በ ኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም

አዲስ አበባ – ግንቦት 07/2012 ዓ.ም – የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወርቃማ ዘመን መሪ፣ ታታሪ እና ፍጹም ሀገር ወዳድ የነበሩትን አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬን: በተወለዱ በ69 ዓመታቸው ግንቦት 07 ቀን 2008 ዓ.ም ነበር በህይዎት ያጣናቸው፡፡ እኔም የእኚህን ባለ ብዙ ገድል የሀገር ባለውለታ እና ውጤታማ አሰልጣኝ ከሰፊው የህይወት ታሪካቸው በጥቂቱ ለመቃኘት እና ለማስታወስ ሞክሪያለሁ፡፡ መልካም ንባብ!

ጥር 1939 ዓ ም ሰሜን ሸዋ፡ ተጉለት እና ቡልጋ የተወለዱት ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ፡ ገና በልጅነታቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በቀድሞው አስፋ ወሠን ት/ቤት የዘመናዊ ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ፡፡ በስፖርት ፍቅር በጠዋቱ የተለከፉት ዶ/ር ወልደመስቀል በጊዜው በትምህርት ቤቱ ይካሄዱ በነበሩ የመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ይፎካከሩ ነበር፡፡ በትምህርታቸው ገፍተው በመቀጠልም በጎርጎሮውያኑ የዘመን ቀመር ከ1964 -1970 በድጋሜ ከ1974 -1982 በአጠቃላይ ለ14 አመታት ወጣትነታቸውን ባሳለፉባት ምስራቅ አውሮፓዋቷ ሀገር ሀንጋሪ፡ በባዮሎጂ ሳይንስ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ የደረሰ ትምህርት ቀስመውባታል፡፡

ዶ/ር ወልደመስቀል ወደ ውጭ ሀገር  ለትምህርት ከማምራታቸው ከቀናት አስቀድሞ በ1964 የቶኪዮ ኦሊምፒክ በሚሳተፈው የአትሌቲክስ ቡድናችን ውስጥ በ800  እና 1500 ሜትር ሀገራቸውን ወክለው እንዲወዳደሩ ተመርጠው የነበረ ቢሆንም፤ እርሳቸው ግን ትምህርቴ ይበልጥብኛል በማለት ውድድሩን በመተው ወደ ሀንጋሪ አምርተዋል፡፡

ቆፍጣናው አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ ወደ ስልጣናው ዓለም የገቡት በኮተቤ ኮሌጅ መምህር እያሉ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሲሆን፡ በ1972ቱ የሙኒክ ኦሊምፒክ በሚሳተፈው ቡድናችን ውስጥ ዋና አሰልጣኝ ለነበሩት ሌላኛው ውጤታማ አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ምክትል በመሆን ነበር፡፡

አሰልጣኙ ከሀገረ ሀንጋሪ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በ1982 ከሰሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ፡ በስፖርት ኮሚሽን ውስጥ በከፍተኛ ባለሙያነት ያገለገሉ ሲሆን፡ ወደ አትሌቲክስ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝነት የመጡት ደግሞ የአሰልጣኝ ንጉሴ ሮባን ኅልፈት ተከትሎ በ1992 ነበር፡፡

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው ምርጥ ምርጥ አትሌቶች ጀርባ እኚህ ኮስታራ አሰልጣኝ ይገኛሉ፡፡ ከ1992 የባርሴሎና እስከ 2008 የቤጂንግ ኦሊምፒክ ድረስ ለ16 ዓመታት በዘለቀው የዋና አሰልጣኝነት ዘመናቸው፡ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያኮሯትን በተለይም የ5000 እና የ10,000 ሜትር አትሌቶችን ለድርብርብ ስኬቶች በማብቃታቸው ታሪክ ሁሌም ከፍ አድርጎ ሲዘክራቸው ይኖራል፡፡

ዶ/ር ወልደመስቀል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን እያሰለጠኑ በተሳተፉባቸው አምስት የኦሊምፒክ መድረኮች ላይ ለሀገራችን 28 ሜዳሊያዎችን አሸንፈዋል፡ (13 ወርቅ 5 ብር እና 10 ነሐስ)፡፡

ሀገር ወዳዱ፣ ስኬታማው እና ቆፍጣናው አሰልጣኝ ወልደመስቀል ኮስትሬ በህይወት እያሉ፡ በአትሌቲክሱ ዓለም ለአሰልጣኞች የሚሰጠውን ትልቁን የአለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ክብርን በ2006 እንዲሁም ከማለፋቸው አንድ አመት አስቀድሞ በተካሄደው የ2007ዓ.ም  የበጎ ሰው ሽልማት ደግሞ የዓመቱ ምርጥ የስፖርት ሰው ክብሮችን ተጎናጽፈዋል፡፡

ዶክተሩ ምንም እንኳን በአብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የሚታወቁት በስኬታማ የአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኝነታቸው  ቢሆንም፡ እርሳቸው ግን ሁለገብ የስፖርት ባለሞያ እና ለእግር ኳስም የተለዬ ፍቅር የነበራቸው፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበርን በአሰልጣኝነት፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ደግሞ በምክትል አሰልጣኝነት ማገልገላቸውን ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *