የግል ምልከታ| በ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ|ለ ልዩ ስፖርት ብቻ | 


አዲስ አበባ – ነሀሴ 21/2011ዓ.ም – በእግር ኳስ ፌደሬሽን ወይም ማህበራት ከጠቅላላ ጉባኤው ቀጥሎ ከፍተኛው የስልጣን አካል ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ (executive committee) ነው፡፡

የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢ በመሆን የእግር ኳሱን እንቅስቃሴ የሚመሩ ናቸው ፡፡ በጠቅላላ ጉባኤ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ስራ ላይ መዋላቸውን የሚከታተሉ ለሚመሩት እግር ኳስ መመሪያ (regulation) የማውጣት ስልጣን የተሰጣቸው የፅ/ቤቱን (administration) ወይም የአስተዳደር ስራን በየጊዜው የሚከታተሉና ውሳኔ የሚሰጡ ጠቅላላ ጉባኤውንና ፅ/ቤቱን ድልድይ ሆነው የሚያገናኙ የእግር ኳስ አደረጃጀት ልብ ናቸው፡፡

በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚያገለግሉ አባላት የእግር ኳስ አሰራርን ጠንቅቀው የሚያውቁ ለእግር ኳስ ልዩ ፍቅር ያላቸው ተለዋዋጭ ከሆነው የእግር ኳስ ዓለም ጋር አብረው መራመድ የሚችሉና ለዚህም የመሪነት ክህሎት ያላቸው መሆን ይኖርባቸዋል ፡፡

የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ

በስራ አስፈፃሚ የሚካተቱ የኮሚቴ አባላት በቀጥታ ከእግር ኳስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች (individuals) ሊሆኑ ይገባል፡፡ በደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ማህበር የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ  አባላት ብዛት 41 እንደሆነ በቀጥታ ከእግር ኳሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን መተዳደሪያ ደንባቸው ያሳያል፡፡

አንድ ፕሬዚደንት እና አራት ምክትል ፕሬዚደንቶች ይኖሩታል፡፡ አንዱ ምክትል ፕሬዚደንት የብሄራዊ እግር ኳስ ሊግ (national soccer league) ሊቀመንበር ነው፡፡ 28 የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ከክልል ፌደሬሽኖች የሚመረጡ ናቸው፡፡ ስድስት የኮሚቴ አባላት ከብሄራዊ እግር ኳስ ሊግ  የሚመረጡ ናቸው፡፡

በጋና እግር ኳስ ማህበር የስራ አስፈፃሚ ቦርድ ብዛት 22 እንደሆነ መተዳደሪያ ደንባቸው ይገልፃል፡፡ ከጠቅላላ ጉባኤው የሚመረጥ አንድ ፕሬዚደንትና አንድ ም/ ፕሬዚደንት የአስሩ የክልል እግር ኳስ ማህበራት በፕሬዚደንትነታቸው በስራ አስፈፃሚ ቦርድ ይወከላሉ ፡፡

የፕሪሚየር ሊግ ቦርድ ስድስት ተወካዮች በስራ አስፈፃሚ ቦርድ ውክልና ተስቷቸዋል፡፡በተመሳሳይ የአንደኛ ዲቪዚዮን ሊግ ቦርድ (division one league bord) አራት ተወካይ በስራ አስፈፃሚ ቦርዱ ቦታ አላቸው፡፡

በኬንያ እግር ኳስ ማህበር ብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ብዛት 12 ሲሆን አንድ ፕሬዚደንት፤ አንድ ምክትል ፕሬዚደንት፤ የኬንያ ፕሪሚየር ሊግ ኮሚቴ፤ አንድ ተወካይ የኬንያ አንደኛ ዲቪዚዮን (division one league) አንድ ተወካይ እና የስምንቱ ክፍለ ሀገራት እግር ኳስ ማህበር ተወካዮች ናቸው ፡፡

እኛስ?

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አደረጃጀትን በተመለከተ በተሸሻለው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 28 ላይ፤- ‹‹ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥንቅርና ምርጫ
1. የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ 11 አባላት ያሉት ሆኖ ጥንቅሩ እንደሚከተለው ይሆናል ፡፡
ሀ/ ፕሬዚደንት
ለ/ ም/ፕሬዚደንት
ሐ/ 9 አባላት
2. የፅ/ቤት ኃላፊው ያለድምፅ በአባልነት ይሳተፋል ፡፡
3. ጠቅላላ ጉባኤው ለፕሬዝዳንት ከተጠቆሙት ዕጩዎች መካከል ፕሬዚደንቱን ይመርጣል ፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ለስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ አባልነት ከተመረጡት መካከል ም/ፕሬዚደንቱን ይመርጣል›› በሚል ይገልፀዋል ፡፡

ከዚህ አንቀፅ መረዳት እንደሚቻለው 11 የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መኖራቸውን እና ከእነዚህም ፕሬዚደንትና ም/ፕሬዚደንት እንደሚመረጥ እንጂ የኮሚቴ አባላት ጥንቅር ወይም ውክልና ከየትኛው ዘርፍ ክልል ወይም ከተማ አስተዳደር መሆኑን በግልፅ አያሳይም ፡፡

የማን ውክልና?

ከላይ በገለፅናቸው ሀገራት እግር ኳስ ማህበራት የክለቦች ውክልና እና የሚወከሉበትም ብዛት  በግልፅ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ተገልጿል፡፡  ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ያውም ውድድርን ዋናው ስራው አድርጎ ለሚንቀሳቀስ ፌዴሬሽን በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ የክለቦች ውክልና አለመኖሩ የሚገርም ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ  የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ችግር ብቻ ሳይሆን ክለቦችም ራሳቸውን አደራጅተው ህጋዊ ተቋም ፈጥረው መንቀሳቀስ አለመቻላቸው ውክልና ለማጣታቸው ተጠያቂዎች ናቸው፡፡

11 የኮሚቴ አባላት ዘጠኙን የክልል መስተዳድሮችና ሁለቱን የከተማ አስተዳደር የያዙ ውክልና ነው ሊባል ይችላል። ነገር ግን በመተዳደሪያ ደንቡ በግልፅ ውክልናቸውን የሚያሳይ አንቀፅ የለም ፡፡

በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀፅ 31 ንዑስ አንቀፅ 7 ላይ ‹‹አንድ የፌዴሬሽን አባል ሊግ ክለብ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ በአንድ የምርጫ ዘመን ከአንድ የበለጠ ተመራጭ ሊኖረው አይችልም›› ይላል ፡፡

ነገር ግን በ2006 ዓ.ም በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፌደሬሽን የተወከሉ ሁለት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በአንድ የምርጫ ዘመን በስራ አስፈፃሚነት ተመርጠው ፌዴሬሽኑን እያገለገሉ ይገኙ ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ ያወጣውን ደንብ አውቆ አክብሮና ሌሎችም እንዲያከብሩት በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት ከላይ የተገለፀው አንቀፅ ያመላክታል፡፡

ትርፍ ሰዓት-ለእግር ኳስ?

በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት የሚመረጡት ግለሰቦች በከፍተኛ የመንግስት ወይም የልማት ድርጅቶች ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

በሚያገኙት ትርፍ ሰዓትም ሌሎች ስራዎች (comittement) ያላቸው በመሆኑ በቂ ጊዜ ለእግር ኳሱ መስጠት አይችሉም፡፡ ሁልጊዜ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ውሳኔ የሚወስነው በተጓደሉ ኮሚቴዎች ነው፡፡ በተወሰኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ላይ ስራ በዝቶ የሚታየውም ለዚህ ነው፡፡

በእያንዳንዱ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ በቂ ዕውቀት ኖሯቸው ስራውን ሊሰሩ የሚችሉበት ስርዓት (system) ስለሌላቸው በየጊዜው በሚፈጠሩ አለመግባባቶች አንዱ አንዱን ሲያግድ መልሶ ሲያስገባ እንደገና ሲያግድ ለእግር ኳስ ልማት የሚውለውን ጊዜ ጥቅም በማይሰጡ አጀንዳዎች እንዲያልፍ ያደርጉታል ፡፡

የእግር ኳሱ የደም ስር ነው ያልነው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በአደረጃጀት በአሰራርና በሰው ሀይል ችግር ተተብትቦ በመያዙ ደም ስሩ ጠቧል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ከነጭራሹ ደምስሩ ሊዘጋ ይችላል፡፡

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በቀጣይም  ቋሚ ኮሚቴዎችን በተመለከተ ሌሎች መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ።


ስለ ጸሀፊው


አቶ ገዛኸኝ ወልዴ

ስራ:

በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙ

የትምህርት ደረጃ፡

የማስተርስ ዲግሪ በህዝብ አስተዳደር እና የልማት አመራር

ቢኤ ዲግሪ በኢንፎርሜሽን ሳይንስ

የፊፋ የአስተዳደር እና አመራር ስልጠና የወሰዱ

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *