በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ላለፉት አምስት ወራት ተቋርጦ የነበረው አለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር፡ በሞናኮ ዋንዳ ዲያመንድ ሊግ ትላንት ካቆመበት ሲቀጥል በርካታ አስገራሚ ውጤቶች ተመዝግበውበታል።

ከእነዚህም መካከል ዩጋንዳዊዉ የ10,000ሜ የዓለም ሻምፒዮን ጆሽዋ ቼፕቴጊ ኢትዮጵያዊዉ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከ16 ዓመታት በፊት ሔንግሎ ላይ ባስመዘገበው 12:37.35 ይዞት የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን 12:35.36 በሆነ ሰዓት በመግባት የግሉ ያደረገበት ይጠቀሳል።

የ23 አመቱ ዩጋንዳዊ የትላንቱን ጨምሮ ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ ያስመዘገበው 4ኛ የዓለም ክብረወሰኑ ሲሆን፣ የ15, 10 እና 5 ኪሜ የጎዳና ላይ ውድድር ክብረወሰኖች ደግሞ የተቀሩት ናቸው።

ምንም እንኳን የአትሌት ቀኒነሳ በቀለ ይሄኛው ክብረ ወሰን ቢሰበርም፡ አሁንም ድረስ የ5000ሜ የቤት ውስጥ (12:49.60) እና የ10,000ሜ (26:17.53) ውድድሮች የዓለም ክብረ ወሰኖች በአትሌቱ ስም ይገኛሉ።

ከውድድሩ አስቀድሞ ከሔለን ኦቢሪ እና ሲፈን ሀሰን ጋር ከፍተኛ ፉክክር እንደምታደረግ ስትጠበቅ የነበረችው ለተሰንበት ግደይ በበኩሏ በ5000ሜ ውድድር የኢትዮጵያውያንን የምሽቱ የተሻለ ውጤት አስመዝግባለች።

የ10,000 ሜ የአለም የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ ለተሰንበት፡ እስከ ፉክክሩ ማጠናቀቂያ ድረስ ከፍተኛ ትንቅንቅ ብታካሂድም በኬንያዊቷ አትሌት በ አራት ሰኮንዶች ተቀድማ በ14:26.57 ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች።

በ1500ሜ የተሳተፈው ሌላኛው ኢትዮጵያው አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ አምስተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፡ የርቀቱ የዓለም ቀጥር አንድ አትሌት ኬንያዊዉ ቲሞቲ ቺሪዮት ደግሞ ውድድሩን በቀዳሚነት ጨርሷል።

ሞሮኳዊው ኤል ባካሊ በሻነፈበት የ3000ሜ መሠናክል የተሳተፉት የርቀቱ የአለም የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ለሜቻ ግርማ እና የአምናው የውድድሩ ባለድል ጌትነት ዋሌ በቅደም ተከተል 8ኛ እና 10ኛ ሆነው አጠናቀዋል።

በአጠቃላይ ትላንት ምሽት በሞናኮ የተከናወነው የ2020 የመጀመሪያው የዲያመንድ ሊግ ውድድር፡ አንድ የዓለም፣ ሶስት የአካባቢ (አህጉር)፣ ሁለት የውድድሩ፣ ሶስት የቦታው እና ዘጠኝ ብሔራዊ ክብረ ወሰኖች የተሻሻሉበት ነበር።

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *