በ ማርቆስ ኤሊያስ – ለልዩ ስፖርት

እግርኳሳችን ከባርሴሎና እግርኳስ ክለብ አካዳሚ ምን ሊማር ይችላል?

 ለአንድ አገር የእግርኳስ ዕድገት ወይም እግርኳስ ክለብ ስኬት አስፈላጊ ከሚባሉ ግብዓቶች መሐከል አንዱ የእግርኳስ ማሰልጠኛ ማዕከል (አካዳሚ)  መሆኑ የተደበቀ ምስጢር አይደለም፡፡ ዋነኛ ዓላማውም ታዳጊዎቹ  በስርዓት የታነፁ እንዲሆኑ፡ በዋናው ቡድን ደረጃ ለመጫወት የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው እና ከዋናው ቡድን የጨዋታ ዘይቤ ጋር እንዲላመዱ ማድረግ ነው፡፡

በአውሮፓ በዚህ ረገድ በርካታ ክለቦች ስኬታማ ናቸው፡፡ በሆላንድ አያክስ እና ፌይኖርድ፣ በስፔን ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና፣ በፖርቹጋል ቤንፊካ፡ ፖርቶ እና ስፖርቲንግ ሊዝበን፣ በእንግሊዝ ማንቸስተር ዩናይትድ፡ አርሰናል እና ሊቨርፑል፣ በጀርመን ባየርን ሙኒክ እና ሼልከ 04 የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የባርሰሎናው ላ ሜሲያ አካዳሚ  ለአመታት ባፈራቸው ከዋክብቶች ብዛት  ከሁሉም  ይበልጥ ትኩረትን እንደሳበ ቆይቷል፡፡ በ1702 የተገነባው ይኽ አካዳሚ በ1966 እንደ አዲስ ታድሶ አግልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ከጥቅምት 1979 ጀምሮ ከካታሎንያ ውጭ ለሚመጡ ሰልጣኞችም የማደርያ አገልግሎት መስጠቱ ባርሴሎናን የበለጠ ተጠቃሚ እንዳደረገው ይታመናል፡፡ ከ1979-2009  ባሉት አመታት ላ ሜሲያ 440 ሰልጣኞችን ተቀብሎ አሰልጥኗል፡፡ ከእነኚህ መካከል ግማሽ ያህሉ ከካታሎንያ የመጡ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሌሎቹ የስፔን  ክፍለ ሀገራት፤ ከካሜሩን፣ ከብራዚል፣ ከሴኔጋል እንዲሁም  ከአርጀንቲና የመጡ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የማሰልጠኛ ማዕከሉ ውጤቶች መካከል እስካሁን ድረስ ለዋናው ቡድን የመጫወት ዕድል ያገኙት 40 ያህሉ ናቸው፡፡

የላ ሜሲያ የምልመላ ሂደት እና አሰራር

ባርሴሎና ከሌሎች ክለቦች ለየት ባለ መልኩ በታዳጊዎች ምልመላ ቴክኒኩ ላይ ያተኩራል፡፡ በዚህ ረገድ ክለቡ እንከን አልባ ምልመላዎችን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡ የላ ሜሲያ መልማዮች በዚህ ረገድ በሶስት ነገሮች ላይ ያተኩራሉ፡፡

*ቴክኒክ፣ ፍጥነት፣ ጨዋታን የሚመለከቱበት እይታ እንደ መስፈርት ይተታያል፡፡ ይኽ መስፈርት በእያንዳንዱ የዕድሜ እርከን የሚተገበር ነው፡፡  ክለቡ ናይጄርያ እና ግብፅን ጨምሮ በ20 አገራት ቅርንጫፎችን ከፍቶ ስራውን ይከውናል፡፡

ላ ሜሲያ በስሩ 40 መልማዮች አሉት፡ እነዚህም 15 በካታሎንያ፣ 15 ከቀሪው የስፔን ክፍል እንዲሁም 10 መልማዮች ደግሞ በመላው ዓለም የሚሰሩ ናቸው፡፡  በዚህ መሰረት ከስድስት እስከ ስምንት ዓመት የሚሆናቸው 1000 ታዳጊዎች የሙከራ ዕድል ተሰጥቶዋቸው 200 ሰልጣኞች ወደ አካዳሚው ይገባሉ፡፡ ቀሪዎቹ ሰልጣኞች ለ15 አከባቢያዊ ክለቦች ተሰጥተው እንዲዘጋጁ ይደረጋል፡፡ ባርሴሎና ለእነኚህ ክለቦች የገንዘብ፣ የስልጠና እና የቴክኒክ ምክር እና ድጋፍ ይሰጣል፡፡

የባርሴሎና ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ከ300 በላይ ተጨዋቾችን ይይዛል፡፡ 24 አሰልጣኞች ይኽንን በ12 የተከፈለ ቡድን ይመራሉ፡፡ ዶክተሮች፣ የስነልቦና እና የስነምግብ ባለሙያዎች እንዲሁም ምግብ አብሳዮች እና ፊዚዮቴራፒስቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 56 ባለሙያዎች የዚህ ቡድን አካል ሆነው  ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡

“የአካዳሚያችን ዋነኛ ዓላማ ከታች እስከ ላይ ተመሳሳይ የጨዋታ ፍልስፍና እና አስተሳሰብ መፍጠር ነው” ይላሉ – የቀድሞ የክለቡ ቴክኒክ ዳይሬክተር ፔፕ ሴጉራ፡፡

በላ ሜሲያ የ4-3-3 የጨዋታ አሰላለፍ የሆላንድ እግርኳስ ፍልስፍና የሆነው ቶታል ፉትቦል (የማያቋርጥ የቦታ ልውውጥ)  እና የስፔን እግር ኳስ መገለጫ የሆነው ቲኪታካ (የማያቋርጥ የኳስ ቅብብል) ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡

በተለይ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በ2008 ክረምት ባርሴሎናን ከተረከበ በሁዋላ ከቋሚ 11ዱ ውስጥ ሰባቱ በተደጋጋሚ ጊዜ የላ ሜሲያ ፍሬዎች ነበሩ፡፡ በ2009 ደግሞ የመጀመሪያው የላ ሜሲያ ፍሬ ሊናል ሜሲ የባሎን ዲኦር ተሸላሚ ሆነ፡፡ በቀጣዩ  ዓመት የመጨረሻዎቹ ሶስት  የሽልማቱ ዕጩዎች ሊዮኔል ሜሲ፣ አንድሬስ ኢንዬስታ እና ዣቪ ኸርናንዴዝ መሆናቸው ለላ ሜሲያ አካዳሚ ትልቅ ኩራት ከማጎናጸፉም በላይ  ዝናውን በመላው ዓለም ያናኘ ነበር፡፡

የላ ሜሲያ አካዳሚ የእግር ኳስ ልማት ተፅዕኖ ከባርሴሎና አልፎ በስፔን ብሔራዊ ቡድን በጉልህ ተንፀባርቋል፡፡ በአሰልጣኝ ቪቼንቴ ዴል ቦስኬ የተመራችው ስፔን በደቡብ አፍሪካ በተዘጋጀው ዓለም ዋንጫ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፕዮን ስትሆን ሰባቱ ተጨዋቾች የላ ሜሲያ ፍሬዎች ነበሩ፡፡ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ፈረንሳያዊ አጥቂ ኤሪክ ካንቶና “በ2010 የዓለም ዋንጫውን ያነሳችው ስፔን ሳትሆን ባርሴሎና ነው” ማለቱ የዚህ ማሳያ ነው፡፡

ህዳር 25/2012 ባርሴሎና ዛሬ በህይወት በሌሉት አሰልጣኝ ቲቶ ቪላኖቫ እየተመራ ከሌቫንቴ ጋር ባደረገው ጨዋታ 13ኛው ደቂቃ ላይ ዳኒ አልቬስ በጉዳት ተቀይሮ ሲወጣ ተክቶት የገባው ማርቲን ሞንቶያ መሆኑን ተከትሎ የቡድኑ ቋሚ 11 ሙሉ በሙሉ  የላ ሜሲያ ፍሬ ዎች በመሆናቸው  አዲስ ታሪክ ጽፈዋል፡፡

የላ ሜሲያ ፍልስፍና እና ራዕይ

*በተቻለ አቅም በርካታ ዋንጫዎችን ማንሳት(ላ ሊጋ፣ ኮፓ ዴል ሬይ፣ የስፓኒሽ ሱፐርካፕ፣ ቻምፒዮንስ ሊግ፣ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ፣ የፊፋ ዓለም ክለቦች ዋንጫ)

*ማራኪ እግር ኳስን መጫወት

*በዋናው ቡድን ውስጥ ከፍተኛውን የላ ሜሲያ ሰልጣኝ ቁጥር መጠቀም

የላ ሜሲያ ሰልጣኞች ቀናቸውን እንዴት ያሳልፋሉ?

ታላላቅ እግርኳስ ተጨዋቾችን ያፈራው ላ ሜሲያ  ሙሉ ለሙሉ ትኩረቱን እግርኳስ ላይ ያመዝናል? የሚል ጥያቄ ከተነሳ መልሱ በፍፁም የሚል ነው፡፡ ይልቁንም ይበልጥ የቀለም ትምህርት ላይ ያተኩራል፡፡ ለእግር ኳስ በቀን ውስጥ የሚሰጠው ጊዜ  90 ደቂቃ ብቻ ነው፡፡

አንድ የላ ሜሲያ ሰልጣኝ በአማካይ ቀኑን የሚያሳልፈው በሚከተለው መልኩ ነው፡፡ ጠዋት 12:45 ከእንቅልፍ መነሻ ሰዓት ነው፡፡ 1፡15 ላይ ሰልጣኙ ለቁርስ ራሱን ያዘጋጃል፡፡ 1፡30 ሲሆን ሰልጣኞች የሚፈልጉትን የምግብ አማራጭ ይመገባል፡፡ 2:00 ሲል ሰልጣኞች በአውቶቡስ ወደ ት/ቤት ይሄዳሉ፡፡ እስከ 8:00 በት/ቤት ያሳልፋሉ፡፡ የቀለም ትምህርት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡

ከ8፡00-9፡00 ያለው ጊዜ የምሳ ሰዓት ነው፡፡ እግረመንገዳቸውን ራሳቸውን ዘና ያደርጋሉ፡፡ ከ9፡30-10፡30 ያለው ጊዜ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው እንግሊዝኛ፣ሒሳብ ወይም የሳይንስ ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፡፡ 11:00 ሲሆን ልምምድ መስራት ይጀመራል፡፡ 90 ደቂቃ የሚወስደው ልምምድ ከተጠናቀቀ በሁዋላ ምሽት 2፡00 ሰልጣኞች ነፃ የሚሆኑበት ጊዜ በመሆኑ ከኢንተርኔት ጋር ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ,ያነባሉ ወይም የቪዲዮ ጌም ይጫወታሉ፡፡ ምሽት 3፡00 የራት ሰዓት ነው፡፡ ከ3፡30-4፡30 ትርፍ ጊዜ ነው፡፡ ከ4፡30 ጀምሮ ወደ እንቅልፋቸው ይመለሳሉ፡፡

ባርሴሎና ለላ ሜሲያ በዓመት ምን ያህል ይከፍላል?

ባርሴሎና ከአካዳሚው በሚወጡ ታዳጊዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያደርጋል፡፡ አንዱ ማሳያ ለአካዳሚው ሰልጣኞች የሚከፍለው ዓመታዊ ክፍያ እና ተያያዥ ወጪ ነው፡፡

ክለቡ ለቢ ቡድኑ የሚያወጣውን ወጪ ሳይጨምር በዓመት 10 ሚሊዮን ዩሮ ይከፍላል፡፡ ይኽ ክፍያ ባየርን ሙኒክ እና አርሰናል እያንዳንዳቸው በዓመት ከሚፈፅሙት 3 ሚሊዮን ዩሮ ከሶስት እጥፍ በላይ ይልቃል፡፡ እንዲህ ከፍ ያለ ትኩረት እና ወጪ ክለቡ ምን ያክል ለታዳጊ ሰልጣኞች የክለቡ ዲኤንኤ በውስጣቸው እንዲኖር እና የጨዋታ ፍልስፍናውን እንዲገነዘቡ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡

ወጥ የሆነ ምልመላ

የላ ሜሲያ የታዳጊዎች ምልመላ ከእንግሊዝ በተቃራኒ ነው፡፡ ከቁመት እና አካላዊ ጥንካሬ በተቃራኒ ቴክኒክ ቅድሚያውን ይወስዳል፡፡ ሊዮኔል ሜሲን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ከተክለ ሰውነታቸው ጋር ተያይዞ በእንግሊዝ ትኩረት አያገኙም፡፡ ይኽ አካሄድ በተለይም ዮሃን ክሯይፍ ባርሤሎናን ከተረከበ በሁዋላ ይበልጥ ጎልቶ ተስተውሏል፡፡

ባርሣ በዚህ የምልመላ መንገድ ሜሲ፣ ዣቪ ኸርናንዴዝ እና አንድሬስ ኢንዬስታን የመሳሰሉ አስደናቂ ተጫዋቾችን አፍርቷል፡፡ እነኚህ ከዋክብት ከተጋጣሚ ቡድኖች ለሚገጥማቸው ፈተና ክህሎት፣ አስደናቂ የኳስ ቁጥጥር እና የማይዛነፍ የኳስ ቅብብልን እንደ መፍትሔ ይጠቀማሉ፡፡ ምክንያቱም የተሰሩበት መንገድ ይህ ስለሆነ፡፡


ስለ ጸሀፊው


ማርቆስ ኤሊያስ – ጋዜጠኛ እና የጨዋታ አስተላላፊ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *