የዓለማቀፉ የእግር ኳስ ፌድሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) የፊታችን ሚያዚያ በአዲስ አበባ የሚያካሂደውን 70ኛ ኮንግረስ ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን አዳራሽ የባለድርሻ አካላት ውይይት ተካሂዷል፡፡

ውይይቱ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን፤ በመርሃግብሩ ላይ ፊፋን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን የተወከሉ ባለድርሻ አካላትም ተገኝተውበታል፡፡

የ70ኛው የፊፋ ኮንግረስ ውጤታማ በመሆነ መልኩ ለማስተናገድ የሚያስችል የመነሻ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል። በመቀጠልም የኮንግረሱ አዘጋጅ ብሄራዊ አብይ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡

የኮሚቴው ስብጥርም የሚከተለውን ይመስላል ፡ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፤ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፤ አዲስ አበባ ፖሊስ፤ የሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር፤ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ የኢፌዲሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፤ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት፤ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኢፌዲሪ ገቢዎች እና ጉምሩክ፤ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፤ የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ የብሮድካስት ባለስልጣን፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬት እና የብሄራዊ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ናቸው፡፡

70ኛውን የፊፋ ኮንግረስ ለማዘጋጀት የተዋቀረውን ብሄራዊ አብይ ኮሚቴ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበለይ ጠባቂነት የሚመሩት ሲሆን፡ የኮሚቴው ሰብሳቢዎች ደግሞ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ናቸው፡፡

በዕለቱም ስድስት ተጨማሪ ንዑሳን ኮሚቴዎች በአብይ ኮሚቴው ስር ተዋቅረዋል፡፡ እነዚህም፡ የጸጥታ ደህንነት ና ቪዛ ኮሚቴ፤ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ኮሚቴ፤ የህክምና ኮሚቴ፤ የመስተንግዶ ዝግጅት እና ትራንስፖርት ኮሚቴ እና የመዝናኛ እና ቱሪዝም ኮሚቴ ናቸው፡፡

የአለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበራት ፌዴሬሽን (ፊፋ) ኮርፖሬት ኤቨንት ማኔጀር የሆኑት ሚስ ካሪን አስተርበርገር ኮንግረሱ አዲስ አበባ ሲዘጋጅ ቀደም ብለው መሰራት ያለባቸው የትኞቹ ስራዎች እደሆኑ ገለጻ አድርገዋል፡፡

አዲስ አበባ ለመሰልታላላቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እንግዳ ባትሆንም የሚከተሉት ወሳኝ ነጥቦች ላይ ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ ሚስ ካሪን አስተርበርገር በስብሰባው ለተገኙት የኮንግረሱ ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ አሳውቀዋል፡፡

1. የፊፋ ኮንግረስ ላይ ከ1400 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የገለጹት ሚስ ካሪን፡ ከእርሱ በተጨማሪም 600 ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ እና አፍሪካ ህብረት ውስጥ ለሚሰሩ ለስብሰባው እና ለእግር ኳስ ጨዋታ የሚያገለግሉ ግንባታዎችን የሚሰሩ ሰዎች እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የፊፋ ኮንግረስን ውጤታማ ለማድረግ 300 የሚደርሱ የፊፋ ሙያተኞች ከስብሰባው ሁለት ሳምንት በፊት እንደሚገኙ ገልጸዋል።

2. በስብሰባው ተሳታፊ የሚሆኑ የፊፋ አባል ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የትኛውን የቪዛ ዓይነት መጠቀም እንዳለባቸው ተለይቶ ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ (በውይይቱ የኮንፍረንስ ቪዛ መጠቀም እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡)

3. 70ኛው የፊፋ ኮንግረስ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላት የህክምና አገልግሎት በምን መልኩ ማግኘት እንዳለባቸው ቅድመ ዝግጅት እንደረግ።

4. በኮንግረሱ ወቅት መንገዶች ከትራፊክ ነጻ በምን መልኩ ሊሆኑ ይገባል? የመጓጓዣ አማራጮች ምን መሆን እንዳለባቸው ብሎም እያንዳንዱ መጓጓዣ: አቅጣጫ አመልካች(ጂፒኤስ) መሳሪያ መገጠም እንዳለብት ለዚህም ቅድመ ዝግጅቶች እንዲጠናቀቁ ሀሳብ ቀርቧል፡፡

5. ከፊፋ ለኮንግረሱ የሚገቡ እቃዎች ከመጋቢት ወር ስለሚጀምሩ የገቢዎች እና ጉምሩክ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ እንዲችሉ መመሪያ እንዲሰጣቸው፡፡

6. ለፊፋ ኮንግረስ የሚመጡ ጋዜጠኞች የሚጠየቁት ቪዛ ምን መሆን አለበት አንዲሁም የሚሳተፉበት ማረጋገጫ ወረቀት በምን መልኩ ማግኘት አለባቸው የሚለው ምላሽ እንዲያገኝ፡፡

7. ለፊፋ ኮንግረስ የቴሌኮም አግልግሎት 400 ሲም ካርዶች፤ 4G ኢንተርኔት አገልግሎት እና የሬዲዮ መገናኛ ዘዴ እንዲዘጋጅ

8. ለፊፋ ስብሰባ የሚመጡ ተሳታፊዎች የደህንነት ዋስትና እንዲሰጥ የሚሉ እና ሌሎች ነጥቦችን የፊፋ ተወካይ አቅርበዋል፡፡

መረጃው: የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ነው

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *