በአንጋፋው ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔፓሪስ – ፈረንሳይ – ነሀሴ 2011 ዓ.ም – ኢትዮጵያ ከኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ጋር የተዋወቀችው እ.ኤ.አ በ1924 የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴን (አይ.ኦ.ሲ) እ.ኤ.አ በ1894 የመሠረቱትና የመጀመሪያውን ዘመናዊ የኦሊምፒክ ጨዋታ ያዘጋጁት ፈረንሳያዊ ምሁር ፒየር ደ ኩበርተን፤ ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን የኢትዮጵያ አልጋ ወራሽን በፓሪስ ከተማ ላይ በሚካሄደው የአሊምፒክ ጨዋታ ላይ እንዲገኙ ስለጋበዟቸው ነው፡፡

ከልዑልነታቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሊምፒክ ጨዋታ የተመለከቱ ኢትዮጵያውያኖችም፡ ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት፣ ራስ ስዩም መንገሻ፣ ራስ ጉግሳ ዓርዓያ፣ ራስ ናደው አባ ወሎ፣ ደጃዝማች ገብረ ስላሴ፣ ደጃዝማች ሙሉጌታ ይገዙ፣ ብላታ ሕሩይ ወልደስላሴ፣ ልጅ መኮንን እንዳልካቸው፣ ሊጋባ ወዳጄ ውቤ፣ አቶ ሳህሉ ጸዳሉ፣ አቶ ብርሃነ ማርቆስ እና አቶ ተስፋዬ ተገኝ ነበሩ፡፡ ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንንም ያኔውኑ ኢትዮጵያ በአይ.ኦ.ሲ እንድትታወቅና አትሌቶቿ እ.ኤ.አ በ1928 በአምስተርዳም – ሆላንድ በሚደረገው የኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ እንዲካፈሉ ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡

በዚያን ጊዜ የአይ.ኦ.ሲ ፕሬዝዳንት የነበሩት ስፍራቸውን ለቤልጂኩ ተወላጅ ሌባዬ ላቱር አስረክበው ስለነበር ልዑል ራስ ተፈሪ ከቤልጅክ መንግስት ጋር አዲስ አበባ ባለው ኤምባሲ አማካኝነት ውይይት አድርገው ነበር፡፡በፈረንሳይ ቋንቋ የተጻፉት ደብዳቤዎችም በእኔ እጅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በዚያን ዘመን አፍሪካን የመናቅ ጠባይ ስለነበረ ሙከራው ሊሳካ አልቻለም፡፡

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ተብለው ከነገሱ እና ፋሽስቱ ጣልያን አገራችንን ለቆ ከወጣ በኋላ ነው እ.ኤአ. በ1948 የኢትዮጵያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ያቋቋሙትና በአንዱ አንቀጽ ላይ የኢትዮጵያ አሊምፒክ ኮሚቴ ተመስርቶ ‹‹አትሌቶቻቻን በኦሊምፒክ ጨዋታ እንዲካፈሉ‹‹ የሚል ውሳኔ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ የሰፈረው፡፡

የስፖርት ኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ጀኔራል ዐቢይ አበበ፣ ምክትል ፕሬዝዳንት ፊታውራሪ ደምሴ ወልደአማኑኤል ፣ ዋና ጸሀፊ አቶ ዓምደሚካኤል ደሳለኝ፣ ገንዘብ ያዥ ሻለቃ ኮስትሮፍ ቦጎስያን ሲሆኑ አባሎች ኮሎኔል ክፍሌ ዕርገቱ፣ ሙሴ ኤድዋር ቪርቪሊል፣ ሙሴ ካችክ ቦጎስያን እንዲሆኑ በግርማዊነታቸው መልካም ፈቃድ መሾማቸው በነጋሪት ጋዜጣ ቁጥር 112- 1941 ላይ ታትሟል፡፡

የኦሊምፒክ ጨዋታ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ776 ዓ.ዓ ኦሎምፒያ በምትባል የግሪክ ከተማ ይካሄድ እንደነበር የሚያውቁት ጃንሆይ፣ ኤድዋር ቪርቪሊል የሚባሉት የግሪክ ተወላጅ እና የአዲስ አበባ ነዋሪ የኮሚቴው አባል አንዲሆኑ መወሰናቸው ምክንያት ነበረው፡፡

ኢትዮጵያ በአይ.ኦ.ሲ እንድትመዘገብ አስፈላጊውን እርምጃዎች እንዲያሳኩ ሃላፊነቱም ለእኚሁ ግሪካዊ ተሰጠ፡፡ እርሳቸውም እ.ኤ.አ በ1949 የመጀመሪያ ደብዳቤያቸውን ጽፈው ሁሉንም ነገር ካስተካከሉ በኋላ፣ እንዳጋጣሚ እ.ኤ.አ በ1954 አቴንስ (ግሪክ) ከተማ ተሰብስቦ የነበረው የአይ.ኦ.ሲ ስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀበላት፡፡

የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ተሳትፎ

ከዚያም ሙሴ ቪርቪሊል የስፖርት ኮንፌዴሬሽኑ ዋና ጸሀፊ ሆነው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤአ. በ1956 በሜልቦርን (አውስትራሊያ) በተካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታ እንድትካፈል አደረጉ፡፡ ከአመታት በፊት ለክቡር ዘበኛ ፈረሰኛ ክፍል የሚያገለግሉ ትላልቅ ፈረሶች ለመግዛት አውስትራሊያ ሄደው የነበሩት ሻለቃ ኮስትሮፍ ቦጎስያን የኮንፌዴሬሽኑ ገንዘብ ያዥ እና የዴሌጋሲዮኑ (የልዑክ ቡድኑ) መሪ ሆነው ተመረጡ፡፡

ከአዲስ አበባ ሜልቦርን ደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ ውድ ስለነበር ጄኔራል አቢይ አበበ ጃንሆይን አስፈቅደው ከኢትዮጵያ አየር ሀይል አንድ ዲሲን አውሮፕላን ተመድቦ ዴሌጋሲዮኑን ይዞ ተጓዘ፡፡ ሰባት ቀናትን የፈጀው ጉዞ ብዙ ሀገራትን አቆራርጦ ከ127 ሰዓታት በረራ በኋላ ሜልቦርን ደርሶ ተመልሷል፡፡አብራሪውም ወዳጄ ካፕቴን አለማየሁ ወልደሰንበት ነበር፡፡

 

እ.ኤ.አ በ1960 ነበር አቶ ይደነቃቸው ተሰማ የስፖርት ኮንፌዴሬሽኑ ዋና ጸሀፊ ሆኖ የተሸመው እና ሻምበል አበበ ቢቂላ የሚገኝበትን ዴሌጋሲዮንን እየመራ ወደ ሮም ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የተጓዘው፡፡ እስከዚያ ድረስ የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ብቻ ነበር፡፡

እኔም ያገሬ ህዝብ የኦሊምፒክ ፍልስፍናን እንዲረዳ ‹‹የኦሊምፒክ ጨዋታ›› የሚል መጽሀፍ አሳትሜ፡ የመጀመሪያውን እትም ሀምሌ 16 በጃንሆይ የልደት በዓል ቀን ቤተ መንግስት ሄጀ ለንጉሰ ነገስቱ አበረከትኩ፡፡ በጣልያን ወረራ ዘመን ስለ እግር ኳስ ጨዋታ ‹‹የሮማ ብርሀን›› በተባለው ጋዜጣ ላይ ይጽፉ የነበሩት እና ጣልያኖች ያቋቋሙትን የስፖርት ጽህፈት ቤት ተረክበው የሚያስተዳድሩት አቶ ዓምደሚካኤል ደሳለኝ ነበሩ፡፡

እርሳቸውም የኢትዮጵያ ማስታወቂያ መምሪያ ሀላፊ በነበሩበት ወቅት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከአዲስ አበባ ስታዲየም የራዲዮ መስመር ተዘርግቶ፣ እ.ኤ.አ በ1957 የኢትዮጵያ እና የሱዳንን ብሔራዊ ቡድኖች የእግር ኳስ ጨዋታ ለማስተላለፍ የበቃሁት፡፡ እኔም ‹‹ ለኢትዮጵያ ድምጽ ራዲዮ ጣቢያ›› እና አቶ አሀዱ ሳቡሬ ዋና አዘጋጅ በነበሩበት ‹‹ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ እንድሰራ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ ሆኜ የተቀጠርኩት በአቶ ዓምደሚካዔል ደሳለኝ ውሳኔ ነው፡፡

ጃንሆይ ስፖርት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ትልቅ ጥረት አድርገዋል፡፡ በትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር ላይ በመገኘት ዋንጫ እና ሜዳልያ ይሸልሙ ነበር፡፡ ጥንት እኛ ተማሪዎች ሆነን ለገና በዓል ቤተ መንገስት እየሄድን ሹራብ እና ብስኩት ከጃንሆይ እጅ እንቀበል ነበር፤ ሹራበቻችንንም ለሰፈር እግር ኳስ ግጥሚያዎች እንደ ማሊያ እንጠቀምባቸው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ ኮሚቴዋን የመሰረተችው እ.ኤ.አ በ1967 ነው፡፡ ከዚያ በፊት በአይ.ኦ.ሲ ይታወቅ የነበረው የስፖርት ኮንፌዴሬሽኑ ነበር፡፡ በዚህም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ፣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሀፊ ደግሞ እኔ እራሴ ሆነን ተመርጠን አገልግለናል፡፡

ጃንሆይ የልጅ ልጆቻቸው የኦሊምፒክን ፍልስፍና እንዲቀስሙ በማለት ይዘናቸው ወደ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች እንድንሄድ በሰጡት ትእዛዝ መሰረት እ.ኤ.አ በ1968 ልዑል ዳዊት መኮንን ሜክሲኮ፣ እ.ኤ.አ በ1972 ልዑል ሚካኤል መኮንን ሙኒክ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ለሜክሲኮ አሊምፒክ የእግር ኳስ ውድድር ለመካፈል በመጨረሻው የማጣሪያ ግጥሚያ ላይ በአንድ ዩጋንዳዊ ዳኛ ምክንያት ማለፍ ያለመቻሉን አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለጃንሆይ አስረድቶ፤ እርሳቸውም ሁኔታው ስላሳዘናቸው፤ ተጫዋቾቹ ወደ ሜክሲኮ እንዲሄዱ ትእዛዝ ሰጡ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከብሄራዊ ቲያትር እና ከሃገር ፍቅር የተውጣጡ 30 የሚሆኑ ሰዎች በጠቅላላው ወደ 60 የሚደርስ ዴሌጋሲዮን ነበር የተያዘው፡፡ በሜክሲኮ ያስተናገዱን አምባሳደራችን ደግሞ አቶ ጌታቸው በቀለ ነበሩ፡፡ በጊዜው መንግስት የፈቀደልንን ወጪ ስላጣጣምነው የሀገር ባህል ልብስ መግዣ አልተረፈንም ነበር፡፡ የደሌጋሲዮኑን ዩኒፎርም አቶ ተስፋዬ ዘለለው ዘንድ አሰፍተን፡ ሁሉም ሱፍ ለባሽ ሆኗል፡፡ ቁም ነገሩ ግን ያገራችንን ልብስ መልበስ ነበር፡፡

የኦሊምፒክ ኮሚቴው ዋና ጸሀፊ እኔ ስለነበርኩ ዘዴ መፈለግ ነበረብኝ፡፡ አንድ ቀን ለወዳጆቼ ወሬ ሳወራ የአዲስ አበባን ባንክ የመሰረቱት አቶ አበበ ሀብተዮሐንስ ‹‹እንዴት ካኪ ማሰፋት እና ነጠላ መግዛት አቃታችሁ?›› በማለት መላው የኢትዮጵያ ዴሌጋሲዮንን የሀገር ልብስ አንዲለብስ ወጭውን ሸፈኑልን፡፡ ኢትዮጵያም ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ አደባባይ ያገር ባህል ልብስ የለበሰ ዴሌጋሲዮን አሰለፈች፡፡

የሚያሳዝነው አሁን ሀገራችን በዘር ተከፋፍላ በምትሰቃይበት ዘመን የየትኛውን ብሔር ይልበሱ በማለት የፖለቲካ ሰዎች ስላልተስማሙ የኢትዮጵያ አትሌቶች ቱታ ለብሰው መሰለፍ ጀምረዋል፡፡ በጃንሆይ ጊዜ የነበረው ክብር እና ኩራትም ድራሹ ጠፍቷል፡፡

ፍቅሩ ኪዳኔ፡ ለልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ እና ግዮን መጽሄት

author image

About Liyusport.com

ልዩ ስፖርት ድረ-ገጽ የኢትዮጵያን ስፖርት እና ከባቢውን በመሰረታዊነት ሊለውጡ የሚችሉ የባለሙያ ሃሳቦች: ትችቶች፡ የምርምር ውጤቶች እና ሀተታዊ ጽሁፎች በራሳቸው በባለሞያወቹ ብዕር እና አንደበት ተዘጋጅተው በጽሁፍ እና በድምጽ የሚስተናገዱበት፡ እንዲሁም የምርመራ ጋዜጠኝነትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጋዜጠኝነት ውጤት የሆኑ ፅሁፎች የሚቀርቡበት እና በአይነቱ ልዩ የሆነ የስፖርት ድረ-ገፅ ነው፡፡

You Might Also Like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *