የግል ምልከታ | በስፖርቱ ባለሞያ |

የዶሀው አለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊጠናቀቅ ሰዓታት ሲቀሩት በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ አንድ የመጨረሻ ውድድር ብቻ ይጠበቃል፡፡ የወንዶች 10ሺ ሜትር ፍጻሜ!

ሀጎስ ገ/ሂዎት፤ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና አንዳምላክ በልሁ የሚሳተፉበት ይህ ውድድር ለሶስት የአለም ሻምፒዮናዎች አጥተነው የቆየውን የወንዶች የ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ልናገኝበት እንደምንችል ይጠበቃል፡፡ አትሌቶቻችን በዚህ አመት በርቀቱ 1ኛ፣ 2ኛ እና 4ኛ ደረጃን መያዛቸው ለዚህ ውጤት መጠበቅ አንዱ ምክንያት ነው፡፡

በዚህ ውድድር ላይ አትሌቶቻችን አይቻልም የሚባለውን ፈጽመው ከ1-3 ቢያጠናቅቁ ከአለም ሶስተኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ሆነን የመጨረስ እድል ይኖረናል (ጃማይካና ቻይና ባላቸው ሜዳልያ ላይ የማይጨምሩ ከሆነ)፡፡ ይህም ዘንድሮም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2005ዓ.ም. በኋላ የዘለቀውን የኬንያ ተከታይ ሆኖ ማጠናቀቅ የማያስቀር የውድድር ሆኖ ይቀጥላል ሆኖ ማለት ነው፡፡

የዶሃው ውድድር ባለፉት 10 አመታት ካየናቸው የተለየ የሚያደርገው፡ በበጎ ጎኑ ብዙ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሜዳልያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባታቸው፤ በወንድ አትሌቶቻችን የተመዘገቡት ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች (የማራቶን ከ18 አመት በኋላ፤ የ5ሺ በ5 አለም ሻምፒዮና ለ2ኛ ጊዜ መሆናቸው)፤ የ3000ሜ. መሰናክል ከወርቅ የማይተናነስ በ1 መቶኛ ሰኮንድ ተቀድሞ የመጣ ብር ሜዳልያ መሆኑ፤ አትሌቶቻችን በተለየ የቡድን መንፈስ ውድድሮቻችውን ማከናወናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ነገር ግን ሁል ጊዜ ከፌደሬሽናችን አፍ የማይጠፋ ከኬንያ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅደናል የሚል ነገር ዘንድሮም አለመሳካቱ ኬንያውያን በአትሌቲክስ ዘርፍ በምን ያህል ስፋት እየተንቀሳቀሱ እንዳሉ ካለማገናዘብ የመጣ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡

ምክንያቱም ኬንያውያን ባለፉት አመታት ሜዳልያ ያስመዘገቡባቸው ውጤቶች ከ400ሜ መሰናክል እስከ ማራቶን፤ በሜዳ ተግባራት ደግሞ የጦር ውርወራን ሲያካትት፤ ኢትዮጵያችን አጭር የሚባለው ርቀት 800ሜ. እንዲሁም በአለመሸ ሻምፒዮናው ምንም የሜዳ ተግባራት ላይ የሚሳተፍ አትሌት አለማፍራቷን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ ከዘንድሮው ውጤት እኔ በበኩሌ ያስተዋልኩት ፌደሬሽኑ ያመጣው ለውጥ የቡድን መንፈስ ላይ በደምብ መሰራቱ፤ የአትሌቶች ምርጫ ላይ ያን ያህል በአትሌቶች ዘንድ ቅሬታን ያስነሳ አለመሆኑ (የተሻለ እና ግልጽ የምርጫ መስፈርት መዘጋጀቱ) ሲሆን የተመዘገበው ውጤት ግን ከ3000ሜ. መሰናክል በስተቀር በተለምዶ ኢትዮጵያ በምትታወቅባቸው ርቀቶች ከመሆኑ አንጻር የሜዳልያ ቁጥርን ማሳደግ መሰረት አድርጎ የተደረገ ዝግጅት አለመኖሩን ያሳያል፡፡

ወደፊትም የተሻለ ሜዳልያ ብዛት ለማስመዝገብ በታወቅንባቸው ውድድሮች ላይ ብቻ የቡድን ስራ በመስራት ከ1-3 እንዲወጡ ከመጸለይ ባለፈ የውድድር አድማስ ማስፋት ላይ ቢሰራ የሚል ጽኑ እምነት አለኝ!

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *