የግል ምልከታ | በአዲሱ የፌዴሬሸኑ የሊግ ፎርማት ዙሪያ | በአቶ ተስፋዬ ካሕሳይ | የስፖርት አስተዳደር ባለሞያ| ለልዩ ስፖርት |


በመዲናችን አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፎቅ ተደረመሰ እና ድልድይ ፈረሰ የሚሉ አይነት ዜናዎችን መስማት እየተለመደ የመጣ ነገር እንደሆነ ይሰማኛል። ለምን እንዲህ ሆነ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ ደግሞ በአብዛኛው ግልጽና የማያሻማ ሆኖ እናገኘዋለን።

ይኼውም ባለሞያዎቹን ያፈራው ስርዓት ወይም ሲስተም ችግር፥ ተገቢ ባለሞያዎችን በተገቢው ቦታ አለመቅጠር፣ ተገቢ ግብዓት አለመጠቀም ወይም መሰረቱን በተገቢው ሁኔታ አለመገንባት (በአሸዋ ላይ መገንባት) ወይንም በሌሎች ምክንያቶች ሊሆን ይችላል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስም እንዲሁ ጥራት እንደሌለው ጅምር ህንጻ ሲፈርስ፡ መልሶ ለመገንባት ጥረት ሲደረግ እና እንደገና ሲፈርስ ይኼው አዲሱ አመት 2012 ላይ ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግንባታ የተጀመረው ከ76 ዓመታት በፊት በ1936 ዓ.ም ቢሆንም እስከአሁን ድረስ ትክክለኛውን መሠረት ማግኘት ስላልቻለ አሁንም ጊዜ ጠብቆ ሊደረመስ እንደደረሰ ህንጻ ተንጋድዶ ቆሞ ይገኛል።

ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ግድ የሚለን በርካታ ሰዎችም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህ ነገር ከመከሰቱ በፊት መሠረቱ ልክ ያልሆነው ተቋም እንደገና መገንባት እንዳለበት ላለፉት አስርት ዓመታት በተለያዩ መንገዶች ብንጠይቅም ሰሚ አልተገኘም፡፡

ይባስ ብሎ እግር ኳሱ በአሁኑ ወቅት የብሄር እና የመንግስት ፖለቲካ ጥገኛ እንዲሁም የካድሬዎች እና የጡረተኞች የጊዜ ማሳለፊያ ወይም መጠቀሚያ ሆኖ፡ እድገቱም ከድጡ ወደ ማጡ እየዋዠቀ አወዳደቁ የማያምር መስሏል፡፡

ለዚህም ነው እግር ኳሱ በአስቸኳይ ራሱን ችሎ ከብሄር፣ ከሃይማኖት እና ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ እንዲገነባ ካላደረግነው፡ ከስፖርቱ ማግኘት ያለብንን በርካታ በጎ ነገሮች ከማጣታችን አልፎ: ክፉ ነገሩን መጋታችን የማይቀር መሆኑን አመላካች ነገሮችን እየታዘብን መሆኑን ለመናገር የምንወደው።

የልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት ስልጠና እና ብቁነት ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የአንድ ሀገር የእግር ኳስ ደረጃ እና ጥራት የሚወሰነው ከዝቅተኛው የአገሪቱ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ጫፍ ድረስ በተዋቀረ አስተዳደራዊ አደረጃጀት እና የውድድር መርሃ ግብር ነው፡፡

የስፖርት ስልጠና መሠረታዊ ነገር ሲሆን፣ የስልጠናው ወጤት የሚለካው ደግሞ በውድድሮች ላይ በሚታየው ውጤት ነው፡፡
ህዝባዊ ክለቦች እና ውድድሮች እየበዙ እና እያደጉ በሄዱ ቁጥር የተለያዩ ደረጃዎች እና ፍላጎቶች ስለሚከሰቱ ሊግ የሚባለው አስተሳሰብ ይፈጠራል፡፡

በሊግ መሠረታዊ መርህ መሰረት በቁጥር ያነሱ ግን ከፍተኛ አፈጻጸም እና አቅም ያላቸው ቡድኖችን ወይንም ክለቦችን በላይኛው ጫፍ ላይ የሚመደብ ሲሆን ሌሎቹም እንደየደረጃቸው ወደታች ይመደባሉ፡፡

በታችኛው ህዝባዊ መዋቅርም በሺዎች የሚቆጠሩ ቡድኖች ወይም ክለቦች ይኖራሉ፡፡ መሠረቱም እሱ ነው፤ አሸዋ ሳይሆን አለት! ይህን ተከትሎ ክለቦች እንደየውጤታቸው  በመውጣትና በመውረድ ላይ የተመሠረተ ውድድር ያካሂዳሉ፡፡ ይህም ሊግ በፒራሚድ ቅርጽ ይቀመጣል፡፡

እንግዲህ በሊግ ሲስተም ለመሳተፍ ክለቦቹ ራሳቸውን ለማዘጋጀት ፈቅደው እና ግዴታ ገብተው በውድድሩ ውስጥ ይሳተፋሉ ማለት ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በግዴታ ሳይሆን በራሳቸው አቅም እና ሁኔታ ተመስርተው ማለት ነው፡፡

በሀገራችን የእግር ኳስ ውድድር ግን ክለቦች ሳይወያዩበት እና ሳይፈቅዱ ከላይ በተጣለባቸው ሁኔታ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተብሎ በሚታወቀው ውድድር ውስጥ እንዲሳተፉ ሲደረግ ክለቦቹ ሳይመክሩበት እና ለዚህ የሚሆን መዋእለ ነዋይ እና መሠረተ ልማት ሳያዘጋጁ አንዳንዶቹም (አብዛኞቹ ማለት ይቻላል) ክለብ የሚባለውን አቋም ሳይኖራቸው በስሜት እና በድፍረት ውድድሩ ውስጥ ገብተው እየተወዳደሩ ይገኛሉ፡፡

ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በኋላ ግን እነሆ አልቻልንም! የሚል ጥያቄ በማንሳት ሊጉን ፈተና ሆነውበታል፡፡ እርግጥ ነው አወዳዳሪው አካል ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ክለቦቹ ክለብ እንዲሆኑ እና የራሳቸውን ቋሚ እና በቂ ገቢ የሚፈጥሩበትን ስርዓት መዘርጋት ባለመቻሉ ዋናው ተጠያቂ ቢሆንም አንጋፋ የሚባሉት ክለቦችም ከተጠያቂነት ሊያመልጡ አይችሉም፡ ቢያንስ አርአያ መሆን ባለመቻል።

ያም ሆነ ይህ በተለይ በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ ለመሳተፍ የገንዘብ እና የደህንነት ስጋት ስላለብን ፕሪምየር ሊጉ መታጠፍ አለበት ብለው ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2011 ዓም የመጨረሻው ቀን የእብደት የሚያስመስልበት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ይህም ውሳኔ 16 ክለቦች ይሳተፉበት የነበረውን የፕሪምየር ሊግ ውድድር 24 ክለቦች እንዲሳተፉበት በማድረግ በሁለት ምድብ ሆነው የ2012 ዓም ውድድርን እንዲያካሂዱ መወሰኑን ነው፡፡

ይሄንን ውሳኔ እብደት ነው እንድል ከሚያሰኙኝ ምክንያቶች የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡-

1ኛ፡ የውድድሩ ባለቤቶች ክለቦቹ በመሆናቸው የሚመቻቸውን መወሰን ያለባቸው ራሳቸው ክለቦቹ ናቸው፣

2ኛ፡ ክለቦቹ ተሰብስበው ቢወስኑ እንኳ የመሸጋገሪያ ጊዜ ስለሚያስፈልግ አዲሱ ፎርማት ሊጀመር የሚችለው በ2013 የውድድር ዘመን እንጂ በ2012 መሆን አይገባውም ካለዚያ ያለፈውን አይነት ስህተት መድገማችን የማይቀር ነው፣

3ኛ፡ አሁን ባለው የፕሪምየር ሊግ ውድድር የሚጠቀሱት የገንዘብ እና የደህንነት ስጋት ችግሮች ፌዴሬሽኑ አሁን መፍትሔ ብሎ ባስቀመጠው ውሳኔ ሊቀረፍ ስለማይችል፣

4ኛ፡ ፌዴሬሽኑ አንድ ፕሪምየር ሊግ በወጉ መምራት ሳይችል እንዴት ሁለት ፕሪምየር ሊግ ሊመራ ይችላል ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚያፈልግ በመሆኑ፡፡

በእኔ እምነት እግር ኳሳችን በብዙ ምክንያቶች መሰረቱን እንዲያስተካክል ያስችለው ዘንድ ከዜሮ መጀመር እንዳለበት ስለማምን፡ የአዲስ አበባ ክለቦች ያቀረቡት ጥያቄ የተሻለ መፍትሄ ሆኖ ይሰማኛል፤ ነገር ግን እሱም ቢሆን ግብታዊ በመሆኑ በጥልቀት ታስቦበት የሚተገበር ከሆነ ነው፡፡

በተረፈ በዘርፈ ብዙ ችግሮች የተቀፈደደውን እግር ኳሳችንን ለማዳን ችግሮቹ በጥቅል ታይተው ጥቅል መፍትሄ እንጂ የሚያስፈልጋቸው አንድን ስህተት መዝዞ ለመፍታት መሞከር ወደ ባሰ የችግር ባህር ውስጥ መግባት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡

ስለሆነም ፌዴሬሽኑ አሁን መፍትሄ ብሎ ያቀረበው ውሳኔ ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት ከላይ ያስቀመጥኳቸውን አንኳር ነጥቦች ቢመለከታቸው እመክራለሁ። ካልሆነ ግን በመግቢያዬ እንደገለጽኩት አንድን ትልቅ ዝሆን ሁለት ቦታ በመክፈል ሁለት ትንንሽ ዝሆኖችን ማግኘት አይቻልም፤ ይልቁንም የአንዱንም ህይወት ይነጥቃል እንጂ …


ስለ ጸሀፊው


 

አቶ ተስፋዬ ካህሳይ

– ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲን ቢ.ኤ ዲግሪ

– ከ15 ዓመታት በላይ በባንክ ሥራ እስከ ከፍተኛ ሃላፊነት

– የፊፋ ክለብ አስተዳደርን ጨምሮ የተለያዩ የማኔጅሜነት እና የማርኬቲን ኮርሶች

– በግል ንግድ ሥራ የሚተዳደር

በተጨማሪም፡- በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበርን በማደራጀት እና በሕግ እንዲመዘገብ በአስተባባሪ ኮሚቴነት እና በማህበሩ ሊቀመንበርነት፤ በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የቦርድ አባል በመሆን የተለያዩ አስተዋጽኦዎችን ያበረከተ፤ በ1999 ዓ.ም የፌዴሬሽኑን ደካማ አሰራር በመቃወም የክለቦች ህብረት በአዲስ አበባ እንዲቋቋም ከመጀመሪያዎቹ ሃሳብ አመንጪነት እና አስተባባሪነት፤ በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ አባልነት፤ በ2009 ዓም በሰመራ በተደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፕሬዚዳንት ከተወዳደሩት አራት ሰዎች ውስጥ አንዱ የነበረ።

author image

About Liyusport.com

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *