የግል ምልከታ| በአሰልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ | ለልዩ ስፖርት |

የሀገራችን እግር ኳስ ዘርፈ ብዙ እና መሰረታዊ አንገብጋቢ ችግሮች ቢኖሩበትም፡ አብዛኛውን ጊዜ ያለውን እንጥፍጣፊ አቅሙን ሲያውል የምንመለከተው እዚህ ግቡ በማይባሉ እና በቀላሉ ሊፈቱ በሚችሉ ችግሮቹ ላይ ነው። በእኔ እምነት የእግር ኳሳችን መሰረታዊ ችግሮች ናቸው ብዬ ከማስቀምጣቸው ነገሮች በዋነኝነት ሊጠቀስ የሚችለው የወጣት እና አዳዲስ ተጫዋቾች በሊጉ ላይ በብዛት አለመታየትን ነው።

ለምን ይህ ሆነ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኛቸው በርካታ እና እርስ በእርስ የተያያዙ ምክንያቶች አሉ። ከነዚህም ውስጥ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል የሜዳ ችግር፣ የፕሮጀክቶች እጥረት፣ የእድሜ ማጭበርበር፣ የተያያዥ ስልጠና ችግር፣ የክለቦች በወጣቶች ላይ ፍላጐት ማጣት የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።

ከላይ የጠቃቀስኳቸውን የእግር ኳሳችን ታዳጊ የማፍራት ችግር መንስዔዎችን በጥቂቱ ሰፋ አድርጌ ለመመልከት ልሞክር።

የመለማመጃ/መወዳደሪያ ሜዳ ችግር

በከተማችን አዲስ አበባ በተለይም ካለፉት ቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ የሜዳ እጥረት ይታያል፡፡  ታዳጊዎች በየሰፈራቸው ብሎም በየት/ቤቶቻቸው የመጫወቻ ሜዳ እጥረት ስላለ፡ ያላቸውን እምቅ አቅም ማወቅም ሆነ ማዳበር አይችሉም። በተለይም አሁን በብዛት በሚገኙት የግል ት/ቤቶች ራሱን የቻለ የእግር ኳስ ሜዳ ያለው ተቋም ማግኘት ሲበዛ ከባድ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ይህ ማለት አብዛኛወቹን ባለ ተሰጥዖ ተጫዋቾች ልናገኝበት በምንችልበት በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች ብዙውን ጊዜያቸውን በሚያሳልፉባቸው አካባቢዎች ሜዳ አለመኖሩ ብቃት ያላቸው ታዳጊዎችን የማግኘቱን ጉዞ ሲበዛ ፈታኝ ያደርገዋል።

 

የፕሮጀክቶች እጥረት

ይኼ ከሜዳ ችግር ጋር ቢገናኝም በሀገር አቀፍ ደረጃ በብዛት ድጋፍ የሚያገኙ ተከታታይና ጥራት ያለው ስልጠና የሚያገኙ ፕሮጀክቶች በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸው በተፈለገው መጠን ተጫዋቾች እንዳይፈሩ ያደርጋል፡፡

ከዚህ ውጪ በየሰፈሩ እና በየአካባቢው በራሳቸው ተነሳሽነት በአነስተኛ በጀት፣ በአካባቢ ሰው መዋጮ፣ በተጫዋቾችና አሠልጣኞች መዋጮ እንዲሁም ባልተመቻቸ ሁኔታ እየሰሩ በርካታ ለፕሪምየር ሊግ እና ለብሄራዊ ቡድኖች የሚበቁ ተጫዋቾችን በተለያየ ደረጃ እያፈሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም በሚመለከተው አካል የስልጠና /ለአሰልጣኞች/ የማቴሪያል እንዲሁም ለእግር ኳስ ስልጠና አስፈላጊውን ድጋፍ ሰለማይደረግላቸው ቁጥራቸው እየተመናመነ መጥቷል፡፡

የስልጠና ችግር

ከላይ እንደገለጽኩት የፕሮጀክቶች እጥረት ቢኖርም፡ አሁን ያሉትን እንኳን ማንዋል አዘጋጅቶ በአግባቡ ስልጠና እንዲሠጥ እና እንዲሁም ስልጠናውን ተከታትሎ ከአንድ የእድሜ እርከን ወደሚቀጥለው እንዲሄድ የሚያደርግ የተመቻቸ ስርዓት ባለመኖሩ እና ታዳጊዎች በፕሮጀክት ከሰለጠኑ በኃላ ቅብብሎሹ ወጥ እና ቀጣይነት ስለሌለው፤ ታዳጊዎቹ ክለብ በመግቢያ ዕድሜያቸው ወቅት ተገቢውን እድል ስለማያገኙ ትኩረታቸውን ወደሌላ ሙያ ያደርጋሉ፡፡  ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በሀ-17 እና በሀ-20 የሚገኙ አብዛኞቹ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦቻችን ዕድሜያቸው ያለፈ እና የጠነከሩ ተጫዋቾችን ስለሚፈልጉ፡ እነዚህኞቹ ዕድሜያችሁ ገና ነው ተብለው ስለሚመለሱ ነው።

ነገሩን የበለጠ ውስብስብ እና ከባድ የሚያደርገው፡ እነዚህ ታዳጊዎች ተመልሰው ወደ ፕሮጀክት እንዳይሄዱ አድሜያቸው ያልፋል፡ በክለቦቹ ደግሞ ከዕድሜ በላይ ስለሚፈለግ ጠብቁ ይባሉና በመሀል ይባክናሉ፡፡

የእድሜ ማጭበርበር

የታዳጊ ተጫዋቾቻችን የእድሜ ማጭበርበር የሚመጣበት ዋነኛ ምክንያት በተለይም በክለቦቹ በኩል ከላይ እንደገለጽኩት ውጤትን ፍለጋ ነው፡፡  ለምሳሌ ያክል ክለቦችም ሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለታዳጊ ቡድን የአሰልጣኝነት ቅጥር ማስታወቂያ ሲያወጡ፡ አንዱ መስፈርታቸው ውጤታማ የሆነ /ዋንጫ የበላ/ የሚል ነው። ታዲያ አሠልጣኙ ይህንን ዕድል ለማግኘት፡ ከፍ ከፍ ያለ እድሜ እና ጠንከር ያለ ተክለሰውነት ያላቸውን ተጫዋቾች ቢመርጥ ሊያስገርመን አይገባም። ስለዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው አካላት አንድን የታዳጊ ቡድን አሰልጣኝ ዋንጫ መብላቱን እንደ ዋነኛ መስፈርት መቁጠራቸውን እስካልቀየሩ እና የታዳጊዎች ስልጠና መሰረታዊ ሀሳብን እስካልተረዱ ድረስ እድሜ ማጭበርበሩ አሁንም መቀጠሉ አይቀርም።

ሌላኛው ችግር ደግሞ፡ ለአንድ ክለብ የታዳጊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የሚከፈለው ዝቅተኛ ደሞዝ መሆኑ (3000ብር በወር)፡ አሠልጣኙ በቶሎ ውጤት አምጥቶ ወደ ቀጣዩ እርከን ማደግ ስለሚፈልግ እንደዚህ አይነት ስህተት ውስጥ መግባቱ ነው። ስለዚህ ክለቦቻችን እዚህኛው ጉዳይ ላይም ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ባይ ነኝ፡፡

የተያያዥ ስልጠና ችግር

በሀገራችን እግር ኳስ ላይ በተለይም የታዳጊዎች ስልጠና እና ማብቃት ላይ ላለው ችግር አንዱና ዋነኛው በየ እድሜ እርከኑ በአግባቡ ተጠንተው የተዘጋጁ የስልጠና ማንዋሎች አለመኖር ነው። ይህ ደግሞ ታዳጊዎች ወጥ የሆነ እና ተከታታይነት ያለው ስልጠና እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል።

ለዚህ አንደመፍትሄ ማስቀመጥ የሚቻለው ደግሞ  የስልጠና ማንዋል በማዘጋጀት ከሀ-15 ወደ ሀ-17 ከዚህ ደግሞ ወደ ሀ-20 እንዲሄድ በማድረግ ልክ አንድ ተማሪ ከ1ኛ ክፍል ወደ 2ኛ ከዚያም ወደ 3ኛ ክፍል እንደሚሄድ ሁሉ፣ ስልጠናውም ተያያዥነተ ይኖረው እና የዋናው ቡድን አሠልጣኞች ለክለቡ የሚሆን አጨዋወት ያላቸውን ታዳጊወችን በፈለጉት ጊዜ እንዲጠቀሟቸው በማድረግ ጤናማ የሆነ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ልማት ስርዓትን መፍጠር ይቻላል።

የክለቦቻችን በወጣት ተጫዋቾች ላይ ፍላጐት ማጣት

የሀገራችን ክለቦች በአብዛኛው ከአንድ አመት ውድድር በላይ እቅድ ስለሌላቸው እና በጀታቸውም በቀጥታ ከመንግስት ካዝና በመሆኑ፡ ከሚያገኙት ላይ ቆጥቦ ታዳጊዋች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ለመጠቀም ያላቸው ፍላጐት አነስተኛ ነው፡፡

የሀገራችን ክለቦች ይህንን ሂደት የማይከተሉት የመንግስት ጡረተኞች ስለሆኑ ነው፡፡  ከመንግስት የሚያገኙት እና ዝውውር ላይ ብቻ የሚረጩት ገንዘብ መጠኑ ቢቀንስ ግን፡ የግዳቸውን ወደዚህ ታዳጊዎችን ወደማብቃት ስርዓት ሲስተም ይገቡ ነበር፡፡

ይህ ሆነ ማለት ደግሞ፡ በርካታ ብቃት ያላቸው ታዳጊዎችን በጥራት ማፍራት ይቻላል። የሀገራችን እግር ኳስም በከፍተኛ ተነሳሽነት እና ፍላጎት የሚጫወቱ በርካታ ተጫዋቾች ይሞላል፡ ያኔ ውጤታማነት ይከተላል፡፡


ስለ ጸሀፊው


አሰልጣኝ ታዲዮስ ተክሉ

-ለኢትዮጵያ  17 ዓመት ብሔራዊ ቡድን የተጫወተ
-የጫካ ሜዳ ታደጊዎችን በማሰልጠን የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ የታዳጊዎች ውድድር ዋንጫ በማንሳት ኮኮብ አሰልጣኝ የሆነ
-በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ለአራት ዓመታት የ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ  በርካታ ታዳጊዎቹን ያፈራ
-በአሁን ሰዓት የኢትዮ ኤሌትሪክ ክለብ የሴቶች ቡድን ምክትል አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ የሚገኝ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *