አዲስ አበባ – ሰኔ 19/2012 ዓ.ም – ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር እና ቢጂአይ ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አምስት አመታት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ፈጸሙ።

በሸራተን አዲስ ሆቴል በተከናወነው የፊርማ ስምምነት ስነ-ስርዓት ላይ፡ የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ሚ/ር ሎውረን ሌኩዬ “እውነተኛ ወዳጅነት በእንዲህ አይነት ወቅት ይፈተናል። እኛም ዛሬ ይህንን የአጋርነት ስምምነት በመፈጸም በጥሩም ሆነ በመጥፎ ጊዜ ለክለቡ ያለንን አጋርነት አረጋግጠናል።” ብለዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የቦርድ ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል በበኩላቸው “በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የተፈጸመው ይህ ስምምነት የክለባችንን ህዝባዊነት የበለጠ የሚያጠናክር እና ለኢትዮጵያ ስፖርትም ትልቅ እንድምታ ያለው እንዲሁም የሁለቱን አንጋፋ ተቋማት ለዘመናት የዘለቀ ወዳጅነት ቀጣይነት ያረጋገጠ ነው።” ብለዋል።

ስለ ስፖንሰርሺፑ ዝርዝር ስምምነት የተጠየቁት የየተቋማቱ ኃላፊዎች “የክለቡን ክብር እና የኩባንያውን አቅም የሚመጥን እንዲሁም የወቅቱን ሁኔታ ያገናዘበ ስምምነት ፈጽመናል። ነገር ግን ይሄን ያክል አድርገናል ብለን ቁጥር በመጥራት ሌሎች ላይ መደናገጥን መፍጠር እና ራሳችንን ማግዘፍ አንፈልግም።” በማለት ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

ቀጣዮቹ ሁለት እና ሶስት ወራት የክለቡ የአክሲዮን ማህበርነት ሁኔታ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚገባበት እና የቡድኑ የልምምድ ማዕከል ግንባታ የሚከናወንበት እንደሚሆን እና የስቴዲየሙ ግንባታ ጉዳይን በተመለከተ ግን ዋናው ችግር የፋይናንስ መሆኑን በመግለጽ፡ ሌሎች ክለቡን የሚያጠናክሩ ስራዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ቆይተው፡ ከ2014 ዓ.ም በኋላ ስራውን ለመጀመር ሀሳብ መኖሩም ተገልጿል።

የክለቡ ከፍተኛ አመራር እና ደጋፊዎች የሆኑት አቶ አብነት ገብረመስቀል እና አቶ ጀማል አህመድ፡ በቅርቡ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን  የኃላፊነት ቦታ መረከባቸው ለክለቡ ትልቅ ጥቅም እንደሚያመጣ እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *