በ ኃይለእግዚአብሔር አድሐኖም

አዲስ አበባ – ነሀሴ 25/2011 ዓ.ም – ላለፉት ተከታታይ ሁለት ሳምንታት በሞሮኮ አስተናጋጅነት ሲከናወን የሰነበተው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ዛሬ አመሻሽ ላይ በሚካሄድ የመዝጊያ ስነስርዓት ፍጻሜውን ያገኛል።

በአፍሪካ ህብረት የስፖርት እና ባህል ኮሚሽን የበላይ ጠባቂነት እና በአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ህብረት (አኖካ) አስተባባሪነት በየአራት አመቱ የሚካሄደው ይህ ውድድር ዘንድሮም በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር  ከ53 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ4300 በላይ አትሌቶች የተሳተፉበት ደማቅ የውድድር ቆይታን አሳልፏል።

ኢትዮጵያም ለዚህ ውድድር ከመንግስት እንደተገኘ በተገለጸ የ60 ሚሊዮን ብር የባጀት ድጋፍ  ለሶስት ወራት የቆዬ ከፍተኛ የሚባል ዝግጅት በማድረግ፤ 188 ስፖርተኞችን በ13 የስፖርት አይነቶች ለማሳተፍ እና 28 ሜዳሊያዎችን ለማሸነፍ አቅዳ ነበር ወደ ስፍራው የተጓዘችው።

ነገር ግን የዚህ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ውጤት ለውድድሩ ዝግጅት ሲባል እንደተመደበው ባጀት፥ እንዳሳተፈችው የስፖርተኛ እና እንደተሳተፈችበት የስፖርት አይነት ብዛት  እንዲሁም እንደተደረገው ቅድመ ዝግጅት አልሆነም።

ኢትዮጵያ በውድድሩ 6 የወርቅ፣ 5 የብር እና 12 የነሀስ በድምሩ 23 ሜዳሊያዎችን በመሠብሰብ ከአጠቃላይ ተሳታፊዎች 9ኛ ደረጃን በመያዝ ለማጠናቀቅ ችላለች።

ይህ ውጤት ከአራት አመታት በፊት በኮንጎ ብራዛቪል ከተመዘገበው 7 የወርቅ፥ 5 የብር እና 10 የነሀስ ሜዳሊያዎች (22) እና ካጠናቀቀችበት 10ኛ ደረጃ አንጻር ሲታይ በአጠቃላይ የሜዳሊያ ብዛት እና ደረጃ መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም የወርቅ ሜዳሊያ ብዛት እና የዘንድሮውን ዕቅድ ማሳካት ግን አልተቻለም።

በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ ከተሳተፈችባቸው 13 የስፖርት አይነቶች ሜዳሊያ ማግኘት የተቻለው በአራቱ ማለትም  በአትሌቲክስ፥ ብስክሌት፥ ቦክስ እና ወርልድ ቴኳንዶ ብቻ መሆኑ አሁንም በሌሎቹ የስፖርት አይነቶች ላይ መሰራት ያለባቸው ቀሪ የቤት ስራዎች እንዳሉ ያመላከተ ውድድር ነበር ለማለት ያስደፍራል።

የሴቶች 10,000ሜ አሸናፊዎቹ ጸሀይ፥ ዘይነባ እና ደራ  – ከሸላሚዋ ኮ/ል ደራርቱ ቱሉ ጋር – ፎቶ Carole 

የተለመደው ውጤታማነት ያልተለየው የአትሌቲክስ ስፖርት በዚህ ውድድር ላይ ከአጠቃላይ የአትዮጵያ ውጤት 78% (18 ሜዳሊያ) ማስመዝገብ ችሏል፡ በዚህም ምክንያት በአትሌቲክስ ብቻ ያለውን ደረጃ ከተመለከትን ኢትዮጵያ ከናይጀሪያ እና ኬንያ በመቀጠል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በተለይም በሴቶች 10,000ሜ እና ግማሽ ማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶስት ተከታትለው በመግባት አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገባቸው በጉልህ የሚታወስ ነው። በአንጻሩ ብዙ የተጠበቀው የወንዶች 5000ሜ ላይ ምንም አይነት ሜዳሊያ አለመገኘቱ ግን የሚያስቆጭ ነበር።

ግብጽ ፥ ናይጀሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ከብዙሃኑ በሰፊ ልዩነት ወድድሩን በቅደምተከተል በበላይነት ያጠናቀቁ ሀገራት ናቸው።

በ12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ሜዳሊያ ያሸነፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሙሉ ስም ዝርዝር

የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎች

1. ብርሃኑ ወንድሙ በ10, 000ሜ ወንዶች
2. ሂሩት መሸሻ በ800ሜ ሴቶች
3. ታሪኩ ግርማ ወርልድ ቴኳንዶ ከ63ኪግ በታች ወንዶች
4. መቅደስ አበበ በ3000ሜመ ሴቶች
5. ጸሀይ ገመቹ በ10,000ሜ ሴቶች
6. ያለምዘር የኋላ በሴቶች ግማሽ ማራቶን

የብር ሜዳሊያ አሸናፊዎች

1. ሀዊ ፈይሳ በ5000ሜ ሴቶች
2. ጌትነት ዋለ በ3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች
3. ዮሐንስ አልጋው በ20ኪሜ የወንዶች ርምጃ
4. ዘይነባ ይመር በ10,000ሜ ሴቶች
5. ደጊቱ አዝመራው በሴቶች ግማሽ ማራቶን

የነሀስ ሜዳሊያ አሸናፊዎች

1. አርአያት ዲቦ በሴቶች የከፍታ ዝላይ
2. ጀማል ይመር በ10,000ሜ ወንዶች
3. አለሚቱ ታሪኩ በ5000 ሜትር ሴቶች
4. የብስክሌት የሴቶች የቡድን ታይም ትሪያል
5. ጸባኦት ጎሳዬ ወርልድ ቴኳንዶ ሴቶች ከ53 ኪግ በታች
6. ሰለሞን ቱፍ ወርልድ ቴኳንዶ ወንዶች ከ54 ኪግ በታች
7. የኋልዬ በለጠው በ20ኪሜ የሴቶች ርምጃ
8. ወይንሸት አንሳ በ3000ሜመ ሴቶች
9. ደራ ዲዳ በ10,000ሜ ሴቶች
10. ዳዊት በቀለ በ52ኪግ ቦክስ ወንዶች
11. መሠረት በለጠ በሴቶች ግማሽ ማራቶን
12.  ለምለም ሀይሉ በ1500ሜ ሴቶች

author image

About Haileegziabher Adhanom

Sports Writer & Managing Editor

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *