በ ኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም
አዲስ አበባ – መስከረም 09/2012 ዓ.ም

ልዩ ልዩ መገለጫዎች ያሏቸው እና ደጋግመው የሚከሰቱ አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳቶች በስፖርቱ አለም ውስጥ የአትሌቶች ትልቆቹ ባላጋራዎች ናቸው፡፡ አትሌቶች በተፈጥሮም ሆነ በጠንካራ ልምምድ የገነቡትን እምቅ አቅም በውድድር መድረኮች ላይ በሚገባ ለማሳየት ከሁሉም ነገር በላይ ጤናማ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንዳንድ ምርጥ የሚባሉ እና ተስፋ ሰጭ ስፖርተኞች ቶሎ ብቅ ብለው የሚጠፉበት ዋነኛው ምክንያትም ስፖርታዊ ጉዳት ነው፡፡

እኔም ለሙያው እና አትሌቶቹ ባለኝ ቅርበት የተነሳ እንደክፍተት የተመለከትኩትን ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ያለመስጠት ችግር ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ እና ስፖርተኞቻችን ይህንን አሳሳቢ ችግር በመቋቋም ጤናማ እና ብቁ ሆነው በውጤታማነታቸው እንዲቆዩ ይረዳቸው ዘንድ ቀጥሎ ያለውን ሙያዊ ምክሬን ለማካፈል እወዳለሁ፡፡

ቅድመ ምርመራ ማድረግ

በሀገራችን ብዙም የማይዘወተር ነገር ግን መተግበር ያለበት ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ማንኛውም አትሌት ከእረፍት ወደ ልምምድም ሆነ የውድድር ዝግጅት ከመመለሱ አስቀድሞ አጠቃላይ የጤና ምርመራ ማድረግ ነው፡፡

ምርመራዎቹም በዋናነት የነጭ እና የቀይ የደም ሴሎች ቆጠራ፣ የአይረን፣ የፕሮቲን እና የቫይታሚን መጠን፣ የልብ፣ የመተንፈሻ አካላት፣ የጡንቻ፣ የአጥንት እና አጠቃላይ የጤና ሁኔታን የሚመለከቱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ መመርመር ብቻ ሳይሆን የምርመራ ውጤቶቹን በአግባቡ መዝግቦ በማስቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለህክምና ባለሞያዎች ማሳየትም ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ምርመራ ቀድሞ ማድረግ ጥቅሙ፡ በዋናነት ጉዳቶች እና ህመሞች እንዳሉ በምርመራ ከተደረሰባቸው እነዚህ ነገሮች ከመባባሳቸው እና በአትሌቱ ላይ ከፍ ያለ የጤና ጉዳት ከማድረሳቸው አስቀድሞ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግ እና አሰልጣኞችም የአትሌቱን የጤና ሁኔታ ያገናዘበ ሳይንሳዊ የልምምድ ፕሮግራም እንዲዘጋጁ ለማድረግ ነው፡፡

ራስን መንከባከብ

አትሌቶች አቅም በፈቀደ መጠን ለራሳቸው ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በቂ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ እረፍት ማድረግ፣ ከአሰልጣኝ እውቅና ውጭ የሆነ እና ያልተመጠነ ልምምድን ፈጽሞ አለማድረግ፣ የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓትን መከተል ለምሳሌ፡ በትንሹ በቀን እሰከ አራት ሊትር የሚደርስ ውሃ መጠጣትን አለመርሳት፣ ተጨማሪ የጅምናዚየም እና እንደ ውሃ ዋና እና የብስክሌት አይነት የጎንዮሽ ስፖርቶች ላይ መሳተፍ፣ የስፖርት ማሳጅን በሚገባ መጠቀም፡፡ የስፖርት ማሳጅ ከመደበኛው ማሳጅ የሚለይ ሲሆን በተለይም ከአድካሚ ልምምድ በኋላ በቶሎ ለማገገም ፍቱን መፍትሄ ነው፡፡ በተጨማሪም ንጽህናቸው የተጠበቁ ምቾት ያላቸው የስፖርት ትጥቆችን መጠቀምም ሌላኛው መረሳት የሌለበትጉዳይ ነው፡፡

ባለሙያን ማማከር

በዚህ ዘመን በተፈጥሮ ከሚገኝ ችሎታ በተጨማሪ ጊዜው ያፈራውን እና ሳይንሳዊ የሆነውን የስልጠና ዘዴ መከተል ለጤናማ አትሌትነት እና ለውጤታማነት በእጂጉ ጠቃሚው ነገር ነው፡፡ በመሆኑም አትሌቶች በተቻለ መጠን ከስፖርቱ ባለሞያዎች ጋር በቅርበት እንዲሰሩ ይመከራል፡፡

በመሆኑም ስፖርተኞቻችን ከአሰልጣኞቻቸው በተጨማሪ ከህክምና፣ ከስነ-ምግብ፣ ከስነ-ልቦና፣ ከፊዚዮቴራፒ፣ ከተግባቦት እና ሌሎችም ባለሞያዎች ጋር መስራት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ሊያውቁ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

የጉዳት ትንሽ የለውም

ብዙ የሀገራችን አትሌቶች የአቅማቸውን ያክል ውጤታማ እንዳይሆኑ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ እና ዋነኛውየህመም ስሜት ሲሰማ ‹‹ አሁን ይሻለኛል፤ ቀላል ነው›› በሚል ስሜት በወቅቱ ህክምና አለማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሔው እያንዳንዷ የህመም ስሜት ስትሰማን ወዲያውኑ ለህክምና ባለሞያ ማሳወቅ እና ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ህክምናውን መከታተል ነው፡፡

ነገር ግን ይህን ሳያደርጉ ‹‹ቀላል ነው›› እና ‹‹አሁን ይሻለኛል›› በሚል ስሜት ያለ ሀኪም ፈቃድ የተለመዱ የማስታገሻ እንክብሎችን መውሰድ የአትሌቱን የስኬት እድሜ በማሳጠር ጉዳቱን ከግለሰብ አልፎ ለሀገርም እንዲተርፍ ያደርገዋል፡፡

አንድ ማሳያ ብነግርህ፡ ‹‹በቅርቡ በጥሩ ደረጃ ላይ የምትገኝ አንዲት የሀገራችን አትሌት ልምምድ ላይ ባጋጠማት ቀላል እና በትክክለኛው የህክምና መንገድ ቢታይ በፍጥነት ሊድን የሚችል ጉዳት በወቅቱ ተገቢውን ህክምና ባለማግኘቷ ረዘም ላለ እና ለተወሳሰበ ተጨማሪ ጉዳት ተዳርጋለች፡፡››

ከዚህ የምንማረው ዋናው ቁምነገር የጉዳት ትንሽ አለመኖሩን እና ከባለሙያ ጋር እየተነጋገሩ መስራት ለረጅም እና ውጤታማ የአትሌቲክስ ህይዎት አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *