በ አንጋፋው ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ – ለ ልዩ ስፖርት 


ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ

ፓሪስ ፈረንሳይ – ነሀሴ 30/2011 ዓ.ም – ነጋድራስ ተሰማ እሼቴ በአማርኛ ቋንቋ እና ግጥም የበለጸጉ ስለነበሩ፣ በመስከረም 1 ቀን 1914 ዓ.ም ለተወለደው ልጃቸው “ይድነቃቸው” የሚል ስም ሲያወጡለት በሀገሪቱ ውስጥ ተሰምቶ የማይታወቅ መሆኑን ዘመናት መስክረዋል፡፡

ይድነቃቸው በትምህርቱ እና በእውቀቱ መቼም የሚደነቅ ቢሆንም ዝናው ጎልቶ ሊታይ የቻለው ግን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተሰልፎ በታሪክ በተመዘገበው የመጀመሪያ ግጥሚያ የአርመኖቹ ቡድን አራራት ላይ ሁለት ግብ በማስቆጠሩ ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሚሰራው ስራ በሙሉ የሚደነቅ ብቻ ነበር፡፡

የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪ ሆኖ ስፖርት በሰፊው ያዘወትር ነበር፡፡  በወቅቱ ባልንጀሮቹ ወደ ሆለታ ሚሊቴሪ አካዳሚ ሲያመሩ፡  እሱ ሀገራችን ባስቸኳይ የሚያስፈልጓትን ሰነዶች ከፈረንሳይኛ እና ጣልያንኛ እንዲተረጉሙ ከአቶ ከበደ ሚካኤል እና ተክለጻዲቅ መኩሪያ ጋር በትምህርት ሚንስቴር መስራት ጀመረ፡፡

ከዚያም የዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል አስተዳዳሪ ሆኖ ሲሰራ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደሚያስፈልግ በመረዳት አቅሙን በሙሉ ምስረታው ላይ አዋለ፡፡

ጋሼ ይድነቃቸው እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

ጋሼ ይድነቃቸው ማንበብ ስለሚወድና አዲስ አአባ ውስጥ የፈለገውን ጋዜጣ ስለማያገኝ ከፈረንሳይ ሀገር  ‹‹ሌኪፕ›› የሚባል የእለት የስፖርት ጋዜጣ፥  ‹‹ፍራንስ ፉትቦል›› እና ‹‹ሚርዎር ዱ ስፖርት›› የሚባሉ ሳምንታዊ መጽሄቶችና፣የጣልያኑን የዕለት ስፖርታዊ ጋዜጣ  ‹‹ጋዜታ ዴሎ ስፖርት›› በኮንትራት ማስመጣት ጀመረ፡፡

እ.ኤ.አ 1943 ያቋቋመው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም እየተጠናከረ መስፋፋቱን ቀጥሏል፡፡ የፌዴሬሽኑን ስራ በሙሉ የሚያካሂደውም ራሱ ጋሼ ይድነቃቸው ነው፡፡

የፌዴሬሽኑ የመጀመሪያው የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባሎች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ፕሬዝዳንት፡ ሌተና ኮሎኔል ከበደ ገብሬ በኋላም ሌተና ጄነራል፣ የኢትዮጵያን ቃኘው ሻለቃ ጦርን ኮሪያ ያዘመቱ፣ በኮንጎ የተባበሩት መንግስታት ጦር ዋና አዛዥ  እና የመከላከያ ሚንስትር የነበሩ፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተና ኮሎኔል አበበ ደገፉ የፖሊስ ሰራዊት አዛዥ እና ከፈረንሳይ ሚሊቴሪ አካዳሚ የተመረቁ፡፡ ሻምበል ወልደ ዮሐንስ ሽታ በኋላ ጄኔራል ገንዘብ ያዥ፣ በኮሪያ እና በኮንጎ የኢትዮጵያ ጦር አዛዥ  የነበሩ፡፡  አባሎች፡ አቶ ገብረስላሴ ኦዳ፡ የጎማ ፋብሪካ ባለቤት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ፕሬዝዳንት የአቶ አብነት ገብረመስቀል አጎት፤ጋዜጣ ዲሚትሪ ስጎለምቢስ፤ አሁን በቅርቡ በ98 ዓመታቸው ያረፉት  ሻለቃ ኃይሌ ባይከዳኝ በኃላ ሜጄር ጄኔራል፤ ሻለቃ ጋሻው ከበደ በኋላ ሜጄር ጄኔራል እና ሻለቃ አለሙ ግዛው ከፖሊስ ሰራዊት ነበሩ፡፡

ቴክኒክ ኮሚቴው ውስጥ ደግሞ ስዊድናዊው ኦኒ ኒስካነን፣ ሙሴ ናልዲና፣ አንድ ህንዳዊ፣ አንድ እንግሊዛዊ እና ሌላ ስዊድናዊ ባለሞያዎች ነበሩ፡፡

የፌዴሬሽኑን የጽሕፈት ቤት ችግር ለማቃለል በገንዘብ ያዡ በሻምበል ወልደዮሐንስ ሽታ አማካኝነት ከክብር ዘበኛ ጦር መምሪያ በተገኘ የአምስት መቶ ብር ብድር  አንድ ክፍል ቢሮ እና ተላላኪ  ጃንሜዳ ተገኝቶ ዋናው ጸሐፊ ይድነቃቸው ተሰማ ስራውን ያራምድ ጀመረ፡፡

እዚህ ጋር መዘንጋት የሌለብን ጋሼ ይድነቃቸው በወቅቱ በተመሳሳይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ተጫዋች፥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እና አሰልጣኝ ነበረ፡፡ በጊዜው ታዲያ ማንም ሰው ይህንን ምክንያት አድርጎ በጋሼ ይድነቃቸው ስራ ላይ ቅሬታ አለኝ ሲል ተሰምቶ አይታወቅም ነበር፡፡

ምክንያቱ ደግሞ በዚያን ዘመን የነበሩት ሁሉ አገራቸው እንድትበለጽግ የሚሹ የእግር ኳስ ጨዋታ እንዲዳብር ጥረት የሚያደርገውን ሰው ከማድነቅ ሌላ በሆነው ባልሆነው ትችት የሚሰነዝሩ አልነበሩም እና ነው፡፡ ይሔ የሆነው በዚህ ዘመን ቢሆን ኖሮ ያውም በዘር በተከፋፈልንበት ወቅት፣ ጦርነት መነሳቱ አይቀርም ነበር፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከተመሰረተ ከዘጠኝ አመታት በኋላ እ.ኤ.አ በ1952 የፊፋ አባል ሆኖ ተመዘገበ፡፡ ከጣልያን ወረራ አስቀድሞ የነበሩት ትምህርት ቤቶች በፈረንሳይኛ ያስተምሩ ስለነበር እና ሁሉም የፌዴሬሽኑ ሃላፊዎች ፈረንሳይኛ ይችሉ ስለነበር የፈዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ለመጀመሪያ ጊዜ የረቀቀው በፈረንሳይኛ ቋንቋ ነበር፡፡

ከዚያም ጋሼ ይድነቃቸው ሁሉንም ህጎች ወደ አማርኛ መተርጎም ጀምሮ ስለነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሆነው የእግር ኳስ የጨዋታ ህጎች ነበር፡፡ እሰከዚያ ድረስ ለእግር ኳስ የጨዋታ ህጎች የምንገለገልበት ቋንቋ ጣልያንኛ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡  ፎሪ፣ሪጎሬ፣ ኮርና፣ ማኖ፣ እንዲሁም ከእንግሊዝ የተዋስነው፣ ጎል፣ ፋውል፣ ኦፍሳይድ ወዘተ…

ሀገሪቷን የጠቀመው የጋሼ ይድነቃቸው የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ ማወቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ሪጎሬ ወይንም ፔናሊቲን ፍጹም ቅጣት ምት ብሎ ተረጎመው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ድረስ በስፖርቱ ውስጥ የምንጠቀምባቸውን የቴክኒክ ቃላትን በተለይም በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣  ቦክስ፣ ብስክሌት ወዘተ… አብዛኞቹን ጋሼ ይድነቃቸው የፈጠራቸው ናቸው፡፡

በራሳችን ቋንቋ ለመኩራት ያበቃንም  ለፊፋ እና ለሌሎች ኮንፌዴሬሽኖች የምንልካቸው ሰነዶች በሁለት ቋንቋ ማለትም በአማርኛ እና በፈረንሳይኛ በመታተሙ ነው፡፡

ጋሼ ይድነቃቸው ተሰማ፥ አቶ መኮንን ሙላት፡ የአዲስ አበባ ከንቲባ እና የኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑ እና አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ፡ ፓሪስ – ሻን ኤሊዜ ጎዳና ላይ እ.ኤ.አ በ1966 

እኔና ጋሼ ይድነቃቸው

የእግር ኳስ ጨዋታ በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ይቻል ዘንድ ሀረር መምህራን ማሰልጠኛ ተሰብስበው ለነበሩት ለሀገሪቱ የስፖርት መምህራን በሙሉ ጋሼ ይድነቃቸው የእግር ኳስ ህጎችን በማስተማር እያንዳንዳቸው በሚኖሩባቸው ክፍለሐገሮች ቡድኖች እንዲያቋቁሙ እና አዘጋጅ ከሚቴ እንዲመሰረቱ ሀላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ከስፖርት መምህራኑ መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡

ከዚያም እ.ኤ.አ በ1954 ፊፋ ሚስተር አንድሬዜቪች የሚባሉ የዩጎዝላቪያ ተወላጅ ወደ አዲስ አበባ ልኮ የዳኞች ኮርስ ተካፍለናል፡፡ እኔም አርቢትር ሆኜ ተመርቄያለሁ፡፡ የአርቢትሮች ደጋፊ የሆንኩትም በዚህ የተነሳ ነው፡፡

ድሬዳዋ ከተማ አሊያንዝ ፍራንሴዝ ት/ት ቤት ሳስተምር የምድር ባቡር ቡድን አቋቁመን በሻምፒዮናው ከመጫወቴ በፊት በአርቢትርነት አገልግያለሁ፡፡ የጋሼ ይድነቃቸውን ትምህርት በስራ ላይ ማዋል የጀመርኩት ያኔ ነው፡፡

ጋዜጣ ከእጁ የማይለየው እና ማንበብ የሚወደው ጋሼ ይድነቃቸው፡ ለሁሉም ዜናዎቹን አካፍሎ፣ አስረድቶ፣ አስተምሮ ነው ትርፍ ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው፡፡

ሁሌም የስፖርት ጋዜጦቹን አንብቦ ሲጨርስ ለእኔ ስለሚሰጠኝ ወደ ጋዜጤኝነት ሞያ ያዘነበልኩት በዚህ ምክንያት ነው። እንዳውም የጣሊያንኛ ቋንቋ እንድማር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ የተሰራው የጣሊያን ት/ቤት አስገብቶኝ ማታ ማታ ተምሬ ጋዜጣ ዴሎ ስፖርትን ብቻየን በማንበብ የዡቬንቱስ ክለብን እከታተል ነበር፡፡

በወቅቱ አንድ አንድ በጣሊያኖች የሚተዳደሩ ቡና ቤቶች ውስጥ  ልክ እንደ ጣሊያን ሀገር፡ ቶቶ ካልቾ ማለትም የሻምፒዮናውን ውድድር ውጤት በመወራረድ መጫወት ይቻል ነበር፡፡ እኔም ደሞዝ በሚወጣበት ሳምንት ተጫውቼ ምንም አላገኘሁም ነበር፡፡

ጋሼ ይድነቃቸው እና የጸረ አፓርታይድ ትግላቸው

ጋሼ ይድነቃቸው የአለምን ፖለቲካ ይከታተል ስለነበረ በደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ላይ የሚፈፀመውን ግፍ በሚገባ ያውቅ ነበር፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን ካርቱም ላይ ሲመሰርቱ አራት ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካ፡፡ የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር እጣ ሲወጣም ኢትዮጵያ ከ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን ደግሞ  ከግብጽ ጋር ነበር የደረሳቸው፡፡

ደቡብ አፍሪካ በጊዜው ትከተለው በነበረው የአፓርታይድ የፖለቲካ ስርዓት መሰረት “የማሰልፈው ቡድን ወይ በጥቁሮች ብቻ የተገነባ አለዚያ በነጮች እንጂ መቀላቀል አልችልም”  በማለቷ ከውድድሩ እንድትወጣ ተደረገች፣ ኢትዮጵያም ለፍጻሜው ግጥሚያ አለፈች፡፡ ግብጽም ሱዳንን እና ኢትዮጵያን አሸንፋ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ዋንጫ ወሰደች፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም አፍሪካ በአፓርታይድ ላይ ዘመቻ ከፈተች፡፡

ጋሼ ይድነቃቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የደቡብ አፍሪካ ጥቁር የስፖርት ሀላፊዎችን ሮም ጣሊያን ሀገር እ.ኤ.አ በ1960 አግኝቶ አነጋገራቸው፡፡ ከዚያም ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ጃንሆይ የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው አዘው አፍሪካን ሊጎበኙ ቻሉ፡፡ ሲመለሱም ኮልፌ የውትድርና ትምህርት ቀስመው ሀገራቸው ሲገቡ ተይዘው ነው ለ27 ዓመታት የታሰሩት፡፡

አስከፊው የአፓርታይድ የፖለቲካ ስርዓትን ለመጀመሪያ ጊዜ ያጠፋው የስፖርቱ ዓለም ነው፡፡ እዚህ ላይ የጋሼ ይድነቃቸው እና የኢትዮጵያ ሚና ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው ማስታወስ ይገባል፡፡

እ.ኤ.አ 1968 ሜክሲኮ ሲቲ ከግራ ወደ ቀኝ፡ ሻለቃ ኦኒ ኒስካኔን (የአበበ ቢቂላ እና ማሞ ወልዴ አሰልጣኝ)፥ አምባሳደር ጌታቸው በቀለ፥ ሙሴ ጋንጋ፥ ዶ/ር አብርሃም ተድላ (የተሸሸጉት)፥ ጋሼ ይድነቃቸው ተሰማ፥ መቶ አለቃ ማሞ ወልዴ (የኦሊምፒክ ማራቶን ሻምፒዮን)፥ ኮሎኔል በቀለ ግዛው፥ አቶ ገብረእግዚአብሔር፥ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ እና አቶ ንጉሴ ሮባ

ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ1968 ወደ ሜክሲኮ ለኦሊምፒክ ጨዋታ ለመሄድ ስንዘጋጅ የኢንቴርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ደቡብ አፍሪካን መጋበዙን ሰማን፡፡  የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንቱ ጋሼ ይድነቃቸው እና ዋና ጸሀፊው እኔ ከተመካከርን በኋላ ደቡብ አፍሪካ ባለችበት ኢትዮጵያ በውድድሩ አትካፈልም የሚል ዜና አስተላለፍኩ፡፡ ኢትዮጵያን ተከትለውም 49 ሀገራት ደቡብ አፍሪካ ከተጋበዘች አንካፈልም በማለት አስታወቁ፡፡

በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ የሜክሲኮው አምባሳደር፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አቶ ከተማ ይፍሩ እና ጠቅላይ ሚንስትሩ ጸሀፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ዘንድ ቀርበው ሲጠይቁ ‹‹እኛ ኢትዮጵያ እንድትወጣ አላዘዝንም›› የሚል መልስ ሲሰሙ አምባሳደሩ ‹‹ጃንሆይ ጋር አቅርቡኝ›› ብለው ጠየቁ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ለጃንሆይ መልስ የሚሰጥ ስለጠፋ፡ ጃንሆይም ‹‹ይድነቃቸውን ጥሩት›› ብለው አዘዙ፡፡ ‹‹አንተነህ ወይ ኢትዮጵያ በሚክሲኮው ኦሊምፒክ አትካፈልም ብለህ የወሰንከው?›› ብለው ሲጠይቁት፤ ጋሼ ይድነቃቸውም ‹‹አዎን እኔ ነኝ›› ብሎ መለሰ፡፡ ‹‹አክሊሉን ወይም ከተማን ሳታማክር?›› ብለው በድጋሚ ጠየቁት፤ እርሱም ‹‹ግርማዊነትዎ የሰጡት ቋሚ ትእዛዝ አለ ይኼውም፤ ደቡብ አፍሪካ ያለችበት የትኛውም አይነት ዝግጀት ውስጥ ኢትዮጵያ እንዳትካፈል የሚለውን መመሪያ በመከተል ነው›› ብሎ መለሰላቸው፡፡ ጃንሆይም ‹‹በል ይሄንን ሜክሲኮ ኤምባሲ ሂደህ ለአምባሳደሩ አስረዳው›› ብለው አዘዙት፡፡

ከዚያም አለምአቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሁኔታው ስላላማረው የደቡብ አፍሪካን ግብዣ ሰርዞ ሁላችንም ሜክሲኮ ልንገኝ ችለናል፡፡ ጃንሆይም የልጅ ልጃቸው ልዑል ዳዊት መኮንን ከእኛ ጋር እንዲሄድ አዘው አብሮን ሰንበቷል፡፡

ከዚያም ደቡብ አፍሪካ ከሁሉም አለምአቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ውስጥ እንድትወጣ ኢትዮጵያ ዘመቻ ማካሄድ ጀመረች፡፡ በዚህም ከአይ ኦ ሲ፣ ከፊፋ፣ ከወርልድ አትሌቲክስ እና ከሌሎችም አባልነቷ ታገደች፡፡

ደቡብ አፍሪካ ዳግም ወደ ስፖርቱ አለም የተመለሰችው በ1992 የባርሴሎና ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ኔልሰን ማንዴላ በተገኙበት ነው፡፡ የዚያ ውድድር ዋና ትዕይንት ደግሞ ደራርቱ ቱሉ በ10,000ሜትር አሸንፋ ሁለተኛ ከወጣችው ደቡብ አፍሪከዊቷ ነጭ አትሌት ኤሌና ማየር ጋር ሆነው ስቴዲየሙን ሲዞሩ ተመልካቾቹ ቆመው ሲያጨብጭቡ የነበረው ክስተት ነበር፡፡ ደራርቱ ቱሉ ጨዋ ኢትዮጵያዊት በደግነቷ፣ በሩህሩህነቷ እና በየዋህነቷ የምትደነቅ ጥሩ ወዳጄ ነች፡፡

በጸረ አፓርታይድ ትግሉ ወቅት አስቸጋሪ ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ ፊፋ የደቡብ አፍሪካ ነጮችን ለመደገፍ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያደርገው ጥረት ነበር፡፡ ጋሼ ይድነቃቸውን እና የፊፋውን ፕሬዝዳንት ሰር ስታንሌ ራውስን ያጣላቸውም ይሄው ጉዳይ ነው፡፡

ፊፋ እ.ኤ.አ በ1966 በእንግሊዝ ይካሄድ በነበረው የዓለም ዋንጫ ውድድር አፍሪካ እና ኤዥያ ማጣሪያ አዘጋጅተው አሸናፊው አንድ ቡድን እንዲካፈል የሚል ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡

ጋሼ ይድነቃቸውም ለራሷ ለአፍሪካ አንድ ቦታ ካልተሰጣት በዚህ ማጣሪያ አትካፈልም በማለት ከውድድሩ እንድትወጣ ሲያደርጉ ኤዥያ ማጣሪያውን አዘጋጅታ፡ አሸናፊዋ ሰሜን ኮሪያ  በውድድሩ ተካፍላለች፡፡

ይኼው ሙግት ቀጥሎ እና የጋሼ ይድነቃቸው ትግል ፍሬ አፍርቶ እ.ኤ.አ በ1970 ለሜክሲኮው የአለም ዋንጫ አፍሪካ የራሷን ስፍራ አግኝታ ሞሮኮ ተካፈለች፡፡ ይህንን የአለም ዋንጫ ከጋሼ ይድነቃቸው ጋር በመሆን እኔ ፣ አቶ ብርሃኑ እንዳለ፣ አቶ ፍስሐዬ ሐረጎት፣ አቶ ቱፋ ሻይ አቶ አሳዶር ቮርፖሪያን እና ባለቤቱ ወደ ሜክሲኮ ተጉዘን ተመልክተናል፡፡

የስቶክማንድቪል  ሆስፒታል ጉብኝት

እ.ኤ.አ በ1971 ሉክሰምቡርግ ላይ በተካሄደው ጉባኤ ነበር ጋሼ ይድነቃቸው ተሰማ  የአለምአቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ሆኖ የተመረጠው፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ  በዲሞክራሲያዊ መርህ መሰረት አንድ ሀገር በኮሚቴው ውስጥ አንድ አባል ብቻ እንዲኖረው ‹‹ አንድ ሀገር፡ አንድ አባል›› የሚል ዘዴ መቀየስ አለበት በማለት በኮሚቴው ውስጥ ፍትሀዊ ውክልና እንዲኖር  አጥብቆ ይከራከር ነበር፡፡

ከዚህ ጉባኤ ጉዞ መልስ ነበር፡ ወደ እንግሊዝ ሀገር በማቅናት በመኪና አደጋ ጉዳት ደርሶበት ህክምናውን በስቶክማንድቪል ሆስፒታል ውስጥ ሆኖ እየተከታተለ የነበረውን ጀግናውን አትሌት አበበ ቢቂላን የጠየቅነው፡፡

አበበን ከመኪና አደጋው ዜና መሰማት በኋላ ከመላው አለም እና ከልዩልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚጎርፉ የማጽናኛ እና የሚያበረታቱ  ብዙ ደብዳቤዎች ደርሰውት ባንድ ጆንያ ውስጥ ታጉሮ ተቀምጦ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሀፊ እንደመሆኔ መጠን በሱ ስም መልስ ለመስጠት አንዳንድ ደብዳቤዎችን መርጬ ወሰድኩ፡፡ ለአበበ ደብዳቤ ከጻፉ ታላላቅ ሰዎች መካከል የብሪታኒያ ንግስት ኤሊዛቤት እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ይጠቀሳሉ፡፡ እንዲያውም ንግስት ኤሊዛቤት ሆስፒታል ድረስ ሄደውም ጠይቀውታል፡፡

ጋሼ ይድነቃቸው የአፍሪካ ጠበቃ

እ.ኤ.አ በ1981 ሎሜ – ቶጎ ላይ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (አኖካ) ጋሼ ይድነቃቸው ባረቀቀው መተዳደሪያ ደንቦች አማካኝነት ተመሰረተ፡፡

ጋሼ ይድነቃቸው የዓለም የስፖርት እንቅስቃሴ መመሪያዎችን አበጥሮ ስለሚያውቅና የማንኛውንም ስብሰባ ሰነዶች በደምብ አጥንቶ ስለሚካፈል፡ በሁሉም ስፍራ አፍሪካውያን ኃላፊነቱን የሚጥሉት እርሱ ላይ ነው፡፡ ጋሼ ይድነቃቸው የአፍሪካ ጠበቃ ነው በማለት ሁሉም ለምክር የሚመጡትም እርሱ ዘንድ ነበር፡፡

ብዙዎቹ አለምአቀፍ የስፖርት ተቋማት ሲመሰረቱ አፍሪካ አልነበረችም ስለዚህ መብቷን ለማስከበር ታጋይ ያስፈልጋት ነበር፡፡ ሁሉም አፍሪካዊ የሚኮራበት ታጋይ ደግሞ  ጋሼ ይድነቃቸው ተሰማ ነበር፡፡ ጋሼ ፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛን አቀላጥፎ በመናገሩ የተነሳ  ከሁሉም የአፍሪካ የስፖርት መሪዎች ጋርም በሚገባ ይተዋወቅ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጋሼ ይድነቃቸው በግል ባህሪይው ተግባቢ እና ቀልድ አዋቂም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ እ.ኤ.አ የ1968ቱ የሜክሲኮ የኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ትሪቡን ቁጭ ብለን የማሞ ወልዴን የ10000 ሜትር ሩጫ ስንከታተል በአንድ ሴኮንድ ልዩነት የወርቅ ሜዳሊያዋ አመለጠችው፡፡ ያን ጊዜ አንድ የኮንጎ የስፖርት ኃላፊ ይመጣና ጋሼ ይድነቃቸውን ‹‹ ተሰማ ለጥቂት ወርቅ አመለጠህ ይለዋል›› እርሱም መልሶ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ወርቅ ሞልቷል የቸገረን ብር ብቻ ነበር›› ሲል መልሶለታል፡፡

አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ከፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ጋር እ.ኤ.አ 1994 ኬፕታውን ደቡብ አፍሪካ 

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *