ፎቶ፡ ቲክቫህ ስፖርት

በ ብሩክ አብሪና

ከውድድር ዓመቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የመቐለ ሰባ እንደርታ እና የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ በትግራይ አለምአቀፍ ስታድየም የተከናወነ ሲሆን፡ ፋሲል ከነማ በሙጂብ ቃሲም ሁለት ግቦች ታግዞ መቐለን በሜዳው በማሸነፍ ያልተጠበቀ ድል ተቀዳጅቷል።

ሁለቱም ቡድኖች ከዚህ ቀደም ከሚታወቁበት ወይንም ብዙ ጊዜ ይዘውት ከሚገቡት የጨዋታ መንገድ እና አጨዋወት በተለየ መልኩ ባካሄዱበት በዚህ ጨዋታ ባለሜዳው ቡድን ጅማ ላይ ሽንፈት ካስተናገደው ቋሚ 11 ውስጥ መጠነኛ ለውጥ ያደረጉ ሲሆን፡ ተከላካይ ክፍል ላይ ኤድዋርድን በቢያድግልኝ፡
ታፈሰን በአስናቀ፡ አሸናፊን በስዩም እንዲሁም አጥቂው ክብሮምን በኦኪኪ በመተካት ነበር ወደ ሜዳ የገቡት።

ፋሲሎች በተቃራኒው ይህ ነው የሚባል የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ከተለመደው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይልቅ ተጫዋቾቹ አስልጣኙ ለጨዋታው ለመረጡት ታክቲክ ተገዢ የሆኑበትን አጨዋወት የተገበሩት ነበር።

የጨዋታ አቀራረቦች

አሰልጣኝ ገብረመድህን በዚህ ጨዋታ ቡድናቸው ከዚህ ቀደም በሜዳው ከሚጠቀመው የ4-4-2 ወይንም የቀጥተኛ አጨዋወት ይልቅ ወደ 4-3-3 በመለወጥ ይበልጥ በመሀል ሜዳ ያለውን የተጋጣሚውን ጥንካሬ ለመቋቋም ታሳቢ ያደረገ አቀራረብ ይዘው የገቡ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ቡድኑ እንደየ አሰፈላጊነቱ ሊለዋወጥ የሚችልበትን አሰላለፍ ነበር የተጠቀሙት።

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ምንም እንኳን ቡድናቸው በ4-3-3 አቀራረብ ጨዋታውን የጀመረ ቢሆንም ነገር ግን የሁለቱ የመስመር አጥቂዎች የማጥቃት እንቅስቃሴያ የተገደበ እና ቡድኑ በሁለተኛው የሜዳ ክፍል የሚነጠቁ ኳሶችን በመጠቀም ግቦችን ለማስቆጠር ሲሞክር የተመለከትንበት ነበር። በዚህም ቡድኑ ከወጥነት ይልቅ ተለዋዋጭ የሆነ የጨዋታ አተገባበርን ምርጫው አድርጎ እንደገባ ለመመልከት ችለናል።


በጨዋታው የፋሲል ወደ ኋላ አፈግፍጎ መጫወትን ተከትሎ የመቐለ ተከላካዮች ኳሱን ከኋላ መስርቶ ለመውጣት ብዙም አልተቸገሩም ነበር። ነገር ግን ቡድኑ ጎል ያስተናገደበት መንገድ ልምድ ካላቸው ተከላካዮች የማይጠበቅ አይነት ስህተት በመስራታቸው ሲሆን በተለይም በመሀል ተከላካዮቹ በአሌክስ እና በቢያድግልኝ መካከል የነበረው ሰፊ ርቀት ጎል አስቆጣሪው ሙጅብ ቃሲምን ከኳስ ጋር ለብቻው ከግብ ጠባቂያቸው ጋር እንዲገናኝቨ እድል ሊፈጥርለት ችሏል።

ለምሳሌ የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር ፋሲሎች ከመቀለ የመጀመሪያው ግራ የሜዳ ክፍል ወደ 16ከ50 ያሻሙትን ኳስ ሽመክት ያገኘበት እና ተረጋግቶ በደረቱ ያበረደበት መንገድ በሁለቱ ተከላካዮች በኩል ያለውን ሰፊ የቦታ እና ንግግር ክፍተት ያሳዬ ነበር። በሁለተኛው ግብ ላይም ቢሆን ምንም እንኳን የኳሱ መነሻ ከመሀል ሜዳ በሄኖክ እና በአሚኑ አለመግባባት የተፈጠረ ቢሆንም፡ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች በሱራፌል እንቅስቃሴ የተቆረጡቀት መንገድ አስገራሚ ሲሆን ይህም ሁለቱም ወደ ሱራፌል እንቅስቃሴ በመሳባቸው ምክንያት ለሙጂብ በድጋሚ ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት ለብቻው እንዲገኝ አድርጎታል። ምንም እንኳን ተጫዋቹ ያገኛቸውን እድሎች መጠቀሙ ትልቁ ልዩነት ቢሆንም የተከላካዮቹን ስህተት ግን በሚገባ ያሳዬ ነበር።

መቐለዎች ከመከላከል ባለፈ ወደ ማጥቃት ሽግግር በሚያደርጉበት ወቅትም በራሳቸው የሜዳ ክፍል ሆነው የሚጠበቋቸውን የፋሲል ተጫዋቾችን በቀላሉ ሰብረው ለመግባት ተችግረው ነበር። ከሁለተኛው የሜዳ ክፍል እና እንደዚሁም ከመስመር ከሚሻገሩ ኳሶች በተጨማሪም በአንዳንድ አጋጣሚዎች በቀጥታ ከግብ ጠባቂው በሚላኩ ኳሶችን ለማጥቃት ሲሞክሩ የነበረ ሲሆን ይህም በቀላሉ ለፋሲል ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮቹ ምቹ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በሂደቱም በጣም ውጤታማ ለነበረው የፋሲል ከነማ ታክቲካል ጨዋታ እጅ ሰጥተው እንዲወጡ አድርጓቸዋል።

ለባለሜዳዎቹ የጨዋታው ሁነኛ ነጥብ ቀያሪ ክስተት የነበረው አጥቂው አማኑኤል ገብረሚካኤል የተገኘችዋን ፍጹም ቅጣት ምት ወደ ግብነት መቀየር አልመቻሉ ነበር።

ፋሲሎች ኳሱን በሚያገኙበት አጋጣሚ በፍጥነት ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ በ4-3-3 እንደዚሁም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ደግሞ ወደ 4-4-1-1 በመለወጥ ሲጫወቱ ተመልክተናል።

ቡድኑ በሁለቱም የጨዋታ መንገድ ግብ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፡ የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር በ4-3-3 ሶስቱም አጥቂዎቻቸወ በእንቅሰቃሴው የተሳተፉበት ነበር፣ ሁለተኛዋ ግብ ደግሞ ሁለቱም የመስመር አጥቂዎች ሽመክት እና ኢዙ ወደ መከለከል በተመለሱበት እና ሱራፌል ከሙጂብ ጀርባ በነበረበት አጋጣሚ የተቆጠረች ነበረች። በዚህ ጨዋታ ነፃ ሚና የተሰጠው ሱራፌል ዳኛቸው በተለዋዋጭ የቦታ አጠቃቀሙ በፈለገው መልኩ ለመንቀሳስ ችሏል።

ፋሲል ከዚህ ቀደም ከሚታወቅበት የመስመር እና የመሀል ለመሀል (ከሱራፌል እና ከበዛብህ) ከሚነሳው የማጥቃት እንቅስቃሴው በመቐለ የመከላከል ባህሪ ያላቸው አማካዮች መብዛት ምክንያት የተገደበ መሆኑ እንዱሁም ቡድኑም ከሜዳው ውጭ ያለውን አጨዋወቱን በመቀየሩ፡ ውጤት ላይ በማተኮሩ እና ይበልጥ መከላከልን ተቀዳሚ ምርጫው በማድረጉ የከዚህ ቀደሙን ፋሲል ሜዳ ላይ አልተመለከትነውም።

በአጠቃላይ ፋሲሎች ለአሰልጣኙ ታክቲክ በጣም ተገዢ በነበሩበት ጨዋታ ያገኟቸውን አጋጣሚዎች በሚገባ በመጠቀም አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ነገር ግን በተለይም ሁለት ተጫዋቾች (ሱራፌል እና ሽመክት) ያሳዩት ያልተገባ ባህሪ ሊታረም እንደሚገባው ሳልጠቁም ለማለፍ አልፈልግም። በተለይም ሱራፌል ዳኛቸው በጨዋታው ቀይ ካርድ አለመመልከቱ በጣም ዕድለኛ የሚያስብለው ሲሆን እሱም ጥፋቱን በማመን ተመልካቹን በዕረፍት ሰዓት ይቅርታ የጠየቀበት መንገድ የሚያስመሰግነው ነው፤ ሽመክት ጉግሳም ቢሆን ከተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ጋር የነበረው አለመግባባት እና አላስፈላጊ ሰዓት የማባካን እና ተጫዋቾቹ ላይ የተመለከትኳቸው የጨዋታውን መንፈስ የሚቀይሩ ሌሎች እንቅስቃሴዎች መታረም አለባቸው ብዬ አምናለው።

የኔ የጨዋታው ምርጥ ተጫዋቾች

ከመቐለ ሰባ እንደርታ – ዳንኤል ደምሱ

ከወትሮ በጣም በተለየ መልኩ ወደማጥቃት እንቅስቃሴ ተስቦ የጫወተው ዳንኤል ሁለት ቀጥተኛ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻለ ሲሆን ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ላይም ተሳትፎ አድርጓል።

ከፋሲል ከነማ – ዳንኤል ሳማኪ

በጨዋታው አምስት ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን ማዳን የቻለ ሲሆን በተለይም የኦኪኪ የግምባር ኳስ እንደዚሁም የአሸናፊ እና የአማኑኤልን መሬትለመሬት የተመቱ ኳሶች በማዳን ለቡድኑ ማሸነፍ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል።

ሙጂብ ቃሲም

ከየትኛውም ጊዜ በላይ ምርጥ የውድድር አመትን እያሳለፈ የሚገኘው እና በ13 ግቦች ሊጉን በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ የሚገኘው ሙጂብ፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኛቸውን አጋጣሚዎች በሚገባ በመጠቀም የጨዋታውን ሁለቱንም ጎሎች ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፡ በተጨማሪም በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑን በመከላከሉ ረገድ በማገዝም የተዋጣለት ነበር ።

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *