በዐቢይ ሐብታሙ – ለልዩ ስፖርት

ባት (CALF) ምንድን ነው?

ስርወ ቃሉ ከላቲን ሲመዘዝ ሱራ (SURA) ነው። በሰውነት ክፍሎች ጥናት (Anatomy) መሰረት ከጉልበት በታች ያለው የእግር ጀርባ ክፍል ባት(CALF) ይባላል።

ባት ከሁለት ጡንቻዎች የተገነባ ነው። እነዚህ ጡንቻዎች The Gastroncnemius እና The Soleus ይባላሉ።

Gastroncnemius ባት ላይ ሲታይ የዳይመንድ ቅርፅ ያለው ትልቁ ጡንቻ ሲኾን Soleus ደግሞ ትንሹ ጡንቻ ነው። አቀማመጡም ጠፍጠፍ ብሎ ከትልቁ ጡንቻ ሥር ነው።

የባት ጡንቻዎች ከእግር ኋላ ክፍል ጡንቻዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። እነዚህ ሁለት ታላላቅ ጡንቻዎች ከተረከዝ (Heel) ጋር አኪለስ በሚባል የሰውነት ጅማት (Achilles tendon) የተያያዙ ሲኾን ሌሎቹ በርካታ አነስተኛ ጡንቻዎች ደግሞ ከጉልበት(Knee)፣ ቁርጭምሚት (Ankle) እና ከእግር ጣቶች (Toes) ጋር በታታላቅ የሰውነት ጅማቶች ተወዳጅተዋል።

የባት ጡንቻ ጉዳቶች ምንነት

Gasteocnemis እና Soleus ከመጠን በላይ ሲሳሳቡ ሊጎዱ የሚችሉ ጡንቻዎች ናቸው። የባት ጡንቻ ጉዳት የሚባለው በቤት ውስጥ በእንክብካቤ ሊድኑ ከሚችሉት እስከ የባለሙያ እርዳታ የሚሹ የመቀደድና የመሳሳብ ጉዳቶች ድረስ ያሉትን ያጠቃልላል።

የባት ጡንቻ ጉዳት መንስኤዎች

ነጥብ 1

የባት ጡንቻ ጉዳት የሚከሰተው ፍጥነትንና ድንገት እግርን ከመሬት እየነቀሉ መጫወት በሚጠይቁ እንደ እግር ኳስ፣ የሜዳ ቴኒስና ቤዝ ቦል ያሉ ስፖርቶች ላይ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ቀለል ያሉ ሩጫዎችም እክል ሊያስከትሉ የሚችሉባቸው እድሎች ይኖራሉ።

ነጥብ 2

ድንገተኛ እንቅስቃሴዎችና ከመጠን ያለፉ ማሳሳቦች (Over streching) የባት ጡንቻዎችን ሊወጣጥሩ ይችላሉ።

ነጥብ 3

የባት ጡንቻ ጉዳቶች አሳሳቢነት የሚወሰኑት በጉዳቱ መጠን (level of Sevierity) ነው። ለምሳሌ የጡንቻ መተርተር ወይም መቀደድ ከኾነ ከጉልበት በታች ባለው የእግር ክፍል ላይ የመጎተት ዓይነት ስሜትና ፋታ አልባ ህመም (በተለምዶ አኘከኝ እንደሚባለው) ሲያስከትሉ፣ ኮስተር ያሉ ናቸው የሚባልላቸው የባት ጡንቻ መቀደዶች ግን የበረታ ህመም ያስከትላሉ። በዚህ ሳቢያ መራመድ እንኳ ብርቅ ሊኾን ይችላል።

የባት ጠንቻ ጉዳት ዓይነቶች

1.የባት ጡንቻ መተርተር (Cald Muscle Strain)

ከአነስተኛ ህመም እስከ ከፍተኛ ህመም እንዲሁም የባት ጡንቻዎች ሙሉ ለሙሉ መሰንጠቅ ድረስ ይከሰታል። በተጨማሪም አንዳንድ የባት ደም ስሮች ይተረተራሉ።

2. የባት ጡንቻ መወጠር፣ መሳብ ( Pulled Calf Muscle)

መወጠር ወይም መሳብ የባት ጡንቻ ከመጠን ያለፈ መዘርጋትን ያመለክታል

3. የባት ጡንቻ መቀደድ (Calf Muscle Tear)

ሁሉም የባት ጡንቻ መወጠሮች የአንዳንድ ደምስሮች መቀደድን ያስከትላሉ። አለፍ ሲልም የባት ጡንቻ ከፊል አሊያም ሙሉ ለሙሉ ሊያስከትሉ ይችላሉ።

3. የባት ጡንቻ መፍረስ ወይም መፈንዳት (Calf Muscle Rupture)

የጡንቻዎች ሙሉ ለሙሉ መቀደድ ፅኑ ህመምን ከማስከተሉ ባሻገር መራመድ መቻል ፈተና ይኾናል። የጡንቻ መፍረስ የሚባለው ደግሞ በቀላሉ በዓይን ሊታይ በሚችል መልኩ የአምፖል ወይም ክብ ቅርፅ ቆዳ ላይ ሲፈጥር ነው።

4. የባት ጡንቻ ካንሰር (Cancer)

የባት ጡንቻ ካንሰር የተለመደ ነው። ካንሰር ማለት ደግሞ የህዋሶች ጤናማ ያልኾነ አድገት( Abnormal growth of cells) ነው። ጡንቻዎች ማበጥ ሲጀምሩ ሳክሮማ (Sacroma) ወደ ተለያዩ የባት ጡንቻዎች ሲሰራጩ ደግሞ ሜታስታሲስ (Metastasis) ይባላሉ።

ማስታወሻ፡ ከላይ ከተዘረዘሩት የባት ጡንቻ ሁኔታዎች በተጨማሪ እንደ Myositis እና የጡንቻ መቆጣት(Inflammation) ያሉትም ተጠቃሽ ናቸው።

ምርመራዎች፣ ህክምና እንዲሁም የቤት ውስጥ ክብካቤዎች (Tests, Treatments & Home Cares)

የባት ጡንቻ ምርመራዎች (Calf Muscle Tests)

ኤም አር አይ ስካን (MRI – Magnetic Resonance Image Scan)

MRI Scan ኃይል ያለው መግነጢስ(Magnet) ስለሚጠቀም ኮምፒውተር ላይ ስለ ባት ጡንቻ እንዲሁም ሌሎች የእግር መዋቅሮች ዝርዝር የምስል መረጃዎችን ይፈጥራል።

CT Scan (Computed Tomography)

CT Scan በርካታ ጨረሮችን ይጠቀማል። ኮምፒውተር ደግሞ እነዚህን ጨረሮች ወደ ባት ጡንቻና ሌሎች የእግር መዋቅራዊ ምስሎች ያቀናብራቸዋል።

አልትራሳውንድ (Ultrasound)

ቆዳ ላይ የሚቀመጠው መሳሪያ የባት ጡንቻዎች፣ ጅማቶችና የእግር መዋቅሮች ላይ ከፍተኛ ፍሪኩዌንሲ ያላቸውን የድምፅ ሞገዶችን ( Sound waves) ያነጥራል። ከዚያም ሲግናሎቹ የቪዲዮ ስክሪኖች ላይ ወደ ምስልነት በመለወጥ ምርመራ ለሚያደርገው ባለሙያ በሰውነት ውስጥ ያሉ መዋቅሮችን እንዲመለከት ያደርገዋል።

የባት ጡንቻ ህክምናዎች (Calf Muscle Treatments)

PRICE Theraphy

P – Protecting (መከላከል)
R – Resting (ዕረፍት)
I – apply ice(በረዶ)
C – Compression (ባንዴጅ/ፋሻ)
E – Elevation (እግርን መስቀል)

ቀዶ ጥገና (Calf muscle injury)

ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው ሙሉ በሙሉ ለተቀደዱ ጡንቻዎች ለማከም እንዲሁም ሳክሮማን ለማስወገድ ነው።

ኬሞቴራፒ (Chemotheraphy)

የካንሰሩን እድገት ዝግ የሚያደርጉ መድሐኒቶች ሊሰጡ ይችላሉ። እነዚህ መድሐኒቶች ሳክሮማን አሊያም የባት ጡንቻዎችን የሚጎዱ ካንሰሮችን ያስታግሳሉ።

Antibiotics

አንቲባዮቲኮች ባክቴሪያዎችን ይገድላሉ። በተጨማሪም አንዳንድ የማዮስቶሲስ ሁኔታዎችን ለማከም ይረዳሉ።

Physical Therapy

ለአንዳንድ የባት ጡንቻ መድከም ወይም ጉዳት በአካል ብቃት ቴራፒስት መሪነትና ክትትል የሚደረጉ አካላዊ እንቅስቃሴ መርሃ ግብሮች የጡንቻ ጥንካሬንና መደበኛ ተግባርን ዳግም ለመመለስ ይረዳሉ።

የባት ጡንቻ ጉዳትን በቤት ውስጥ የማከሚያ መንገዶች

አብዛኞቹ የባት ጡንቻ መተርተር አሊያም መበጠስ እክሎች በቤት ውስጥ በሚደረጉ እንክብካቤዎች ሊሽሩ ይችላሉ።

፨ የተጎዳውን እግር ለአንድ ወይም ሁለት ቀናት ማሳረፍ።

፨ የበረዶ እሽግ ወይም እርጥብ ፎጣ የተጎዳው አካል ላይ በየሁለት ሰዓታት ልዩነት ከአስር እስከ ሃያ ደቂቃዎች ርዝማኔ ማድረግ እብጠትን ያጎላል። ይህን ነገር ዘወትር ማለዳ ቢያንስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት መጠቀም፦ የተሻለ ውጤት ያመጣል። ይኹንና በበረዶ እሽጉና ቆዳ መካከል ቀጠን ያለ እራፊ ጨርቅ ማድረግ ተመራጭ ነው።

ቅድመ መከላከል (Prevention)

አብዛኞቹ የባት ጡንቻ ጉዳቶች በስፖርታዊ ሂደቶች ወቅት የሚከሰቱ ናቸው። ቅድመ መከላከል ሁሌጊዜ ተመራጭ ነው። በተለይ ቀደም ብሎ እክሉ ገጥሞት የሚያውቅ ስፖርተኛ ልዩ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅበታል።

አካላዊ እንቅስቃሴዎች ሲከናወኑ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች

፨ ከስፖርታዊ ጨዋታዎች አሊያም ውድድሮች በፊት ሰውነትን እያፍታቱ ማማሟቅ (Stretch & Warm up)፣ እንደ እርምጃና ብስክሌት መጋለብ (ጂምን ጨምሮ) ያሉ እንቅስቃሴዎችን ቢያንስ ለአምስትና ከዚያ በላይ ደቂቃዎች ማከናወን።

፨ ጠንካራ ከኾኑ ልምምዶች ወይም አካላዊ እንቅስቃሴዎች በኋላ ቢያንስ ለአምስት ደቂቃዎች ቀለል ያሉ የማሳሳብ ተግባራት፣ የዝግታ እርምጃዎችና የሶምሶማ ሩጫዎችን በማከናወን ሰውነትን ማቀዝቀዝ (Cool down)

፨ በብቃት መወጣት የሚከብዱ ስፖርታዊ ጨዋታዎችና ወድድሮች እንዲሁም ጠንካራ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማስወገድ።

ቸር ያሰንብታችሁ!


ስለ ጸሀፊው


ዐቢይ ሐብታሙ 

መምህር እና ጋዜጠኛ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *