አበረታች መድኃኒቶችና ቅመሞች ሰዎች ከተፈጥሯዊ አቅማቸው ባለፈ ኃይልንና ብርታትን እንዲያገኙ በልዩልዩ መንገድ የሚወሰዷቸው ሲሆኑ፡ እነዚሁኑ ንጥረ ነገሮች እንደ ራሽያ ያሉ ሃገራት ከጥንት ጀምሮ ለመከላከያ ኃይላቸው ብርታት ሲሉ ጥቅም ላይ ያውሏቸው እንደነበር አንዳንድ ፅሁፎች ያስረዳሉ፡፡ ቀስ በቀስም ከሰራዊቱ አልፈው ወደ ስፖርቱ ዓለም ጎራ ስለ ማለታቸው ይነገራል፡፡

በአሁኑ ወቅት በስፖርቱ አለም ያለው የተፎካካሪነት መንፈስ በከፍተኛ ሁኔታ እያየለ በመምጣቱ ስፖርተኞች በተለይም አትሌቶች በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ዝናን፣ ውጤታማነትንና አሸናፊነትን ለመቀዳጀት ሲሉ የተለያዩ የተከለከሉ አበረታች መድኃኒቶችን ሲጠቀሙ ማየት እየተለመደ መጥቷል።

ይህንን ተከትሎም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ችግሩ ይበልጡኑ እየተስፋፋ መጥቶ፡ በተለይም በአትሌቲክሱ ስፖርት ዘርፍ የበርካታ ሃገራት አትሌቶች የቅጣት ሰለባዎች ሲሆኑ እየተመለከትን እንገኛለን፡፡

የሚከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመም አይነቶች

በስፖርቱ ውስጥ የሚገኙ አበረታች መሆናቸው የታወቁ እና የሚከለከሉ መድሀኒቶች በዋናነት በሶስት ይከፈላሉ።

በውድድር ወቅት የሚከለከሉ

አንድ አትሌት ውድድር በሚወዳደርበት ጊዜ እንደየቅመሙ አይነት የሚወሰን ሲሆን ውድድር ከሚጀምርበት የተወሰነ ቀን አንስቶ እስከ ውድድሩ ቀን ድረስ የሚከለከል ይሆናል። ይህም የአለም አቀፉ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ በየዓመቱ በሚያመጣው ዝርዝር መሰረት የሽንት ወይም የደም ናሙና ውስጥ በሚገኘው መጠን መሰረት ይወሰናል፡፡

በሁሉም ጊዜ የሚከለከሉ

ይህ አትሌቱ በልምምድ፣ በእረፍት ወይም በውድድር ወቅት በአጠቃላይ በማንኛውም አይነት ጊዜ እና ሁኔታ የማይወሰዱ የአለም አቀፉ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ በየዓመቱ በሚያመጣው ዝርዝር መሰረት የተከለከሉ ቅመሞች እና ዘዴዎችን ይጨምራል፡፡

ገደብ ተበጅቶላቸው የሚወሰዱ 

በዚህ ስርዓት ውስጥ የሚገቡ ቅመሞች የአለም አቀፉ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ በየዓመቱ በሚያመጣው ዝርዝር መሰረት ከተፈቀደው ገደብ በላይ መውሰድ የሚከለከሉ ቅመሞች የሚካተቱበት ነው፡፡

አትሌቶች በህመም ምክኒያት የሚከለከሉ ቅመሞችን መውሰድ ካለባቸው በቅድሚያ ከሚመለከተው አካል ማለትም ከዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽን ወይም ከብሄራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል ይህም ፈቃድ ተቀባይነት የሚኖረው ወቅቱን የጠበቀ የፈቃድ አጠያየቅ ስርዓትን ከተከተሉ ብቻ ነው፡፡

ቀጥሎ ደግሞ ስለ አበረታች ቅመሞች አይነቶች በጥቂቱ እንመለከታለን።

የደም ዝውውር አፍጣኝ ቅመሞች

ይህ ድርጊት የደም ህዋስ (ሴል) ከተፈጥሮ ውጪ ተጨማሪ ኦክሲጅን እንዲይዝ በማድረግ (የቀይ ደም ሴል ለማምረት የሚያገለግል ተፈጥሮአዊ ሆርሞን) ከተፈጥሮ ውጪ በብዛት በመውሰድ ባልተገባ መንገድ ተጨማሪ ቀይ የደም ሴል የማምረት ሂደት ነው፡፡

ከሰውነት ፈሳሽ የሚያወጡ መድሀኒቶች

ብዙውን ጊዜ አትሌቶች ውድድር በሚቀርብበት ወቅት የሚጠቀሙት ሲሆን ክብደትን ለመቀነስ እንዲሁም የተከለከሉ መድሀኒቶችን በምርመራ ወቅት በሽንት በኩል እንዲወጡ እና እንዳይታዩ ለማድረግ ሲባል እነዚህ መድሀኒቶች ይወሰዳሉ።

ጡንቻ ገንቢ መድሀኒቶች

ጡንቻን ከልምምድ ውጪ ሊያዳብሩ የሚችሉ ቅመሞችን በመድሀኒት መልክ መውሰድ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ያልሆኑ የሰው ልጅ ማሳደጊያ ቅመሞችን በመጠቀም ተጨማሪ ጉልበት የሚገኝበት ዘዴ ነው። እንዲሁም የተከለከሉ መድሀኒቶች መወሰዳቸውን በምርመራ ወቅት የሚደብቁ መድሀኒቶችን ለአብነት መጥቀስ ይሻላል።

ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች አበረታች ቅመሞችን በመጠቀም ከሚተገበሩ እና ተለይተው ከሚታወቁ የዶፒንግ አይነቶች ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል።

1. ጂን ዶፒንግ ፡- በአትሌቱ/ቷ ሰውነት ውስጥ ያለውን ፕሮቲን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን ተፈጥሯዊ ከሆነው በተለየ መልኩ እንዲሰራ ለማድረግ እነዚህን ንጥረ ነገሮች ለሰውነት ማስተዋወቅ ጂን ዶፒንግ ይባላል

2. የደም ዶፒንግ፡- በሰውነትውስጥ በዛ ያለ የቀይ ደም ህዋስን በሰው ሰራሽ መልኩ ከውድድር በፊት በማስገባት ከተፈጥሮ ውጪ ሰውነት ውስጥ በቂ ኦክሲጅን እንዲኖር ያደርጋል

3. ቁሳዊ ዶፒንግ ፡- የሚጨምሩ በአትሌቱ የመወዳደርያ ጫማ ፣ትጥቅ የሚገጠሙ ቁሶች ናቸው

ዶፒንግ በጤና የሚያስከትለው ችግር

እነዚህን በህግም ሆነ በሞራል የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን መጠቀም ከጊዜያዊ ውጤታማነት በተቃራኒው በህግ የሚያስቀጣም ተግባር ሲሆን በተጨማሪም ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩትን ዘላቂ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳቶችን ያደርሳል። እነሱም ፡- ተፈጥሮዓዊ ስርዓትን ያዛባል፣ ለሌሎች የጤና እክሎች ያጋልጣል፣ ለከፍተኛ ጭንቀት ይዳርጋል፣ ከአትሌቲክስ አለም ያሰናብታል፣ ለህልፈተ ሂወት ሊዳርግ ይችላል።

ይህንን ለማስቀረት ከአትሌቱ ምን ይጠበቃል?

በመጀመሪያሁላችንም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ንፁህ ስፖርት እንዲሰፍን ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት ይኖርብናል። ጠንካራ ልምምድ ማድረግ፣ ከምንሰራው የአትሌቲክስ ዘርፍ ጋር የሚሄድ የስነ ምግብ ስርዓት መከተል። ማንኛውንም አይነት መድሀኒት ከመውሰዳችን በፊት ለሀኪም ማማከር፣ የአሸናፊነት መንፈስ ሁልግዜ እንዲኖረን ማድረግ፣ ዶ ፒንግን መጠየፍ፣ መዋጋትና ማጥፋት፣ ማሸነፍን በልምምድ፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ ጠንካራ የማሸነፍ ስነ-ልቦና እና በንፁህነት ማሸነፍ እንደሚቻል ማመን እና እውን ማድረግ፡፡


ቅድስት ታደሰ –  በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስፖርት ህክምና እና ስነ-ምግብ ከፍተኛ ባለሞያ 
author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *