ዐቢይ ሀብታሙ – ለ ልዩ ስፖርት

በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ እየተጠቃች ያለችው ዓለማችን፡ ሰቅዞ ከያዛት ክፉ ደዌ ለመላቀቅ ብርቱ ትግል ላይ ናት። በየዕለቱ የሚወጡ መረጃዎችና ሪፖርቶችም ስጋቶቻችን እያባባሱት ይገኛሉ። ከስጋት ባለፈ ሞት የበረከተባቸው አገራት ቁጥርም ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀበ ነው። በተለይ እንደ ጣልያንና ስፔን ያሉ አገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን በCOVID-19 ሳቢያ በየዕለቱ ያጣሉ። በአንፃሩ የወረርሽኙ መነሻ ናት የምትባለው የቻይናዋ ዉኻን ግዛት በቫይረሱ የሚያዙ አዲስ ሰዎችን በተመለከተ ዜሮ መጠን ማስመዝገቧን ሰምተናል።

የዓለም ጤና ድርጅት ‘ኮሮና ወረርሽ ነው’ ሲል ያወጀው ከሳምንት በፊት ነበር። ወረርሽኙ አሁን ላይ መላ ዓለምን አዳርሷል።

በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ሰዎች የምርመራ ውጤታቸው የሚያሳየው በቫይረሱ መያዛቸውንና ቁጥራቸው በፍጥነት እያሻቀበ መኾኑን ነው። እነዚህ ዓለማቀፍዊ እውነታዎች የስጋት ደረጃዎችን በመጨመር ህዝቦችን ለድንጋጤና ፍርሃት እየዳረጉ ናቸው።

የአዕምሮ ጤናን በተመለከተም በመላው ዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በጭንቀት ብዛት ለአዕምሮ መዛባት እክሎች ተጋላጭ እየኾኑ ይገኛሉ።

የምናያቸውና የምንሰማቸው ነገሮች ደግሞ የአሉታዊ ስሜቶች መነሻና አባባሾች ናቸው።

በተለይ እንደ’ኛ የመረጃ አመራረጥና አወሳሰድ ላይ ክፍተት የሚስተዋልባቸው አገራት ደግሞ ችግሩ የበለጠ ሊንሰራፉባቸው የሚችሉባቸው ዕድሎች ሰፊ ናቸው።

በNHS ሆስፒታል ሀኪም እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ሲኒየር ዩኒቨርስቲ ሌክቸረር የኾኑት ዶክተር አሚር ካሃን ሰዎች እንዲህ ከመጠን ባለፈ የመጨነቃቸው ግንባር ቀደም ምክንያት ስለበሽታው የሚሰሟቸው ነገሮች መኾናቸውን ይገልፃሉ።

ስለቫይረሱ የሚሰሙ አንዳንድ ነገሮች እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ በመኾናቸውም ሰዎችን እያሳሳቱ ይገኛሉ።

አበው ‘ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው’ እንዲሉ፤ በዚህ ሰዓት ስለቫይረሱ ሊነገሩ ከሚገቡ ነገሮች በላይ ለጭንቀት የሚዳረጉ ወሬዎች በስፋት ይናፈሳሉ።

ማኅበረሰቡን ከሚያስገንዘቡ ይልቅ የሀሰት መረጃዎች ተበራክተዋል። የመረጃው ብዛት አይጣል ነው። አንዱ በሌላው ላይ ይደራረባል።

የመረጃዎቹን እውነተኛነትና የጥራት ደረጃ መመርመር ባለመቻላችን ከንቃት ይልቅ ድንዛዜ ውስጥ ገብተናል። ለዚህም ነው ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል የሚባለው።

መረጃዎችን መውሰድ ያለብኝ ከማን ነው? የትኞቹ መረጃዎችስ እውነት ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎች ላይ ማተኮር ይኖርብናል።

ዶክተር አሚር ሰማኋቸው ካሏቸው በርካታ ከእውነት የራቁ ነገሮች መካከል አንዱ ውኃ መጠጣትና ኮረና ቫይረስን ይመለከታል። ውኃን በየአሥራ አምስት ደቂቃዎች ልዩነት መጠጣትና በጥልቀት መተንፈስ ቫይረሱ ሳንባችሁን መጉዳቱን ለመወሰን ይረዳል የሚለው ሃሳብ አስገርሟቸዋል።

ወዲህ ደግሞ አለላችሁ ሌላ ወሬ የፈታው ታሪክ። ‘ኮረና ቫይረስ አፍሪካዊያንን አይዝም’ የሚል ምንጩ የማይታወቅ የመዘናጊያ ወሬ።

በሳምንቱ አጋማሽ ወደ ጤና ጥበቃ ቢሮ ለሥራ ጉዳይ ለመሄድ የተሳፈርኩበት ታክሲ ውስጥ የሰማሁትን ነገር ላጫውታችሁ።

ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ እድሜያቸው በግምት ሰላሳዎቹ የሚሻገር ኹለት ጎልማሶች ስለሰሞነኛው ጉዳይ ይወያያሉ። አንደኛው ለጉዳዩ አየሰጠን ያለነው ትኩረትና የጥንቃቄያችን መጠን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ሲል ባልንጀራውን ይሞግታል። የሌላኛው ሰው ምላሽ ግን ሙግቱን የማይመጥንና አመክንዮ የሌለው ነበር። ”ምን ችግር አለው አረቄና ነጭ ሽንኩርት እያለ የምን ኮረና” የሚል ነበር።

ይህ ሰው ምን ያህል ከነባራዊው አውነት በተቃራኒ ጎራ የተሰለፈ መኾኑን ፍንትው አድርጎ ያሳይ አጋጣሚ አድርጌ ወስጄዋለው። ስለአረቄ እርግጠኛ ሆኜ መናገር ባልችልም ነጭ ሽንኩርት የሚያበረክተው የጤና ጥቅሞች በርካታ መኾኑን አንድ ሁለት ብዬ መዘርዘር አይከብደኝም። ነገር ግን ጥያቄው ‘ኮረናን ለመከላከል ያለው ፋይዳ ምንድነው?’ የሚለው ነው።

አሳሳች መረጃዎች አደገኛ ናቸው። ለአዕምሮ ጤና ችግሮችም ሊያጋልጡን ይችላሉ። ለምሳሌ ከዚህ ቀደም የአዕምሮ ጤና ችግሮች ያልነበሩባቸው ሰዎች በድንገት እንቅልፋቸውን ሊያጡና መደበኛ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሊዛባባቸው ይችላል። በአንፃሩ ከዚሀ ቀደም ተጠቂ የነበሩት የከፋ ችግር ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ።

ሰሞኑን ስለ COVID-19 የሚሰሙ አንዳንዳንድ አሳሳች ወሬዎች በቫይረሱ ብጠቃ እሞት ይኾን? ራሴንና ቤተሰቤንስ ከቫይረሱ ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይኖርብኝ ይኾን? የሚሉ ጥያቄዎች በአምሮአችን ስለሚመላለሱ ጭንቀት ውስጥ ገብተናል።

ይህ ጭንቀት ደግሞ ጥቅምና ጉዳትን በቅጡ ሳንመረምር ባልተረጋገጠ ወሬ ብቻ ተነሳስተን ማስክና ግላቭ በሰልፍ እንድንገዛ አድርጎናል። አለፍ ሲልም ነጭ ሽንኩርትን በ250 ሎሚን 150 ብር በመግዛት የስግብግብ ነጋዴዎችን ኪስ እንድናደልብ አድርጎናል።

አሁን ትክክለኛውን መረጃ መምረጥ የሚገባን ወቅት ላይ እንደመገኘታችን፡ ስጋትን ከሚያባባብሱ ችግሮች ይልቅ የመፍትሔ ሃሳብች ላይ ማተኮር ይኖርብናል።

ከሁሉም በፊት የአዕምሮ ጤናችንን እንጠብቅ። ችግር ውስጥ መኾናችንን አምነን በተቻለ መጠን ከጭንቀት፡ ረብሻና ግርግሩ ወጥተን ቫይረሱ ደጃፍችንን ከመርገጡ በፊት ሊወሰዱ የሚገቡ የቅድመ መከላከል ድርጊቶች ላይ ብቻ እናተኩር።

ሰርጂካል ግላቭ ለመግዛት የመድኃኒት ቤቶችን በር በረጃጅም ሰልፎች ከማጨናነቅ ይልቅ እጆቻችንን በአግባቡ የመታጠብ፡ እና ማህበራዊ ፈቀቅታን የመተግበር ልማድን እናዳብር።

የሚበጀን ተረጋግቶ ማሰብ እንጂ ውክቢያና ጥድፊያ አይደለም። ጭንቀት ውስጥ ባለመግባት የአዕምሯችንን ጤና እንጠብቅለት። ምክንያቱም አዕምሮ ደህና ሲኾን ከጭንቀት ይልቅ መፍትሔ ስለሚሰጠን።

COVID-19 የአምሮ ጤናችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያስከትል ምን አናድርግ? የጥንቃቄ እርምጃዎቻችንስ ምን መምሰል አለባቸው?

የመረጃ (ወሬዎች) አወሳሰድን መመጠን

በ’ርግጥ ‘ዓለም እንዴት ሰነበተች?’ ብሎ መጠየቅ ሰህተት አይደለም። ራስን በወቅታዊ መረጃ ማብቃትም እንደዛው። ስህተት የሚኾነው የተገኘውን መረጃ ሁሉ እንደወረደ ማጋበስ ሲሆን ነው እንጂ።

እኛ በመረጃ አወሳሰድ ረገድ ብዙ ይቀረናል፡ ለዚህም ነው ብስሉን ከጥሬ፣ እውነትን ከውሸት አንጥሮ መለየት ያስፈልጋል የምንለው። ለዚህ ደግሞ መረጃዎችን ከታማኝ የወሬ ምንጮች ብቻ መከታተል ተመራጭ ነው።

ሰሞነኛውን የኮረና ጉዳይ በተመለከተ ተዓማኒ ከኾኑ ብዙሃን መገናኛዎች፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ቢሮ ፣ የአለም ጤና ድርጅትትን እንዲሁም ከዋና ዋና የመንግስት አካላት በተለያዩ መንገዶች በየጊዜው የሚለቋቁ ቫይረሱን የተመለከቱ መረጃዎችንና ሪፖርቶችን በመከታተል ካልተገቡ የሀሰት ወሬዎች በመራቅ አዕምሯችንን ከስጋትና ጭንቀት ለማራቅ እንችላለን።

ለኮሮና ቫይረስ የባህል መድሃኒት በኢትዮጵያ ተገኝቶለታል ተብሎ በማህበራዊ ሚድያ የምወራው ሃሰት ነው::————————–ከኮሮናቫይረስ መከላከል ጋር በተገናኘ…

Posted by Ministry of Health,Ethiopia on Thursday, March 19, 2020

የማኅበራዊ ትስስር ገፆች በተለይም በፌስቡከና ቴሌግራም የሚለቀቁ መረጃዎችን በተመለከተ ጥራት በጎደላቸው የሀሰት ወሬዎች ሰለባ ላለመኾን እንደ ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት ያሉ ጥንቁቅ የኦንላይን መረጃ አቀባዮችን መከታተል ይመከራል።

ራሳችንን ከሀሰት መረጃዎች መጠበቃችን ደግሞ አዕምሯችን ፋታ ስለሚያገኝ ለሌሎች ነገሮች ቦታ እንዲኖረው እናደርገዋለን።

"የኮሮና ቫይረስ በሽታ ዘር፣ ቀለም እና ሃይማኖት ስለማይለይ እንዲሁም ከየትኛውም ሀገር እና እና ዜግነት ጋር ስለማይገናኝ በመተባበር እና በፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት መከላከል ይገባል። በሽታው በሁላችንም ላይ የመጣ የጋራ ፈተና ነው፤ በጋራ እንዋጋዋለን፤ እናሽንፈዋለንም"— የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ

Posted by Elias Meseret on Thursday, March 19, 2020

አንዳንድ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ (በተለይ ለስፖርተኞች)

በኮረና ቫይረስ ሳቢያ በአሁኑ ወቅት ሁሉም የቡድን የስፖርት ውደድሮች በመላው ዓለም መቋረጣቸው ይታወቃል። ስፖርተኞች ከሚወዷቸው ሙያቸው ለጊዜውም ቢኾን መራቃቸውና በአንድ ሥፍራ መወሰናቸው ምናልባት እንደ ድብርት ያሉ አሉታዋዊ ስሜቶች ሊፈጥርባቸው ይችላል። ነገር ግን አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ከነዚህ ጥሩ ያልሆኑ ስሜቶች ነፃ መሆን ይችላሉ። እንቅስቃሴ ለማድረግ ጂም ወይም የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች መሄድ የግድ አይደለም፤ አንድ ሰው ባለበት ቦታ ቀለል ያሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ አዕምሮን ከውጥረት ማላቀቅ ይችላል።

ከሰሞኑ የታዋቂ ስፖርተኞች የማኅበራዊ ትስስር ገፆች ላይ አየተለጠፈች ያለች ጽሑፍ አለች። ‘Stay home stay safe’ “ከቤታችሁ ባለመውጣት ጤንነታችሁን ጠብቁ” እንደማለት ነው፡ ቆንጆ አባባል ናት። እንቅስቃሴ የለመደ እግርን በቤት ውስጥ ሰብስቦ ማስቀመጥ ቢከብድም ለጊዜው ግን ጥሩ መፍትሔ ነው። በተለይ Stay home stay safe ቀለል ባሉ አካላዊ እንቅስቃሴዎች ቢታጀብ ደግሞ እንደ መልዕክቱ ውጤቱም የበለጠ አመርቂ የመሆን እድሉ ሰፊ ይኾናል።

ንፁህ አየር ለማግኘት መሞከር

ለኮሮና አጋላጭ ያልኾኑ ንፁህ አየር መቀበያ ቦታዎች ከተገኙ እግርን ለማፍታታት ወጣ ማለቱ አይከፋም። አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ቫይረሱ አየር እንደልብ በማይንቀሳቀስባቸው ቦታዎች ውስጥ ከፍ ያለ የመዛመት እድል እንዳለው በመጠቆም ላይ ይገኛሉ።

በተጨማሪም እንቅስቄሴን ማድረግ ቤት ውስጥ ከመቀመጥ ብዛት የሚፈጠሩ የድብርትና ጭንቀት ስሜቶችንም ያርቃሉ። ለምሳሌ ክፍት ፓርኮችና አረንጓዴ ስፍራዎች በህዝብ ከተፋፈጉ ሥፍራዎች አንፃር የኮረና ተጋላጭነታቸው አነስተኛ ነው። ነገር ግን ወደነዚህም ቦታዎች ቢኾን የሰዎች እንቅስቃሴዎች ቀዝቀዝ የሚሉባቸቸውን ሰዓታት መምረጥ ያስፈልጋል። ዓላማውም አዕምሮን ዘና እያደረጉ ከመጥፎ ስሜት ለማላቀቅ እስከኾነ ድረስ ቢቻል ስልኮቻችን አለመነካካት ተመራጭ ነው።

የጭንቀት ጊዜያትን መቀነስ

‘ኮሮና ቫይረስ’ የሚል ነገር በአዕምሮአችን ውስጥ ደጋግሞ አየመጣ ዕረፍት እያሳጣን ሊኾን ይችላል። ነገር ግን ችግሩን በማሰብ ብቻ ከምናሳልፈው ጊዜ በላይ መፍትሔው ላይ ማተኮር የአዕምሮ ጤናን እንደሚጠብቅልን ማወቅ ይኖብናል።


ስለ ጸሀፊው


ዐቢይ ሐብታሙ

መምህር እና ጋዜጠኛ

BSE Degree – በኅብረተሰብ ጤና

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *