እነሆ የ2012ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሜየር ሊግ ከተጀመረ ሶስት /3/ ሳምንታትን አስቆጠረ። በእስካሁኑ ሂደት የሊጉ አጀማመር ፍፁም ሰላማዊ መሆኑ እና የየክለቦቹ ደጋፊዎች ያለፈዉ ዓመት ጥላሸትን ፍቀዉ፡ በፍቅር ተሳስረዉ ክለቦቻቸዉን በጨዋነት ሲደግፉ ከዛም አልፎ እንግዶቻቸዉን ተቀብለዉ በክብር ሲሸኙ፤ የኢትዮጵያዊነት ባህል እና ወጋችን በአሁኑ ትዉልድም ቀጥሎ መመልከታችን የሊጋችን ጥሩ ገፅታ መሆኑን በገሃድ ማየት ችለናል።

ነገር ግን በሊጉ የተመለከትነው ወፍራሙ ድክመት የውድድሮቹ የበላይ ኃላፊዎች ሊጉን ከማስጀመራቸዉ በፊት የክለቦችን የመወዳደሪያ ሜዳዎችን በተገቢዉ መንገድ ፈትሸዉ ፈቃድ የሰጡበት ሂደት ላይ የተሰራዉ ሥራ ክፍተት እንደነበረበት በግልጽ መመልከታችን ነዉ።

ዛሬ ዛሬ ክለቦች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ ቡድኖቻቸዉን ሲያጠናክሩ ማየት የሚያስደስት ጉዳይ ቢሆንም፡ ዋናዉን መድረክ ማለትም መወዳደሪያ ሜዳዎቻቸዉን ቸል ማለታቸው ደግሞ አግራሞትን የሚጭር ነዉ።

ለዚህም እንደማሳያነትት የማነሳዉ ባሳለፍነዉ ቅዳሜ፡ ክለቤ ፋሲል ከነማ ፡ ሆሳዕና ላይ ከወልቅጤ ክለብ ጋር በሊጉ የሳምንቱ መርሃግብር ውድድር በባለሜዳው የተሸነፈበትን የመጫወቻ ሜዳ ሁኔታ ነው።

በመሰረቱ በዉድድር የሚገኝ ዉጤት በክለቦች ጥንካሬና ጥረት የሚገኝ መሆኑ የማያጠያይቅ ቢሆንም፡ እንደ ሆሳዕና ዓይነት ስቴዲየሞች ላይ ግን፡ አይደለም እግር ኳስ ተጫዋቾች፡ ፈረስ እንኳን መሮጥ ቀርቶ በስርዓት በማይራመድበት ሜዳ ላይ ተጫውቶ ዉድድርን ማሸነፍ ግን አጋጣሚም ዕድልም ይጠይቃል።

በሌላም በኩል የወላይታም ሜዳ ጥሩ አለመሆኑን የተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኞች ብቻ ሳይሆኑ የባለሜዳዉ አሰልጣኝም በግልፅነት የተናገረዉ ሙያዉን መሰረት በማድረግ ነዉ።

ስለሆነም ፌዴሬሽኑ ሰበታ ሜዳ ላይ እንደወሰነዉ ሁሉ በእነዚህ ሜዳዎች ላይም መሰል እርምጃዉን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል እላለሁ። በሌላም መልኩ የሀገሪቱ 2ኛ ትልቁ ሊግ በሆነዉ ሱፐር ሊግ ዉድድር ላይም የሜዳዎቹ አስቸጋሪነት እግዚኦ የሚያሰኝ መሆኑን እና ቁርጥ ዉሳኔ የሚያስፈልጋቸዉ በርካታ ሜዳዎች እንዳሉ ለመጠቆም እወዳለሁ።

 

ማስታወሻ፡ ይህ ጽሁፍ ከአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የግል የፌስቡክ ገጽ ላይ የተወሰደ ነው።

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *