በዐቢይ ሀብታሙ – ለልዩ ስፖርት

በቅርቡ የታንዛንያውን ክለብ አዛም የተቀላቀለው የኬንያው ክለብ ጎርማያህ የቀድሞ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ማፒጋኖ የታንዛንያ ቮዳፎን ፕሪምየር ሊግ በኹነኛ የሊግ አስተዳደር መመራቱ በርካታ ኬንያዊያን ተጨዋቾች ከየክለቦቻቸው እንዲኮበልሉ እንዳደረጋቸው ይናገራል።

ሁለት የውድድር ዓመታትን ለመቆየት የሚያስችለውን ፊርማ ለታንዛኒያው ኃያል ክለብ ከውል ውረቀቱ ጋር ያወዳጀው ማፒጋኖ  እንደ ሲምባ ኤስ ሲ፣ አዛምና ያንጋ የመሳሰሉ የታንዛኒያ ታላላቅ ክለቦች የገነቧቸው ስፖርታዊ መሰረተ ልማቶችና ፋሲሊቲዎች( Sport Infrastructures & Facilities) የውጭ አገራት በተለይም ኬንያዊያን ተጨዋቾች ወደ ታንዛኒያ የመጉረፋቸው ምስጢር እንደኾነ ያምናል።

ዕለተ ቅዳሜ ደማቅ ክብረ በዓል በማሰናዳት የፈረጠመ የገንዘብ ጡንቻችንን እዩልን ያሉት ሲምባዎች ክለቡን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጨዋቾቻቸውን መስከረም 6፣2020 በሚጀምረው የቮዳኮም ፕሪምየር ሊግ(VPL) ላይ ይዘው ይመጣሉ።

‘የአዛም 2020 ክብረ በዓል’ የሌላኛው ክለብ ፌስቲቫል ነበር። ክብረ በዓሉ ዳሬ ሰላም ከተማ ውስጥ የሚገኘው ቻማዚ ስታዲየም በደማቅ ኹኔታ ተከብሯል። የታንዛኒያ ስፖርቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ሀሪሰን ምዋክዬምቢ፣ የክለቡ ጌቶች ታይኮን ሰዒድ ሳሊም ባክህሬሳ፣ ቦንጎ ስታር አሊ ኪባ እና ሌሎች የክብር እንግዶች ክብረ በዓሉ ላይ ታድመዋል።

ከዚህ ቀደም ሲምባ እግር ኳስ ክለብ ክብረ በዓላቸውን ሞካፓ ስታዲየም እንዳከበሩ ኹሉ ባለተራዎቹ አዛሞችም ድግሳቸውን ያካኼዱት አስር ሺህ የተመልካች መቀመጫዎች በተገጠመለት ቻማዚ ካምቦሎጆ ነበር።

ቻማዚ ስታዲየም በቀለማት ህብር ማጌጡ የበዓሉ ልዩ ድምቀት እንደነበር ዴይሊ ኔሽን የተሰኘው የወሬ ምንጭ በአንድ  ዘገባው ዳሶታል ። ከክለቡ ጌቶች መሃከል ኪባና ቦንጎ ፍላቫ እንዲሁም የዕለቱ አጋፋሪ ምስጋ ስሙ ነጭ በሰማያዊውን የአዛም እግር ኳስ ክለብ ማልያን በመልበስ ለደጋፊዎቻቸው ደስታና ሳቅ ፈጠረውላቸው አሳልፈዋል ።

በቮዳኮም ፕሪምየር ሊግ ላይ አየተወዳደረ በሚገኘው ክለብ ናሙንጉ እና ክለብ አዛም መካከል ተደርጎ በባለሜዳው አዛም ሁለት ለአንድ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የወዳጅነት ጨዋታ ደግሞ የክብረ በዓሉ መደምደሚያ ነበር።

ጎርማያህ የስድስት ወር ደመወዜን ሊከፍለኝ አልቻለም በሚል ከክለቡ ጋር የእንለያይ የጋራ ስምምነት የፈፀመው የክለቡ የቀድሞ ግብ ጠባቂ ማፒጋኖ ወደ ታንዛኒያ ሊግ አምርቷል።

የታንዛኒያ ሊግ በየግዜው አየተሻሻለ መምጣቱ የኬንያ ሊግ ላይ ብልጫን እየወሰደ መኾኑ የተለያዩ ሪፖርቶች መግለፃቸው እንዳሉ ኾነው ግብ ጠባቂው ማፒጋኖ ለኔንሽን ስፖርት የሰጠው ሃሳብ ይጠቀሳል።

“በታንዛኒያ ሊግ ያሉ የብዙሃኑ ትላልቅ ክለቦች ቢዝነስ ሞዴል አውሮፓዊያኑ የሚጠቀሙበት ዓይነት ይመስላል፤ ወደ አገሪቱ የሚጎርፉት ኬንያዊያን ተጫዋቾች ደግሞ ማረጋገጫ መስጠት ይችላሉ። የኬንያ ሊግ እጅ ያጠረው የስፖርቶች መሰረተ ልማት ጉዳይ በታንዛኒያ ሊግ በሽበሽ ነው። የታንዛኒያ ትላላቅ ክለቦች በባለቤትነት የተያዙት ከእግር ኳስ ፍቅር የተነሳ ፈሰስ(Invest) ለማድረግ ዝግጁ በኾኑ ግለሰቦች ነው።”

ታንዛኒያውያን እግር ኳስን ስለሚወዱ ጨዋታዎች እንደማያመልጣቸው የሚገልፀው ይህ ግብ ጠባቂ በአንፃሩ በኬንያ ሊግ ጎርማሃያና ሊዮፓርድስ ከፍተኛ ተከታይ ቢኖራቸውም ቁጥራቸው ከታንዛኒያዊያኖቹ ሲምባና ያንጋ ጋር  ሲወዳደደር እዚህ ግባ የሚባል አለመኾኑን ይናገራል።

እ.ኤ.አ 2015 ለአንድ የውድድር ዘመን ብቻ ለአዛም የተጫወተው የካካሜጋ ሆም ቦይዝ አጥቂ አለን ዋንጋ ታንዛንያዊያን ደጋፊዎች ከኬንያዊያኑ ይልቃሉ የሚለውን የግብ ጠባቂው ማጋፒኖ ሃሳብን ይጋራል። ክለቡ የጥሩ ስፖርታዊ መሰረተ ልማቶች ባለቤት መኾኑ እንዲሁም ተጨዋቾቻቸው ምንም ዓይነት የደመወዝ መዘግየት ስጋት ስለሌለባቸው በምቾት እንዲኖሩ አድርጓቸዋል ሲል ሃሳቡን ያክላል።

አንድ የቀድሞ የኤፍ ሲ ሊዮፓርድስ ኬንያዊ አጥቂ በበኩሉ በተጫዋቾች አያያዝ፣ ስፖርታዊ መሰረተ ልማቶችና የደጋፊ ሰፊ መሰረት(Fan Base) ረገድ ታንዛንያዊያን የተሻሉ ናቸው ይላል። “የትናንሽ ክለቦችና የሴካፋ ጨዋታዎች ላይ ሳይቀር ደጋፊዎቻቸው ስታዲዮሞቻቸውን ይሞላሉ፣ እግር ኳሱ በትልቅ ኢንቨስትመንት የተደገፈ ነው። ለጨዋታ እጅግ ጥልቅ ፍቅር አላቸው።”

በ2015 ከሴካፋ ሻምፒዮኖቹ ጋር የተጫወቱ ሌሎች ኬኔያዊያን ተጨዋቾች አሁን ላይ ለኦማኑ አል ኢቲሃድ የሚጫወተው ሀምፍሪይ ሚይኖ እንዲሁም ጉዳት ላይ የሚገኘው የፖስታ ሬንጀርሱ ተከላካይ ጆአኪንስ አቱዶ ለታንዛኒያው ኃያል ክለብ ከ2012 እስከ 2014 የውድድር ዘመን በጋራ ተጫውተዋል።

የባንዳሪ የቀድሞ ረዳት አሰልጣኝ ኢብራሂም ሺካንዳ ሌላው ለታንዛኒያ ሊግ ቤተኛ ነው የሚባል ነው። 2010 የውድድር ዘመን ላይ የአዛም ክለብ ቁልፍ ተከላካይ ነበር። ሺካንዳ የረዳት አሰልጣኝነት ዕድልን ያገኘው 2014 ላይ ክለቡን ከመልቀቁ በፊት ነበር።

የታንዛኒያ ክለቦች የሚከተሉት የተጨዋች አያያዝ ሞዴልን በተመለከተ ሐምሌ 2018 ላይ ሲንጋዳ ዩናይትድን ለቆ ኬ’ኦጋሎን የተቀላቀለው ማፒጋኖ ለኔሽን ስፖርት እንደተናገረው ክለቡ ለውጭ ተጨዋቾቹ የማደሪያ የሚኾን እያንዳንዳቸው ወለሎች ሦስት መኝታ ክፍሎች  ያሉት ቅንጡ አፓርትመንት ከዳሬ ሰላም ከተማ ጥቂት ማይሎች  ወጣ ብሎ በሚገኝ ኪቺጂ የተባለ ስፍራ እንዳለው ይናገራል።

ሁሉም የውጭ ተጨዋቾች ለወርሃዊ የቤት ክራይ ፍጆታ ቢያንስ እስከ አርባ ሰባት ሺህ ሺሊንግ(47,000.00 sh) ይከፈልላቸዋል። በተጨማሪም ተጨዋቾቹ የግል መኪና ተሰጥቷቸዋል። በየቤታቸው ያሉ የግል ሰራተኞቻቸውን ወርሃዊ ሂሳብንም ክለቡ ይሸፍናል።

የሃያ ሦስት ዓመቱ ማፒጋኖ የጨዋታ ጉርሻ(Bonus) በተመለከተ በተጨዋቾች መሃከል ልዩነት እንደማይፈጠር ይገልፃል።  የአዛም ክለብ አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ አንዱ ከሌላው ሳይለይ በዕለቱ ከስኳድ ዝርዝር ውጪ ለነበሩ ተጨዋቾችም ጭምር የጉርሻ ክፍያ ይከፈላቸዋል። ነገር ግን በዕለቱ ተሰልፈው የተጫወቱት በጨዋታው ላይ እንዳሳዩት ብቃት ከሃያ ሺህ እስከ አምሳ ሺህ ሺሊንግ በየደረጃው ይከፈላቸዋል።

እንደ ሲምባና ያንጋ ሁሉ አዛም ክለብም ቻማዚ ስታዲየም ላይ እጅግ የዳበረ ስፖርታዊ መሰረተ ልማቶች መገንባት ችሏል። ጂምናዚየምና የመዋኛ ገንዳዎች ለተጨዋቾች ተዘጋጅተዋል። በተጨማሪም ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚከፈላቸው የጽዳት ሰራተኞችና ተጨዋቾችን በስነ ምግብ ዙሪያ የሚረዱ   ምግብ አብሳዮች ተቀጥረዋል።

ማፒጋኖ ስለ አገሩ ኬንያ እና ታንዛንያ ክለቦች ባሰበ ቁጥር ልዩነታቸው ፍንትው ብሎ ይታየዋል። ለዚህም ተከታይ ሃሳቡ ኹነኛ አስረጅ ኾኖለታል።

“ኬንያ ውስጥ ጎርማሃያና ሊዮፓርድስ ለስታዲየምና የስልጠና ሜዳዎች ኪራይ ሲከፍሉ በአንፃሩ ታንዛንያ ውስጥ የሚገኙ ትናንሽ ክለቦች እንኳ ሳይቀሩ የራሳቸው የስልጠናና መጫወቻ ሜዳ አላቸው።”

ተጨዋቹ አገራቱን በማነፃፀር ብቻ  ጉዳዩን ማለፍ አልወደደም ይልቁን ኬንያዊያን ክለቦች ቢያደርጉ መልካም ነው ብሎ ያመነበትን የመፍትሔ ሃሳብ እንዲህ ይገልፃል። ” ጎርማያህና ኤ ኤፍ ሲ ሊዮፓርድስ የእግር ኳስ መሰረተ ልማት ላይ ፈሰስ(Invest) ማድረግ አለባቸው። በስርዓት የሚመራ የእግር ኳስ አስተዳደርም  ያስፈልጋቸዋል። ያኔ ከታንዛንያዎቹ ሲምባ፣ አዛምና ያንጋ እኩል መስተካከል ይችላሉ።”

ተጨዋቹ የሁለቱን አገራት ሊጎች በንፅፅር ካስረዳበት ሃሳቡ ወጣ ይልና ስለ ቀጣይ  የታንዛኒያ ቆይታው ሲናገር አዛምን ከተቀላቀለ ጀምሮ በማኔጅመንቱ በኩል በገንዘብም ረገድ በርካታ ድጋፎች ስለተደረገለት ቀጣይ የውድድር ዓመት ጥሩ ብቃቱን ለማሳየት የፊቱን በተስፋ አሻግሬ አየተመለከትኩ ነው ይላል።

በሮማንያዊው አሰልጣኝ አሪስቲካ ቺዮባ አየተመራ የ 2019/2020 ቮዳፎን ፕሪምየር ሊግን ከሻምፒዮኑ ሲምባ በአስራ ስምንት ነጥቦች አንሶ በሰባ ነጥቦች በሦስተኛነት ያጠናቀቀው ክለብ አዛም ምንም እንኳን ከወዲሁ እንደ ኢማኑኤል ቻርለስ፣ አዌሱ አዌሱ፣ አሊ ኒዮንዚማ፣ ኢስማኤል ኢዚዝ እና አዩብ ልያንጋ አይነት አዳዲስ ተጨዋቾችን ቢያስፈርምም አሁንም ቢኾን በተጨዋቾች ዝውውር ላይ ብርቱ ሥራ እያከናወኑ መኾናቸውን የክለቡ ኃላፊዎች ገልፀዋል።

ከዚህ ባሻገር ሁሉም የአገሪቱ ክለቦች ባሳለፉት የውድድር ዘመን (የCOVID 19 ጉዳይ ሳይረሳ) የተስተዋሉ ችግሮቻቸው ዙሪያ እርምት በመውሰድና ጠንካራ ጎናቸውን የበለጠ የማጉላት ሥራ ላይ ይተጋሉ፤ መስከረም 6፣2020 የሚጀምረውን የቮዳፎን ፕሪምየርሊግ በመናፈቅ ጊዜያቸውን የቅድመ ዝግጅት መርሃግብሮቻቸው ላይ ያሳልፋሉ። ሊጉን መዳረሻ ያደረጉ ቤተኞቹና የከርሞዎቹ ኬንያዊያን እግር ኳሰኞችም ሳይዘነጉ!!!

               ቸር ያሰንብተን!!!


ስለ ጸሀፊው


ዐብይ ሐብታሙ

መምህር እና ጋዜጠኛ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *