በ – ብሩክ አብሪና

41ኛው የሸገር ደርቢ ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም መከናወኑና ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 1ለ0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። እኔም ከጨዋታው ውጤት ባሻገር በሜዳ ላይ የነበረውን የሁለቱን ቡድኖች ታክቲካዊ አቀራረብ፡ ጠንካራ እና ደካማ ጎናቸውን እንዲሁም ጥሩ የተንቀሳቀሱ ተጫዋቾችን ለማየት እሞክራለሁ።

ሁለቱ ቡድኖች በተለያየ የጨዋታ አቀራረብ ማለትም ኢትዮጵያ ቡና ኳስን በእግሩ ስር ብዙ በማቆየት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በቀጥታ በሚጣሉ ኳሶች ለመጫወት ወደ ሜዳ የገቡበት እና ለብዙዎች ተገማች የነበረ እንቅስቃሴን ያስመለከተ ጨዋታ ነበር።

በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና በተለመደው 4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን አሰልጣኝ ካሳዬ ከወልዋሎ ጋር ነጥብ ከተጋራው ቡድናቸው አለምአንተን አሳርፈው ታፈስን ወደ ቋሚነት ያመጡት ሲሆን፡ የአማኑኤል ከረዥም ጊዜ በኋላ ወደ የአማካይ ተከላካይነት ቦታው ተመልሶ መሰለፍ ቡድኑ ይበልጥ የማጥቃት ባህሪይ ያላቸውን የአማካይ ክፍል ተጫዋች እንዲኖረው ያደረገ ሲሆን፤ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ባህርዳርን ከአሸነፈው ቋሚ 11ውስጥ በአስቻለው ታመነ እና በአብዱልከሪም ምትክ ደስታ ደሙ እና ያብስራ ተስፋዬን በመተካት በ4-2-3-1 አሰላለፍ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት ።

የጨዋታው ታክቲካዊ ዳሰሳ

ቡናዎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም የሆነ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ለመውሰድ ያልተቸገሩ ሲሆን በተለይም ደግሞ የጊዮርጊስ ደካማ የሆነ የጨዋታ ሀሳብ እና የላላ የሜዳ ላይ የቅንጅት እንቅስቃሴ የተሻለ ነፃነትን ሰጥቷቸዋል።

በዚህ ጨዋታ ግን ቡድኑ በጣም በጣት የሚቆጠሩ መልሶ ማጥቃቶች እና ረዣዥም ኳሶችን የተመለከትን ሲሆን ቡድኑ ኳሱን በነፃነት ከመቀባበል ባለፈ የቅብብሎሹ ጥራትም ከወትሮ የተሻለ የነበረ ሲሆን በጨዋታው በተለይ የሁለቱ የመስመር ተከላካዮች አህመድ ረሺድ እና አስራት ቱንጆ የነበራቸው የጨዋታ አረዳድ ትክክለኝነት የጎላ ነበር። በተለይም ቡድኑ በሁለተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የቁጥር ብልጫ እንዲኖረው በማድረግ የጊዮርጊስን የመሀል ክፍል በቁጥር እጥፍ ሆነው እንዲያገኙት በማድረግ በኩል ተሳክቶላቸዋል።

እዚህ ጋር በሁለተኛው የመጫወቻ ቦታ ላይ ጊዮርጊሶች በሙሉአለም እና በሀይደር የተጫወቱ ሲሆን፡ ሁለቱም በመሰረታዊ የኳስ ችሎታቸው የሚታሙ ባይሆኑም ኳሱን ለመንጠቅ እና መልሶ በሁለተኛው ሜዳ ለማስጀመር ሲደፍሩ አልተመለከትንም፤ ለዚህ ደግም ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ይበልጥ አፈግፍገው መጫወታቸው እና በተቃራኒው ሁለቱ የመስር አጥቂዎች(አቤል ያለው እና ጋዲሳ መብራቴ) እንቅስቃሴ ከሜዳው ሁለተኛ ክፍል እስከሜዳው ሶስተኛ ክፍል ከመሆኑ ባሻገር በጣም በተገደብ አጨዋወት ከእራሳቸው 16 ከሀምሳ ጠርዝ እስከ ቡና 16ከሀምሳ ጠርዝ ብቻ የነበረ መሆኑ፤ እንዲሁም በ10ቁጥር ነፃ ሚና የተሰጠው ያብሳራ ደግም በአማኑኤል ማርክ መደረጉና ኳስ እግሩ ላይ ለማቆየት መቸገሩ ይበልጥ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡናዎች የተሻለ ሙከራም እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል።

በተለይም ሙከራዎቹን ያደረጉት በፈለጉበት መልኩ ከመስመር ተከላካዮች እና ከአማካይ ክፍሉ መሬት ለመሬት ከተሰነጠቁ ኳሶች መሆናቸው ይበልጥ ቡድኑን የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ ምቹ አጋጣሚዎችን ማግኘት ከቻለ ማድረግ እንደሚችል የታየበት ነበር።

በተጨማሪም ከኳስ ጋር ምቾት የሚሰማው የተከላካይ ክፍሉ መግባባት ደግሞ ባለፉት ጊዜያት ስህተት ሲሰራ ለነበረው ክፍል ይበልጥ ጥሩ መሻሻሎችን እያሳዬ እንደሆነ ማሳያ ነው።

በመጀሪያው አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡና ደካማው ጎን የአጥቂው ክፍል ሲሆን፡ የኳስ ብልጫን እንዲወስድ በማድረግ በኩል ጥሩ ቢሆኑም ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም እና በግልም ተከላካዮችን ለመፈተን ያደረጉት እንቅስቃሴ ደካማ ነበር።

በቴክኒኩ በኩል ብዙም ችግር የሌለበት ሚኪያስ ከተደጋጋሚ ጉዳቱ መነሻ በሚመስል መልኩ የተገደበ እንቅሰቃሴ ብቻ ሲያደርግ ተመልክተናል፤ ባለፉት ጨዋታዎች ጥሩ የነበረው ሀብታሙም በተለይ ሰብሮ በመግባት በኩል እንደወትሮ አልነበረም፣ እንዳለም ከቦታ አያያዝ ጀምሮ በሰው ለሰው መከላከል በፍሪምፖንግ መያዙ የሚታወስ ሲሆን በጨዋታው የተወሰኑ አጋጣሚዎች ስህተት ሲሰራ ለነበረው ምንተስኖት በነፃነት ወደ ጨዋታው እንዲገባ አድርጎታል።

በጊዮርጊስ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተለይ በሁለተኛው የሜዳ ክፍል የነበረው ድክመት እና ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ለመግባት የሚያደርገው ሽግግር ከወትሮው ደካማ ከመሆኑ ባለፈ ፡ በዚህ የጨዋታ ክፍለጊዜ ከተፈፀሙ ጥፋቶች አብዛኛውን የፈፀሙት ከወገብ በላይ ያሉ ተጫዋቾች መሆናቸው ደግሞ ምን ያህል በሰው ሜዳ ላይ በነፃነት ለመንቀሳቀስ እንደተቸገሩ እና የቡናን ከኋላ መስርቶ ለመውጣት የሚደረግ እንቅስቃሴን ማቋረጥ አለመቻላቸውን የሚያሳይ ሲሆን ቅድም ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በተለይ ጋዲሳ እና አቤል ሁለቱም አንዳንድ ግዜ ብቻ ነው ከመስመር ወደ መሀል ሰብረው ለመግባት የቻሉት።

አቤል ለጌታነህ ያቀበለው እና ጌታነህ አንግል የገጨበት አጋጣሚ እንዳሁም ጋዲሳ ከደስታ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል የገቡበት አጋጣሚ ላይ ብቻ ነበር በማጥቃት ሽግግር ላይ የተመለከትናቸው። በዚህ እንቅስቃሴ በሶስተኛው ሜዳ ኳስ ሲጠብቅ የነበረው ጌታነህ በግልፅ ደስተኛ እንዳልሆነ የተመለከትንበት የሰውነት እንቅስቃሴን ያሳዬን ሲሆን፡ የያብስራ እንቅስቃሴም ቢሆን ሁለቱ የመስር አጥቂዎችም ሆኑ የመስመር ተከላካዮች ኳስ ለመቀበል አማራጭ ሆነው ብቅ አለማለታቸው ከሁለቱ 6 ቁጥር እና እንዲሁም ከጌታነህ ጋር የነበረው ግንኙነት ውጤታማ ለመሆን አልቻለም።

በአጠቃላይ የመጀመሪያው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ የተጋጣሚው ክፍተቶች ተጨምረውበትም ቢሆን በቡና በኩል ብዙ መልካም ነገሮች የነበሩበት፤ ሲሆን በጊዮርጊስ በኩል ደግሞ በሁሉም ረገድ ደካማ የሚባል እንቅስቃሴን ነበር የተመለከትነው።

የጨዋታው ሁለተኛው አጋማሽ የተለየ መልክ የነበረው ሲሆን፡ የዕረፍቱን ደቂቃ ጊዮርጊሶች በሚገባ የጨዋታ ለውጥ ስለሚያመጡበት መንገድ የተመካከሩበት እና የጨዋታውን እንቅስቃሴ የሚለውጥ ሀሳብ ይዘው የገቡበት እንደዚሁም ቡናዎች በጀመሩት መንገድ ለመጨረስ እና በጨዋታው ከመጀመሪያው አጋማሽ የቀጠለ እንቅሰቃሴ ይዘው የገቡበት ነበር።

ጊዮርጊሶች ተዳክሞ የነበረውን የሁለተኛ ሜዳ ክፍል እንቅስቃሴያቸውን በማረም በተለይም የአቤል እና ጋዲሳን ብቃት ከየአብስራ ጋር የተጠበቀውን ጥምረት ለማምጣት ሞክረዋል።

በጨዋታው የተሻለ መነሳሳት ላይ የነበረው ጌታነህም ይበልጥ ለቡና የግብ ክልል እና ለመሀል ተከላካዮቹ ቀርቦ ለመጨዋት ችሏል፡ ለዚህም እንደማሳያ በሁለተኛው አጋማሽ ግብ እስካስቆጠሩበት ደቂቃ ድረስ ከተደረጉት ሙከራዎች 3ቱን የሞከረው እሱ ሲሆን በተለይ ከ5 ከ50 ውስጥ በግንባሩ የገጨው ኳስ እና በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም ጫና ውስጥ ያልነበረው ተክለማሪያም በጥሩ ቅልጥፍና ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሲሆን ለዚህ ኳስ የመስመር ተከላካዩ ደስታ ደሙ እና የመስመር አጥቂው ጋዲሳ ከሁለተኛው የሜዳ ክፍል ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ለመግባት ያደረጉት ሽግግር ተጠቃሽ ሲሆን ከ2ደቂቃ በኋላ ደግሞ በግራ መስመር በሄኖክ እና አቤል በተመሳሳይ አጨዋወት የተነሳውን ኳስ ከ16ከ50 ውጭም አክርሮ የመታው እና ተክለማሪያም የያዘበት አጋጣሚ እንደዚሁም ይበልጥ ደግሞ የቡድኑን ዋነኛ የማጥቃት እንቅሰቃሴ የሚያሳየው አጋጣሚ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂው ፓትሪክ ማታሲ በተከላካዮቾ ጀርባ ላይ የጣለውን ኳስ ፈቱዲን እና ወንድሜነህን ልምዱን ተጠቅሞ አምልጧቸው የሞከረው ኳስ በድጋሚ ተክለማሪያም ያዳነበት አጋጣሚ የሚጠቀሱ ናቸው።

በእነዚህ ደቂቃዎች ቡናማውቹ የጨዋታ ለውጥ ከማድረግ ይልቅ በጀመሩት መንገድ መቀጠላቸው እና ሁለቱ የመስመር ተከላካዮችም በነበራቸው መንገድ ለማጥቃት በሚወጡበት አጋጣሚ ያለውን ክፍት ቦታ በሁለተኛው ሜዳ የመጨረሻ ክፍል ላይ በመንጠቅ እንደዚሁም ቡድኑ ኳስን ተቀባብሎ ለመጀመር ጥረት በሚያደርግበት ግዜ የጊዮርጊስ ከወገብ በላይ ያሉ ተጨዋቾች በፍጥነት እና ክፍት ቦታዎችን በመዝጋት የቡድኑን ቅርፅ በተወሰነ መልኩ ለማሳጣት ሞክረዋል።

ሌላው ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው ከነበራቸው በተሻለ የቆሙ ኳሶችን ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በነዚህ 15 ደቂቃዎች ሁለት የማዕዘን ምቶችን ያገኙ ሲሆን ሁለተኛውን ፍሬያማ ማድረግ ችለዋል። ሙሉአለም መስፍን በቡና የመከላከል ዞን ውስጥ ነፃ አቋቋም ላይ በመሆን በመጠበቅ ተጨራርፎ የመጣውን ኳስ በቀላሉ ማስቆጠር ችሏል።

የቡና አጥቂዎች ነፃውን የመጫወቻ ቦታ ወይንም ከ16 ከ50 አቅራቢያ የነበረውን ክፍት ቦታ መከላከል አለመቻላቸው ለግቧ መቆጠር አስተዋፆ አበርክቷል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ጊዮርጊሶች ይበልጥ መረጋጋት የታየባቸው ሲሆን፡ ቡናዎችም ባንጻሩ ከመጀመሪያወቀ አጋማሽ የተለዬ ምንነም ነገር ሲያደርጉ አልተመለከትንም።

ቡና በአጠቃላይ ላመነበት ነገር እስከመጨረሻው በትዕግስት መጠበቁ እና እየተመራም በዛው መንገድ ወደግብ መድረስ መቻሉ ለቀጣይ ጥሩ መነሳሳትንም የሚፈጥርለት ሲሆን፤ በጊዮርጊስ በኩል ለማጥቃት የተጠቀመው የተጫዋቾች ቅያሬ የተሻለ የነበረ ሲሆን፡ ይህም ቅያሬ ይበልጥ የአማካይ ክፍሉን በመቀነስና ኳሱን ለተጋጣሚው በመፍቀድ በቀጥተኛ በሚጣሉ ኳሶች እና ከተጋጣሚ በሚነጥቁ እንደዚሁም ተጋጣሚው በሚሰራው ስህተት የሚገኙ ኳሶችን ለመጠቀም ሲሞክር ተስተውሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወትሮው በተለየ መልኩ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የተከላካይ ክፍሉን ከማብዛት ይልቅ የማጥቃት ባህሪያት ያላቸውን ተጫዋቾች ቁጥር በመጨመር በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ጨዋታውን ለመጨረስ ያሰቡበት መንገድ ጥሩ ሆኖ አልፏል። በአጠቃላይ የትናንቱ የሸገር ደርቢ ሁለት ፍፁም የተራራቀ የጨዋታ መንገድ ያላቸው ቡድኖችን አስመልክቶን አልፏል።

የኔ የጨዋታው ኮከቦች

ከኢትዮጵያው ቡና – አማኑኤል ዮሐንስ 

ከበርካታ ጨዋታዎች በኋላ ወደ 6 ቁጥር ሚናው ተመልሶ የተጫወተው አማኑኤል የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ በኩል በሚገባ የተዋጣለት የነበረ ሲሆን፡ በተለይ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ሽግግር ሲያደርግ የነበረው እንቅሰቃሴ እንደዚሁም ክፍት ቦታዎችን ለመሸፈን የነበረው ጥረት ጥሩ የነበረ ሲሆን አህመድ ለሞከረው ኳስም ኳሱን ያቀበለበት መንገድ የልጁን ትክክለኛ ዕይታ የሚያሳይ ነበር።

አህመድ ረሺድ

በዘንድሮው የውድድር አመት ከተከታታይ ጨዋታዎች ድካም በኋላ ወደ ቀደመ አቋሙ እየተመለሰ የሚገኘው የመስመር ተከላካዩ፣ በተለይ በጨዋታው በቦታ አያያዝ እንደዚሁም የአቤል ያለውን ፍጥነት እና ቅልጥፍናን በብስለት በሚፈለገው ደረጃ እንዳይጫወት ከማድረግ ባለፈም በማጥቃት ረገድም ጥሩ የነበረ ሲሆን ሁለት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችንም ማድረግ ችሏል።

ተክለማሪያም ሻንቆ

ግብ ጠባቂው ከተቆጠረበት ከቆመ ኳስ መነሻ ውጭ በጨዋታው ያደናቸው 5 ኳሶች የልጁን ጥሩ ንቃት የሚያሳዩ ሲሆን በተለይ የጌታነህን የግንባር ኳስ እና ሌሎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ያዳነበት እንቅስቃሴው በጨዋታው ካቀበላቸው ኳሶች የተበላሹበት በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ መሆኑን ስናሰብ በእለቱ ጥሩ እንደነበር ከበቂ በላይ ማሳያዎች ናቸው።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ  – ፓትሪክ ማታሲ

ኬኒያዊ ግብ ጠባቂ በጨዋታው ከጊዮርጊስ በኩል ከሁሉም የተሻለ ቁጥሮች ያሉት ሲሆን 5 ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን በማደን ፈረሰኞቹን ታድጓል። በተለይም የአህመድ እና የእንዳለን ኳሶች ያዳነበት መንገድ ግብ ጠባቂውን በብሄራዊ ቡድኑ የሚያሳየውን እንቅሰቃሴም በጊዮርጊስ ቤት ለመድገም ጥሩ መነሳሻ እንደሚሆነው ይጠበቃል። ከዛ ውጭ ለግቡ መቆጠር የተገኘው የማዕዘን ምት መነሻም እሱ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ በጨዋታው መልካም ግዜን እንዳሳለፈ ማሳያ ነው።

ጌታነህ ከበደ

የቀድሞ ብቃቱን ለመመለስ እና በፈረሰኞቹ ደጋፊ የሚፈለገውን አቋሙን ለማሳየት ባለፉት ሳምንታት እየታተረ የሚገኘው ‘ሰበሮም’ በጨዋታው ጥሩ መነሳሳት ከነበራቸው እና የተሻሉ ከነበሩ ተጫዋቾች ግንባር ቀደሙ የነበረ ሲሆን በተጋጣሚያቸው በተወሰደባቸው ብልጫም በግልፅ የራሱን ቡድን አባላት ሲያነሳሳ የተመለከትን ሲሆን የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ከሞከረው እና የግቡ ቋሚ ከገጨበት አጋጣሚ ውጭ 3 ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን በማድረግ በተለይም ከሱ ጀርባ የነበሩት አቤል የአብስራ እና ጋዲሳን ወደ ጨዋታው ለማስገባት ሲሞክር የነበረበት መንገድ የሚበረታታ ነበር።q

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *