውጤቱም የጋራ ተብሎ ሊጠራ እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ ለምሳሌ የጃማይካ የመቶ ሜትር ተወዳዳሪዎችን ብንመለከት ትራኩ ላይ ሲፈነጩ በግል የሚሮጡ ሊመስለን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ለአስር እና አስራ አንድ ሰከንድ በግል ቢሮጡም እንኳ ለአመታት ልምምድ ያደረጉት፣ የሰለጠኑት፣ የበሉት፣ የጠጡት፣ ሆቴል ያረፉት በቡድን ነው፡፡

ዩዚያን ቦልት በዚህ የቡድን መንፈስ ውስጥ ተመችቶት እና ደስ ብሎት ባይሰለጥን እና በልምምድ ላይ ያለውን እንዲያወጣ የሚደርግ አጣማሪ ባይኖረው ኖሮ በትራክ ላይ የሚመጣው ውጤት አነስተኛ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ የሰፋ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዩዚያን ቦልት ውጤት የአሰልጣኙ እና የሌሎች ባለሙያዎች ድምር ውጤት በመሆኑ እንደምናስበው “በግል” የተገኘ ሳይሆን በቡድን የተሳካ ነው ሊባል ይገባል፡፡ ታዲያ ‹‹ሩጫም ሆነ እግር ኳስ እንደ ቡድን ስፖርት ከተቆጠሩ በአንድ የመቶ ሜትር ሯጮች ቡድን እና በአንድ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ቡድን መሀከል ያለው ልዩነት እንዴት ሊገለፅ ይችላል?›› የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ስፖርት ስነ ልቦና መልስ አለው፡፡

ዩዜይን ቦልት እና አሰልጣኙ ግሌን ሚልስ

እንደ ስፖርት ስነ ልቦና ስፖርቶችን የቡድን እና የግል በማለት ከመለየት ይልቅ ተደጋጋፍያዊ (Interactive) እና አብሮአዊ (Coactive) ብሎ መክፈሉ የተሻለ አረዳድ እንዲኖረን ያስችላል፡፡ ተደጋጋፍያዊ የሚባሉ ስፖርቶች እንደ እግር ኳስ ያሉ ስፖርቶችን የሚያካትት ሲሆን የአንድ ተጨዋች ጥንካሬ እና ድክመት በሌላኛው ላይ ጥገኛ ሆኖ የሚገኝበት ነው፡፡ እንደምሳሌም የአማካኙ ጥሩ አለመሆን የአጥቂው ብቃት ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳድረው፣ የአንደኛው መሀል ተከላካይ ብቃት ሌላው ላይ እንደሚመሰረተው ማለት ነው፡፡

ከዚህ በተለየ ኮአክቲቭ በሚባሉ ስፖርቶች የሚሳተፉ ስፖርተኞች ጥንካሬ እና ድክመት በሌላኛው የቡድን አባል ላይ የማይመሰረት ቢሆንም አጠቃላይ ውጤቱ ግን የሁሉም ድምር ውጤት ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ የሰፋ ነው፡፡ ለምሳሌ አራት በመቶ ዱላ ቅብብልን ብንመለከት መጀመሪያ የሚነሳው ተወዳዳሪ ፍጥነት ሌላኛው ተወዳዳሪ ፍጥነት ላይ ምንም ሚና ባይኖረውም አጠቃላይ የቡድኑ ውጤት ላይ ግን ጉልህ ተፅእኖ አለው፡፡ እግር ኳስም ሆነ አራት በመቶ ዱላ ቅብብል የቡድን ስፖርት ቢሆኑም በባህሪ ግን ፈፅሞ እንደሚለያዩ ይሄ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ እግር ኳስ ተደጋጋፍያዊ የቡድን ስፖርት ሲሆን የአራት በመቶ ሜትር ሩጫ ደግሞ አብሮአዊ የቡድን ስፖርት ነው ማለት ነው፡፡

ይህ ትርጓሜ እንደው እንደቀልድ መታለፍ የሌለበት ትንተና ነው፡፡ ትንተናው የእግር ኳስ ስፖርት ባህሪን ጠንቅቀን እንድናውቅ የሚረዳ ሲሆን ስፖርቱን እንደባህሪው እና ተፈጥሯዊ ስሪቱ እንድንመራው፣ እንድናስተዳድረው፣ እንድናሰለጥነው፣ እንድንጫወተው እና እንድንደግፈው የሚያደርግ ነው፡፡ እግር ኳስን በአትሌቲክስ ተፈጥሮ፣ በብስክሌት ውድድር ስሜት ከያዝነው እድገቱ ይገታል፡፡ ተደጋጋፍያዊ ስፖርቶች በአንፃራዊነት ከፍተኛ የሆነ ተግባር ተኮር ውህደት (Task Cohesion) እንዲሁም አብሮአዊ ስፖርቶች ደግሞ በአንፃራዊነት ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ተኮር ውህደት (Social Cohesion) እንደሚያስፈልጋቸው ሳይንሱ ይጠቁማል፡፡

በተግባር ተኮር ውህደት ውስጥ የቡድን አባላት የሚኖራቸውን ግልፅ ሚና እስኪያውቁ (Role Clarity)፣ የተሰጣቸውን ሚና እስኪቀበሉ (Role acceptance)፣ በተሰጣቸው ሚና ዕምነት እስኪያሳድሩ (Role efficacy)፣ በቡድኑ ውስጥ የሚና መደበላለቅ እስኪወገድ (Role Conflict) እና በተሰጠ ሚና እርካታ እስከሚመጣ (Role Satisfaction)  ድረስ ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ለጊዜው የውህደቶቹን ልዩነት ጋብ አድርገን በደፈናው የቡድን ውህደት እንዴት ይመጣል የሚለውን እንመልከት፡፡

የቡድን ግንባታ ሒደቶች

የትኛውም የቡድን ግንባታ የሚጀምረው ከሰዎች ስብስብ (Group) ሲሆን የሰዎች ስብስብ ከቡድን (Team) በእጅጉ የሚለይ ነው (ምንም እንኳን ከአማርኛ አጠቃቀም ውስንነት የተነሳ  ሁለቱንም ‹‹ቡድን›› እያልን በተለምዶ ብንጠራውም በመሀከላቸው ከፍተኛ ልዩነት አለ)፡፡ በአብሮነት እቁብ የሚጥሉ፣ አንድ ዕድር ላይ የሚሳተፉ፣ ጠዋት ጠዋት በአብሮነት ስፖርት የሚሰሩ፣ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ አርማ አዳራሽ ውስጥ የተቀመጡ ሰዎች እና የመሳሰሉት ቡድን ለመሆን ብዙ የሚቀራቸው ነገር አለ፡፡

የሰዎች ስብስብ (Group) ወደ እውነተኛ ቡድን (Team) እንዲያድግ የተለያዩ ተፈጥሯዊ ደረጃዎችን ማለፍ ያለበት ሲሆን ከላይ የቀረበው የተክማን የቡድን ውህደት ደረጃዎች (Tuckman Stages of Group Development) በአምስት ደረጃዎች የተከፈለ ሲሆን የቡድኑ ውጤታማነት በቡድኑ ውህደት ደረጃ ላይ እንደሚመሰረት ያስቀምጣል፡፡ እንደ ተክማን አከፋፈል የመጀመሪያው ደረጃ “የጥንስስ ደረጃ” (Forming Stage) በማለት ሊሰየም የሚችል ሲሆን አባላት እርስ በእርስ የሚተዋወቁበት፣ ጥንካሬያቸውን እና ድክመታቸውን የሚለዩበት፣ በዛ ቡድን ውስጥ ያላቸውን ቦታ እንዲሁም ፍላጎት የሚያጠነጥኑበት እና ውሳኔ የሚወስኑበት ወቅት ነው፡፡

ሰሞኑን በወጡ አለም አቀፍ ዜናዎች አሌክሲ ሳንቼዝ “ገና የመጀመሪያ ልምምዴን ሰርቼ ስጨርስ ነበር ማንቸስተር ዩናይትድን መልቀቅ እና ወደ አርሴናል መመለስ የፈለኩት” ማለቱ በመጀመሪያው የጥንስስ ደረጃ ላይ ከቡድኑ ጋር አብሮ መቀጠል አለመፈለጉን ያሳየናል፡፡ በዚህ ደረጃ የሚኖር የቡድን ውጤታማነት በአማካኝ ደረጃ የሚቀመጥ ሲሆን ቡድኑም ካለቀለት ቡድንነት ይልቅ ‹‹ጊዜያዊ የስራ ቡድን›› (Working Group) በማለት ሊሰየም ይችላል፡፡ ይህንን ተከትሎ ከቀናት ወይም ወራት በኋላ ‹‹የማዕበል ዘመን›› (Storming Stage) የሚመጣ ሲሆን ‹‹የአወኩሽ ናኩሽ›› ባህሪ በአባላት ውስጥ ይስተዋላል፡፡ ተጨዋቾች እርስ በእርስ መጋጨት፣ በቡድኑ ውስጥ ሌሎች ትናንሽ ቡድኖች መፈጠር፣ የሀይል ሚዛንን መሻማት እና አልታዘዝ ባይነት እዚህ ደረጃ ላይ በሚገኙ ቡድኖች ውስጥ ጎልቶ ይታያል፡፡

በዚህ ደረጃ የሚገኙ ቡድኖች ‹‹ሐሰተኛ ቡድን›› (Pseudo Team) የሚል ስያሜ ሲኖራቸው ውጤታማነታቸውም ከተጨዋቾቹ አቅም እና ችሎታ አንፃር እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ በአሰልጣኙ እና አመራር አቅም እንዲሁም በተጨዋቾቹ ችሎታ የማዕበል ዘመኑ አልፎ ቡድኑ ይበልጥ እየተዋሀደ ሲመጣ ወደ ሶስተኛው ደረጃ ያድጋል፡፡ ይህ ሶስተኛ ደረጃ ‹‹የእርጋታ ደረጃ›› (Norming Stage) በማለት የሚገለፅ ሲሆን የተጨዋቾች ህብረት አይሎ እና የቡድኑ ውጤታማነት ጨምሮ የሚታይበት ነው፡፡ በቡድኑ ውስጥ የሚታዩ ትናንሽ ቡድኖች ፈርሰው የተጨዋቾች መስተጋብር የሚያይለበት እና መልካም ንፋስ የሚነፍስበት ወቅት ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ አራተኛው ደረጃ የሚመጣ ሲሆን የአንድ ቡድን የመጨረሻ አቅም የሚታይበት ‹‹የልቅነት ደረጃ›› (Performing Stage) ይከሰታል፡፡

በዚህ ደረጃ ለመድረስ የቻሉ ቡድኖች እውነተኛ አቅማቸውን የሚያሳዩ ሲሆን ይህንን ለረዥም ጊዜያት ይዘው መቀጠል ከቻሉ ከፍተኛ ውጤት ያሳያሉ፡፡ ከጊዜያት በኋላ የመጨረሻው ዘመን ‹‹የድፍርስነት ደረጃ›› (Adjourning Stage) የሚመጣ ሲሆን የትኛውም ነገር ዘለአለም የማይኖር ከመሆኑ አንፃር ከውድድር (Tournament) መጠናቀቅ በኋላ፣ ከተጨዋቾች ከፍተኛ ቅይይር ብዛት፣ ከወሳኝ ተጨዋቾች መልቀቅ፣ ከአሰልጣኝ መሰናበት እና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥም ተፈጥሯዊ የመበተን ሁኔታ ነው፡፡ ለዚህ ሰሞነኛው ባርሴሎና ማሳያ ሲሆን አሁን ላይ ጣዕሙን ጨርሶ፣ ውጤታማነቱ ቀንሶ (ካለፉት 12 አመታት ውስጥ ያለምንም ዋንጫ አመቱን ያጠናቀቀበት ብቸኛው አመት ዘንድሮ መሆኑን ልብ ይሏል)፣ ተጨዋቾችን ማቆየት ተስኖት እየተመለከትነው ነው፡፡

ይህ ከላይ የተቀመጠው የንድፈ ሐሳብ ትንተና (ምንም እንኳን ንድፈ ሐሳብ በሐገራችን እግር ኳስ በእጅጉ የሚጣጣል እና ‹‹እግር ኳስ ውስጥ ቲዮሪ›› የለም የሚሉ የተዛቡ አመለካከቶች እያቆጠቆጡ ቢመጡም) ነገሮችን በምክንያት እንድንከውን፣ በጥልቀት እንድንረዳ ይረዳናል፡፡ ከዚህ ንድፈ ሐሳባዊ ትንተና በጥቅሉ አምስት አንኳር ነጥቦችን ለማውጣት እንችላለን፡፡

  • አንድ ስኬታማ ቡድንን ለመፍጠር በተለይም እንደ እግር ኳስ ያሉ ተደጋጋፍያዊ ቡድኖችን ለመገንባት ጊዜ እና የተጨዋቾች እርጋታ እንደሚያስፈልግ፤
  • ውጤታማነት እና የቡድን ጥንካሬ እንደቡድን ውህደት ደረጃው እንደሚለያይ፤
  • የቡድን ግንባታ ፍጥነት እንደ ቡድኑ አሰልጣኙ ብቃት፣ እንደተጨዋቾቹ ልምድ እና ችሎታ የሚለያይ እንደሆነ፤
  • አንዳንዶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቡድናቸውን ገንብተው ሶስተኛው ወይም አራተኛው ደረጃ ላይ ለመገኘት ሲችሉ ሌሎች ግን ከመጀመሪያው እና ከሁለተኛው ደረጃ ለመውጣት ሲቸገሩ እንደምናስተውል፤
  • የቡድን ግንባታ ወደ ፊት ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላም የሚመለስ ሲሆን ተሰርቶ አልቋል የተባለለት ቡድን በተለያዩ አስተዳደራዊ ምክንያቶች (ለምሳሌ የደሞዝ አለመክፈል)፣ ቴክኒካል ጉዳዮች (ለምሳሌ ውጤት ማጣት)፣ የወሳኝ ተጨዋች ወይም አሰልጣኝ ክለቡን መልቀቅ እና በመሳሰሉት ምክንያት እንደገና ሊሰራ የሚችልበት አስገዳጅ ሁኔታ እንደሚፈጠር፤

በጥቅሉ ከዚህ ከክፍል-1 ጥንቅር የምንረዳው እግር ኳስ ተደጋጋፍያዊ የቡድን ስፖርት (Interactive Team Sport) እንደሆነ እና ይህንን መደጋገፍ ከግብ ለማድረስ የተጨዋቾች የአብሮነት ቆይታ እንዲሁም ዘላቂ የሆነ ውህደት (Cohesion) በተለይም ተግባር ተኮር ውህደት (Task Cohesion) አስፈላጊ እንደሆነ ነው፡፡ በቀጣይ የክፍል-2 ጥንቅር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ክለቦች ላይ ያለውን የተጨዋች እና ቡድን እርጋታ (Player and Team Stability) ትንተናን እና እያስከተለ ያለውን እግር ኳሳዊ ጉዳት ይዳሰሳል፡፡


ስለ ጸሀፊው


ሳሙኤል ስለሺ

ፀሀፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል የስፖርት ስነልቦና እና የእግር ኳስ መምህር እንዲሁም ተመራማሪ ሲሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመኑ ሊያፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል፡፡    

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *