|በ ቅድስት ታደሰ – የአትሌቲክስ ህክምና እና ስነምግብ ባለሞያ – ለልዩ ስፖርት|

ከእያንዳንዱ ስኬታማ አትሌት ጀርባ እጂግ ፈታኝ የሆኑ ነገር ግን በጽናት የታለፉ በርካታ መሰናክሎች እንዳሉ የታወቀ ነው። ከእነዚህ ፈተናወች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ደግሞ የስፖርት ጉዳት ሊሆን ይችላል፤ ይህ ጉዳይ በተለይም በእንስት አትሌቶቻችን ላይ ሲከሰት ደግሞ አስቸጋሪነቱ የበለጠ ይሆናል።

እኔም በተከታዩ ጽሁፌ በአለም ዙሪያ በእንስት አትሌቶቻችን ላይ ደጋግሞ በመከሰት ቅድሚያውን በሚይዘውና፡ በተፈጥሮ የሰውነት ሂደታቸው እና ከስልጠና ጫና ምክንያት በሚመጣው የሦስት ማዕዘንዮሽ ጉዳት /Female Athlete Triad/ ዙሪያ ሙያዊ ሀሳቤን ቀለል ባለ መልኩ ላጋራችሁ ወደድሁ፡፡

የሶስት ማዕዘንዮሽ ጉዳት አሳሳቢነት  ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኝ ግንባር ቀደም ሚና ከነበራቸው ክስተቶች አንዱ፡ እ.ኤ.አ በ1994 በዳኞች “ወፍራም ነሽ” የሚል አስተያዬት ምክንያት የሰውነት ክብደቷን ለመቀነስ በተከተለችው ያልተስተካከለ የአመጋገብ ስርዓት ችግር ምክንያት (Anorexia Nervosa) በ22 ዓመት ዕድሜዋ፡ የሰውነት ክብደቷ በእጂጉ ቀንሶ እና 21 ኪሎግራም ብቻ ሆኖ ህይወቷ ያለፈው አሜሪካዊቷ የጅምናስቲክ ስፖርት ተወዳዳሪ ክሪስቲ ሄንሪክ ህልፈት ዋነኛው ነው።

ይህንን ክስተት ተከትሎ፤ በመላው አለም የሚገኙ አትሌቶች፣ አስልጣኞች፣ የአትሌት ቤተሰቦች እና በአጠቃላይ መላው የስፖርቱ ማህበረሰብ፡ በሴት አትሌቶች ላይ የሚከሰተውን ይህንን የ3ቱ ተያያዥ የማዕዘን ጉዳቶች/Female Athlete Triad/ ጆሮ መስጠት ጀመረ፡፡

በሴት አትሌቶች ላይ የሚከሰተው የሦስቱ ማዕዘን ጉዳት /Female Athlete Triad/ ምንድን ነው?

ይህ ጉዳት በጥቅሉ የሶስት መሰረታዊ የጤና ዕክሎች ውስጣዊ ግንኙነት እና አንዱ የሌላኛው መንስኤ እንዲሁም ተያይዞ የሚመጣ ሲሆን እንደሚከተለው ይብራራሉ፡፡

ሀ. ከተዛባ የአመጋገብ ስርዓት መንስኤ የሚነሳ የሀይል እጥረት /Energy deficiency due to Disordered Eating/

ለ. የወር አበባ ፍሰት መዛባት/ Menstural Dysfunction/

ሐ. የአጥንት መሳሳት እና ተያያዥ የአጥንት ችግሮች/osteoporosis and bone related problems/

ሀ. ከተዛባ የአመጋገብ ስርዓት መንስኤ የሚነሳ የሃይል እጥረት /Energy deficiency due to Disordered Eating/

በተዛባ የአመጋገብ ስርዓት አትሌቷ በስልጠና ዝግጅት ወቅት የሰውነቷ ክብደት መሆን ከሚገባው መጠን በታች ይሆናል፡፡ ይህም የአትሌቷ ክብደት ከመጠን በታች ያነሰ ቢሆንም፡ ነገር ግን አትሌቷ የሰውነት ክብደት ወይም ውፍረት እጨምራለሁ ከሚል ስጋት የተነሳ ተገቢውን የአመጋገብ ስርዓት ባለመከተሏ ምክንያት በሰውነቷ ውስጥ ከፍተኛ የሃይል እጥረት የሚከሰት ይሆናል፡፡

የተዛባ የአመጋገብ ስርዓት መንሴዎች

– በስልጠና ጫና ምክኒያት የሚመጣን የሰውነት ተጨማሪ ሃይል ፍላጎት መተካት አለመቻል፤

– ስልጠና ከሚጀመርበት እድሜ በታች በቶሎ መጀመር

– የማህበራዊ ጉዳይ ቀውስ እና ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መግባት ናቸው፡፡

የአመጋገብ ስርዓት መዛባት ያለባት አትሌት ለተለያዩ የጤና ችግሮች የምትጋለጥ ሲሆን በዋነኛነት፡-

የጡንቻ ችግሮች፣ የደም ዝውውር፣ የልብ ምት ሥርዓት መዛባት ችግሮች፣ የኢስትሮጅን ሆርሞን መዛባት፣ የወር አበባ መቅረት፣ የአጥንት መሳሳት ችግሮች እና የመሳሰሉት ያጋጥማታል፡፡

ለ. የወር አበባ ፍሰት መዛባት /Menstural Dysfunction/

በስፖርት ውስጥ የወር አበባ ፍሰት መዛባት የሚያስከትሉ ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆኑም በዋነኛነት ከሚታዩት ውስጥ፡ ከስልጠና ጫና ጋር ተያይዞ፣ ባልተስተካከለ የአመጋገብ ሥርዓት ክስተት እና በኤስትሮጂን ሆርሞን አሰራር ስርዓት መዛባት ምክንያት የሚከሰቱ ይገኙበታል። ከሌሎች መንስኤዎች ውጪ የወር አበባ ዘግይቶ መምጣት እና በተከታታይ ለ3 ወር እና ከዛ በላይ መቅረት (amennorea) በስፖርቱ ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ጉዳት ነው፡፡

ሐ. የአጥንት መሳሳት እና ተያያዥ ችግሮች /osteoporosis/

ይህ ችግር በወር አበባ የፍሰት መዛባት ምክንያት በተዘዋዋሪ ለአጥንት ጤናማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው የኢስትሮጂን ሆርሞን መቀነስን ስለሚያስከትል እና የዚህ ሆርሞን መቀነስ ለአጥንት መሳሳት እና ጥንካሬ ማጣት፡ ለአይረን ማዕድን መጠን መቀነስ፡ እንዲሁም ለጤናማ የአጥንት ስርዓት ሂደት መፋለስ ችግር ምክኒያት ይሆናል፡፡

ይህም ሴት አትሌቶችን በቀላሉ በጫና ምክኒያት ለሚመጣ ስብራት/ stress fracture/ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡

በሀገራችን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በቂ ጥናቶች ባይኖሩም፡ በቅርብ ጊዜ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፡ ከላይ በተገለፁት ችግሮች ምክንያት ሦስቱም ጉዳቶች በአንድ ጊዜ የመከሰት እድላቸው ሰፊ ነው፡፡

ይህ ጉዳት ለምን ይከሰታል?

የራስ መተማመን መቀነስ በተለይም ከሰውነት አቋም ጋር ተያይዞ የሚመጣ የአበላል ችግር፣ ከተለያየ አቅጣጫ የሚመጡ ግፊቶች እና ውጥረት፣ ሳይንሳዊ የስልጠና ሂደት አለመከተል፣ ወቅታዊ የሆነ የጤና ምርመራ አለማድረግ ወዘተ…

በአትሌቷ ላይ ችግሩ መከሰቱ እንዴት ይታወቃል?

በቀላሉ በችግሩ ምክንያት የሚታዩ ምልዕክቶችን በማየት፣ ለምሳሌ፡- ቶሎ ቶሎ የመድከም ስሜት፣ የቆዳ ድርቀት፣ በተደጋጋሚ የማስታወክ ምክኒያት የሚከሰት የፊት መገርጣት፣ የመገጣጠሚያ፣ የሆድ /ጀርባ/ ደረት ህመም፣ ድብርት እንዲሁም በሌሎች የህመም ምክንያቶች የወር አበባ መቅረት፤ በቂ መረጃ ከአትሌቷ በመውሰድ፣ እንዲሁም የተሟላ አካላዊ እና የላብራቶሪ ምርመራ በማድረግ።

መፍትሔዎች

– በሴት አትሌቶች በሚከስቱ 3ቱ ተያያዥ ጉዳቶች ላይ ለአትሌቶች፣ አሰልጣኞች፣ ቤተሰብና ለሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላት በቂ ግንዛቤ መፍጠር፣
– ሳይንሳዊ የስልጠና ስርዓት መከተል፣
– የስልጠና እና ውድድር አመት ከመጀመሩ በፊት አጠቃላይ የቅድመ ጤና ምርመራ የማድረግ ባህል ማዳበር፣
– ተከታታይነት ያለው የቤተሰብ /አሰልጣኝ እና ሌሎች ደጋፊ አካላት ድጋፍ መስጠት፣
– ዘላቂነት ያለው የስነ-ልቦና፣ ህክምና እና ስነ-ምግብ ክትትል ማድረግ፣

– ችግሩ መኖሩ በምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ ሙሉ ተገቢውን ህክምና ማድረግ፤

* እራሳችንን እና ወገኖቻችንን ከኮሮና ቫይረስ እንከላከል


ስለ ጸሀፊዋ


ቅድስት ታደሰ

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን – የስፖርት ህክምና እና ስነ-ምግብ ከፍተኛ ባለሞያ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *