ዶሃ –  ኳታር – መስከረም 25/2012ዓ.ም – አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ በአለም ሻምፒዮናው የ10000ሜ ወንዶች ውድድር የብር ሜዳሊያ አሸነፈ፡፡ ዮሚፍ ከእልህ አስጨረሽ የመጨረሻ ዙር ፉክክር በኋላ ለኢትዮጵያ አምስተኛውን የውድድሩን የብር ሜዳሊያ ሲያሸንፍ የገባባት 26፡49.34 የርቀቱ የግሉ ምርጥ ሰዓት እና፡ ከውድድሩ አሸናፊ ዩጋንዳዊው አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ በ1.02 ሴኮንድ ብቻ የዘገዬ ሲሆን፡ የሀገሩ ልጆች አንዳምላክ በልሁ (26፡56.71) እና ሀጎስ ገብረሂዎት(27፡11.37) በቅደምተከተል አምስተኛ እና ዘጠነኛ ሆነው ውድድራቸውን አጠናቀዋል፡፡

በአለም ሻምፒዮናው ታሪክ ከየትኛውም ውድድር በላይ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስኬታማነት ጎልቶ በሚታይበት በ10000ሜ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከዚህ ቀደም ዘጠኝ የወርቅ፣ አምስት የብር እና አራት የነሃስ በድምሩ ለ18 ጊዜያት ያክል  ሜዳሊያዎቹን ሲያሸንፉ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ እያንዳንዳቸው ለአራት ጊዜያት ያክል የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ በስኬታማነት ቀዳሚነቱን ቦታ ይዘው ይገኛሉ፡፡

ላለፉት አስር ቀናት በዶሃ አስተናጋጅነት በተሳካ ሁኔታ ሲከናወን የነበረው 17ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ፍጻሜውን ሲያገኝ ኢትዮጵያ በሁለት የወርቅ፣ አምስት የብር እና  አንድ የነሀስ በድምሩ ስምንት ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ፤  ከአፍሪካ ኬንያን በመከተል ሁለተኛ፤ በአለም ደግሞ ከአሜሪካ፣ ኬንያ፣ ጃማይካ እና ቻይና ቀጥሎ በአምስተኛነት ውድድሯን አጠናቃለች፡፡

ኢትዮጵያ በዚህኛው የአለም ሻምፒዮና ያስመዘገበችው አጠቃላይ የሜዳሊያ ብዛት፡ ሶስት ወርቅ፡ አራት ብር እና ሶስት የነሃስ ሜዳሊያዎች ከተገኙበት የ2005ቱ የሄልሲንኪ፣ ከ2013ቱ የሞስኮ፣ ከ2015ቱ የቤይጂንግ እና ከ2003ቱ የሴይንት ዴኒስ የአለም ሻምፒዮና ውድድር ውጤቶች በመቀጠል በአምስተኛ ደረጃ የሚቀመጥ  ውጤት ነው፡፡

በ17ኛው የአለም ሻምፒዮናው ሜዳሊያ ያሸነፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች

ወርቅ

  1. ሙክታር እድሪስ – በ5000ሜ
  2. ሌሊሳ ዴሲሳ – በማራቶን

ብር

  1. ለተሰንበት ግደይ – በ10000ሜ
  2. ሰለሞን ባረጋ – በ5000ሜ
  3. ለሜቻ ግርማ – በ1500ሜ
  4. ሞስነት ገረመው – በማራቶን
  5. ዮሚፍ ቀጀልቻ – በ10000ሜ

ነሀስ

  1. ጉዳፍ ጸጋይ – በ1500ሜ
author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *